Friday, 3 September 2021

ተያይዘው የወደቁ ወንድማማቾች (2ሳሙ. 2፥16)

Please read in PDF


ሳኦል የእግዚአብሔርን መንገድ ባለመከተሉ ምክንያት፣ እግዚአብሔር ዳዊትን “በትይዩ” ንጉሥ አድርጎ ቀባው። ለእግዚአብሔር ቃል ያልታዘዘውና እግዚአብሔርን ፈጽሞ ባለመፈለግ ባዛኙ ሳኦል፣ የዳዊትን መሾም ሲያውቅ፣ ዳዊትን ለመግደል የቻለውን ኹሉ ከማድረግ አላረፈም። በሜዳ፣ በምድረ በዳ፣ በዋሻ፣ በተራራ … ባገኘው ሥፍራ ኹሉ አሳድዶ ሊገድለው እጅጉን ፈለገው። ነገር ግን ዳዊትን መግደል ሳይቻለው፣ “ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ በመጡ ጊዜ ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኙአቸው። የሳኦልንም ራስ ቈርጠው የጦር ዕቃውን ገፍፈው ለጣዖታቱ መቅደስ ለሕዝቡም የምስራች ይሰጥ ዘንድ ወደ ፍልስጥኤማውያን አገር ሁሉ ሰደዱ።” በማለት እንዴት ባለ አስቀያሚ ሞት እንደ ሞተ ይነግረናል፤ (1ሳሙ. 31፥8-9)።


 

ዳዊት፣ አሳዳጁ ንጉሥ ሳኦል እንደ ንጉሥ ሳይኾን “እንደ ተርታ ሰው” በጊልቦዓ ተራራ መሞቱን ሲሰማ በብርቱ ሐዘን ተውጦ፣ “እናንተ የጊልቦዓ ተራሮች ሆይ፥ የሳኦል ጋሻ በዘይት እንዳልተቀባ፥ የኃያላን ጋሻ በዚያ ወድቆአልና ዝናብና ጠል አይውረድባችሁ፥ ቍርባንንም የሚያበቅል እርሻ አይሁንባችሁ” በማለት፣ ለሳኦል በመራራ ለቅሶ ቅኔን ተቀኘለት። ምንም እንኳ ሳኦል፣ ዳዊትን እንደ ጠላቱ ቢቆጥረውም፣ ዳዊት ግን ለሳኦል እጅግ ራራቶ አለቀሰለት! ከሳኦል ሞት በኋላ ዳዊት ዙፋኑን ወረሰ፤ ነገር ግን እንዲሁ ወረሰ ማለት ይከብዳል፤ ቀጥሎ የኾነው ይህን በሚገባ ያመለክታል።

ሰባቱ የመሸጋገሪያ ዓመታት

የይሁዳ ሰዎች፣ የዳዊትን መንገሥ አስቀድመው ቢያውጁም (2ሳሙ. 2፥4)፣ “የሳኦልም ጭፍራ አለቃ የኔር ልጅ አበኔር የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ወደመሃናይም አሻገረው፤ በገለዓድና በአሹራውያን በኢይዝራኤልም በኤፍሬምም በብንያምም በእስራኤልም ሁሉ ላይ አነገሠው።” (2ሳሙ. 2፥8-9)። የወንድማማቾቹ ቤት ለኹለት ተከፈለ። ለኹለት ተከፍሎ ብቻ ግን የቀረ አይደለም። ለሰባት ዓመት ከስድስት ወር እንዲህ በልዩነት ከተቀመጡ በኋላ፣ “የጽሩያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ባሪያዎች ወጥተው በገባዖን ውኃ መቆሚያ አጠገብ … በአንዱ ወገን እነዚህ፥ በሌላውም ወገን እነዚያ ኾነው … እርስ በእርስ እንቈራቈስ ወይም በጨበጣ ውጊያ ይዋጣልን” በማለት ዐሳቡን አበኔር አቀረበ፤ ኢዮአብም ተስማማ። ከዚያም ጐልማሶች፣ “… ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ አሥራ ኹለት፥ ከዳዊትም ባሪያዎች አሥራ ኹለት ተቈጥረው ተነሡ።” መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ቦታ የተከናወነውን ድርጊት እጅግ ልብ በሚሰብር መንገድ እንዲህ ብሎ ይገልጠዋል፤“እያንዳንዱ ሰው የባለባራውን ራስ በመያዝ ሰይፉን በጐን እየሻጠበት ተያይዘው ወደቁ። ስለዚህም በገባዖን የሚገኘው ያ ቦታ ስፍራ “የሰይፍ ምድር”[1] ተባለ።” (ቊ. 16 ዐመት)።

