Please read in PDF
ሾላኮች በምን ይታወቃሉ?
አማኞች ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመናቸው የክርስቶስ ሕይወትና ትምህርት የሚያንጸባርቅ
ሕይወት ሊኖሩ ተጠርተዋል፤ ጌታችን ኢየሱስ ቅዱሳን ደቀ መዛሙርቱን እንደ ተናገረው፣ “ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ።” (ዮሐ. 15፥16) እንዳለው፣ ደቀ መዛሙርት ፍሬ ሊያፈሩና በፍሬአቸውም ኖረው ሊታዩ ተጠርተዋል። ፍሬ ኹለንተናዊ መገለጫ ነው፤ ጠባያችን፣ አስተሳሰባችን፣ ንግግራችን፣ ድርጊታችን … ኹሉ የፍሬያችን
መገለጫ ወይም የኖርንበት መታያችን ነው።
ያልኖርንበት ሕይወት ኾኖ አይገለጥም፣ የኖርንበት ግን በግብዝነት እልፍ
ጊዜ ልንደብቀው ብንጥር እንኳ አንድ ቀን መገለጡ አይቀርም። አምናለሁ
እያለ ነገር ግን ማመኑን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በፍሬ የማይገልጥ እርሱ አንድ ቀን ከዋናው ግንድ መቆረጡ አይቀርም። እየታጠቡ ጭቃነት፣ እየተፉ ዳግም መላስ፣ ከባርነት ነጻ ወጥቶ ዳግም ባርነትን
መመኘት፣ ከአጋንንት ነጻ ወጥቶ እንደ ተጠረገ ባዶ ቤት ያለ ፍሬና ያለ ሕይወት መኖር … ከቀደመ አስከፊ ሕይወት በባሰ ወይም መልሶ
ወደ አዘቅት መጣሉ አይቀሬ ነው።
እውነተኛ አማኝ
የተለወጠ ሕይወትና የተንዠረገገና እጅግ ያማረ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ አለው፤ አማኝ ምን ዓይነት ፍሬ ያፈራል ለሚለው በኹለት ስፍራ
የተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት፣ የእውነተኛ አማኝ ባሕርያት ኹነኛ ማሳያዎች ናቸው፤ አንደኛው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው
ትምህርቱ ላይ ያስተማረው፣ በተለምዶ አንቀጸ ብጹአን ተብሎ የሚጠራው ሲኾን እርሱም እንዲህ ይላል፣
“በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና። የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና። የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና። ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና። የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና። ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና። የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና። ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።” (ማቴ. 5፥3-10)
ሌላኛው ደግሞ ሐዋርያው
ቅዱስ ጳውሎስ፣
“የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው።”
በማለት የገለጣቸው
ናቸው።
አንዳንዶች እኒህ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች በዚህ ምድር የሚፈጸሙ ሳይኾኑ፣
ሌላ ቦታና ኹኔታን እንደሚጠብቁ አበክረው ያስተምራሉ፤ እርግጥ ነው፣ መንፈሳዊ አካል ስንለብስ እኒህን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች በምልአትና
በፍጽምና በሕይወታችን ይገለጣሉ። ነገር ግን በዚህም ሳለን እኒህ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች በሕይወታችን ይገለጣሉ፣ ለምሳሌ ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ በማለት ተናግሮአል፤ “ብዙ ፍሬ ብታፈሩና ደቀ መዛሙርቴ ብትሆኑ በዚህ አባቴ ይከበራል።” (ዮሐ. 15፥8)።
ፍሬ ባናፈራ፣ በአንደበታችን ብቻ እምነት አለን ብንል እግዚአብሔርን እናሰድባለን።
እንዲያውም ሾላኮችን
በመከተል ሊመጣ ያለውን ነገር ቅዱስ ጴጥሮስ ሲናገር እንዲህ ይላል፣ “… እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ፤ ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሉአቸዋል በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል።” (2ጴጥ. 2፥1-2)። በግልጥ ቃልም ለአርነት ተጠርተን
ፍሬ ባለማፍራት ራሳችንን ለባርነት አሳልፈን ብንሰጥ፣ ብርቱ ተግሳጽ እንዳለብንም ተነግሮአል፤ (ገላ. 5፥13)። ስለዚህም በዚህ እውነት ላይ ቆመን “ሾላኮችን በምን እናውቀዋቸዋለን?” ብለን
ብንጠይቅ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ቃል እኒህን ኹለት መሠረታዊ ማወቂያ መንገዶችን ያስቀምጥልናል፤
1.
በሚናገሩአቸው
ንግግር፦ እውነተኛና ብልኅ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የሾላኮቹን ንግግር ወዲያው ወይም መርምሮ የሚያውቅ ነው፤ ቅዱስ
ጳውሎስ እንደ ተናገረው “በሰይጣን እንዳንታለል፤ የእርሱን አሳብ አንስተውምና።” (2ቆሮ. 2፥11)። ሰይጣን ኹል ጊዜ የእኛን የቸለተኝት ዕድል ተጠቃሚ ነው። ልክ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የበደለን ወንድም በይቅርታ አለመቀበል ለሰይጣን
ዕድል እንደሚሰጥ እንዲኹ ደግሞ የስህተት ትምህርትን ቸል ማለት ለሰይጣን መልካም ዕድልን መፍጠር ነው።
ስለዚህም ሰይጣን ባዕድና ኑፋቄያዊ ትምህርቱን በሾላኮቹ አማካይነት የሚያስገባው በንግግር ነው፤ ልክ ሔዋንን አብሮ በንግግር
በመዘግየት የስህተት ዐሳብን ወደ ኅሊናዋ እንዳስገባው እንዲኹ ዛሬም የሚሠራው እንዲህ ባለው የክፋት አሠራር ነው። በሔዋን ንግግር ውስጥ “እግዚአብሔር አምላክ” ማለት ሲገባው፣ “እግዚአብሔር”
ብሎ ብቻ በመናገር አምላክን እንደ እኩያዋ እንድታየው አደረገ፤ ራሱን ግን እውነተኛና ዐሳቢ አድርጎ አቀረበ።
ንግግሮቹ ጣፋጭና
ሳቢ ናቸው። የዛሬዎቹም የስህተት መምህራን ትምህርታቸውና ሃሳባቸው እጅጉን ለሥጋ ጣፋጭ፣ ምቹና ደልዳላ ነው። እንዲያውም ቅዱስ ጳውሎስ የጣፋጭነቱን፤ የሳቢነቱን ልክ ጆሮ አሳካኪ ብሎታል፤
የራስ ጣፋጭ ንግግርን መስማት፣ ስሜት ቀስቃሽና ራስን አለልክ የሚክብ ትምህርትና ንግግርን መስማት የስሑት መምህራን ጆሮ አሳካኪ
በልካቸው የተሰፋ ጠባይ ነው፤ (2ጢሞ. 4፥3)።
እውነተኛ ደቀ
መዛሙርት ክርስቶስን እንጂ ፈጽሞ ራሳቸውን አይሰብኩም፤ “ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታ እንደ ኾነ እንጂ ራሳችንን አንሰብክምና፥” (2ቆሮ.
4፥5) እንዲል። በዚህ ዘመን ራሱን የማይሰብክ፣ በማናቸወም መንገድ ራሱን የማይገልጥ፣ የክርስቶስን ጽድቅና ቅድስና፣ ግርማና መውደድ፣
እርሱን ብቻ የሚሰብክ ማግኘት እጅግ ታላቅ መታደል ነው። ከትልቅ
እስከ ትንሹ ዛሬ ራሱን በመስበክና በማግነን እጅግ ተጠምዶአልና። ብዙዎች በዚህ መንገድ ሲመላለሱ ከኢየሱስ ፈጽመው እንደ ተለዩ እንኳ አያስተውሉም፤
እናም ከሾላኮችና ተከታዮቻቸው በብዙ መራቅ አይገባም ትላላችሁን?
2.
በፍሬአቸው፦ ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራው ስብከቱ የተናገረውን ደግመን ማንሣቱ እጅግ መልካም ነው፤
“የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፥ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም። መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።” (ማቴ. 7፥16-18)
ፍሬ ትምህርትንም
ሥራንም በአንድነት አመልካች ነው ብለናል፤ ምክንያቱም የሥነ ምግባር ውጤት ምንጩ ትምህርትና ዐሳብ ነውና። ሰው በትምህርት ከወደቀ ኹለንተናዊ በኾነ መንገድ በልምምዶቹና በአምልኮውም
ጭምር ፍግም ብሎ ይወድቃል። የአንዳንድ ነቢያትና አገልጋዮች ፍሬ
እሾኽና ኩርንችት በማፍራት ወዲያው ይታወቃል፤ ኀጢአተኝነታቸው ወዲያው ጐልቶ ይወጣል፣ የአንዳንዶች ግን ፈጽሞ ላይታወቅ ይችላል፤
የጌታን ትምህርት እያስተማሩ ራሳቸውን በመደበቅ ለረጅም ጊዜ ሊኖሩ ይችላሉ።
ምናልባትም እንዲህ
ያሉቱ አጋንንትን ጭምር በማውጣትና ታላላቅ ተአምራት በማድረግ ሊታወቁና ብዙዎችን በማስደመም ሊያስከትሉ ኹሉ ይችላሉ፣ ነገር ግን
ፈጽሞ መታለል የለብንም። ምክንያቱም እንዲህ ያሉ ሾላኮች የክርስቶስን
መስቀልና ሞት፣ ውርደቱንም፣ አለ ልክ ዝቅ ማለቱን፣ ስለ መከራም ጭምር ደፍረው ወይም ደጋግመው ሲናገሩ አንሰማቸውም። ስለዚህ ትምህርታቸው ከመስቀሉና ከመከራ የራቀ የስኬትና የድሎት፣ የተባርከሃልና
የያልፍልሃል ሲኾን፣ ኑሮአቸው ደግሞ ከኀጢአት በመራቅና ከኀጢአት
ጋር በመጋደል፣ ብሎም መከራንና ነቀፋን በመታገስ፣ ንስሐንና የኀጢአትን ስርየት በመስበክ ያሸበረቀ አይደለም። እኛ ግን በሞተልን ኢየሱስ በየትኛውም ትምህርቱና ሕይወቱ አናፍርም! ከሾላኮቹ
ይልቅም ኢየሱስ ማርኮናልና እንገዛለታለን! አሜን።
ይቀጥላል …
Kale hiwot yasemaln
ReplyDelete