እጅግ ሊሰቀጥጥ በሚችል መልኩ ከዚያ በኋላ ጽኑ ሰልፍ ኾነ፤ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ ውጊያው ያለ ርኅራኄ ነፍስ ለነፍስ መነጣጠቅ ኾነ። ከዚያም አበኔር በጩኸት ቃል እንዲህ ሲል ተናገረ፣ “ይህ ሰይፍ ለዘላለም ማጥፋት አለበትን? ውጤቱ መራራ መኾኑን አንተስ ሳታውቅ ቀርተህ ነውን? ሰዎችህ ወንድሞቻቸውን ማሳደዱን እንዲያቆሙ ትእዛዝ የማትሰጣቸውስ እስከ መቼ ድረስ አለው?” (ዐመት) ኢዮአብም ከዚያ በኋላ ጦርነቱ እንዲቆም አዘዘ። ወደረኞቹ ወንድማማቾች ጨርሰው “ከመተላለቅ ለጥቂት ተረፉ”!

መውጫ!

ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያደረገችው ጦርነት ቁስሉ በሚገባ አልጠገገም፤ ወንድማማች ሕዝቦች ቢባባሉም፣ ጦር ተሳብቀው ከመተላለቅ ወንድምነቱ አላስጣላቸውም። ከተመሳሳይ የታሪክ ስህተት ላለመማር ደጇን በራስዋ ላይ የዘጋችውና ከእግዚአብሔር ቃል ርቃ የምትኖረው ኢትዮጵያ፣ አኹንም ገላጋይና ሸምጋይ “ጠፍቶ”፤ “እንግዳ ተቀባይ” የተባሉት የገዛ ልጆችዋ በመተላለቅ ላይ ናቸው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ተመሳሳይ ታሪክ መኖሩን አበክሮ ለትምህርትና ለተግሳጽ ይነግረናል፤ (1ጢሞ. 3፥16)።

ኢትዮጵያውያን የጦርነትን አስከፊነትና መራራነት እናውቃለን ብንልም፣ ዛሬም ግን መራራው ጦርነት አንዱ ምርጫችን ነው፤ ግን እስከ መቼ ይኾን መራርነቱ የማይጎፈንነን? እስከ መቼስ የወገን ሞት አይዘገንነን ይኾን? ማዶ ለማዶ ኾኖ፣ የጦርነት ነጋሪት ማስጎሰም፤ የጥላቻ እንቢልታ ማስነፋት፣ የጥፋት ከበሮ መደለቅ … ፍጻሜው ዕልቂትና ከንቱ ቁጭት ነው፤ ስንት ጊዜ ተያይዘን እንወድቃለን? እርስ በእርስ ስንት ጊዜ በጨበጣ ውጊያ፣ ስንት ጊዜው በመቈራቈስ በዓለሙ ኹሉ ፊት መሳቂያና መሳለቂያ እንኾናለን? ስንት ጊዜስ በእግዚአብሔር ፊት የእግዚአብሔርን መልክና አምሳል እናዋርዳለን? ማንስ ይኾን እርስ በእርስ መሳደዳችንን እንተው! ጦርነት ይብቃን! የሚል!?

ዛሬስ ተያይዘው ከወደቁት ምን እንማር ይኾን?!

 



[1] በዕብራይስጥ ሔልቃዝ አዙሪም ይባላል፤ ትርጕሙም የመሻሻጥ ምድር ወይም የጥላቻ ምድር ማለት ነው።

1 comment: