Sunday, 24 March 2019

መጻጉዕ - ፈዋሹ እግዚአብሔር

Please read in PDF
“እኔ ፈዋሽህ እግዚአብሔር ነኝና” (ዘጸ. 15፥26)
   እስራኤል ከግብጽ ምድር ሲወጡ እግዚአብሔር የኤርትራን ባሕር በጸናች እጁ በተዘረጋች ክንዱ፤ በተአምራት አሻግሮአቸዋል፤ ባሕሩን ከተሻገሩ በኋላ ሙሴ ሕዝቡን ይዞ ለሦስት ቀናት የተጓዘው ወደ ሱርም ምድረ በዳ ነው፤ በዚያ ምድረ በዳ ላይ ሕዝቡ ውኃ ማግኘት አልቻሉም፤ ቀጥለው ወደ ማራ ቢመጡም የማራ ውኃ እጅግ መራራ ነበርና መጠጣት አልቻሉም፤ ከዚህ የተነሣ ታላቁን ተአምራት፣ ድንቁን ነገር በኤርትራ ባሕር ዳርቻ ላይ የተመለከቱት እስራኤል፣ ባዳናቸውና በታደጋቸው አምላክ መታመንን ትተው፣ “ሕዝቡም፦ ምን እንጠጣለን? ብለው በሙሴ ላይ አንጐራጐሩ” (ዘጸ. 15፥24)። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ለመነ፣ ያህዌ ኤሎሂም እንዳዘዘውም አደረገ፤  ውኃውም ጣፈጠ።


   እግዚአብሔር ለሦስት ቀናት ያህል ውኃ በሌለበት ምድረ በዳ ሕዝቡን የመራቸው ሊፈትናቸው ነበር፤ ይህንም ውኃውን ካጣፈጠ በኋላ ምክንያቱን ሲናገር እንዲህ ይላል፤በዚያም ሥርዓትንና ፍርድን አደረገላቸው፥ በዚያም ፈተናቸው፤ እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ብቻ ያይደለ በሌላ ስፍራም እስራኤልን ፈትኗቸዋል፤ በመሪባ (ዘጸ. 171-7) በተቤራ (ዘኍል. 113 1326-33) በሌሎችም ቦታዎች ፈትኗቸዋል፤ ነገር ግንትሑት ሊያደርጋቸው በልባቸውም ያለውን ትእዛዙን ይጠብቁ ወይም አይጠብቁ እንደ ሆነ ያውቅ ዘንድ ፈተናቸው” (ዘዳግ. 82)
   ሰዎችን በክፉ የሚፈትን ሰይጣን ብቻ ነው፤ ለዚህም ነው ስሙ “ፈታኝ” ተብሎ የተጠራው (ማቴ. 4፥3፤ 1ተሰ. 3፥5፤ ራእ. 12፥9)፤ ዲያብሎስ ለመጣል (ራእ. 12፥10)፣ ለመክሰስ፣ ለማራቆት (ዘካ. 3፥1)፣ ስም ለማጥፋት (ኢዮ. 1፥9-11)፣ ለመለያየትና በታላቅ መንፈሳዊ ውድቀት ለማዝቀጥ (ሉቃ. 22፥31) እጅግ ተግቶ ይሠራል። እግዚአብሔር በክፉ ስለማይፈተን ማንንም በክፉ አይፈትንም፤ (ያዕ. 1፥13)። እስራኤል ያንን እጅግ ግሩምና አስደናቂ ተአምራት አይተው ፈጽመው በእግዚአብሔር አልታመኑም፤ እንደ ቃሉም አልተገኙም፤ ይልቁን አብዝተው ባለመታመን አጉረመረሙ። እግዚአብሔር በብዙ ሞገስ (ዘጸ. 12፥36)፣ በግልጥ ምሪት (ዘጸ. 13፥21-22) በብርቱ ማዳን (ዘጸ. 14፥14)፣ በግሩም ትድግና (ዘጸ. 14፥20) … ቢያስወጣቸውም ነገር ግን “የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቀው አልሰሙም፥ በፊቱም የሚበጀውን አላደረጉም፥ ትእዛዙንም አላደመጡም፥ ሥርዓቱንም ሁሉ አልጠበቁም”።
   በእግዚአብሔር አለመታመን፣ ቃሉን አጥብቆ አለመስማት፣ በፊቱም የሚበጀውን ነገር አለማድረግ፣ ትእዛዙን አለማድመጥና ሥርዓቱንም ሁሉ አለመጠበቅ ብድራቱ እጅግ አስጨናቂ ነው። ያህዌ ኤሎሂም እስራኤልን የታደገው፣ እርሱን ባልታዘዙት ግብጻውያን ላይ ብዙ መቅሰፍትና በሽታን አምጥቶባቸው ነው። እግዚአብሔር የታመኑትን ልጆቹን፣ በብዙ ዋይታና ሰቆቃ ውስጥ የነበሩትን ሕዝቡን የታደገውና ነጻ ያወጣው እንዲሰሙትና በፊቱ በቅንነት እንዲመላለሱ፣ ትእዛዙን እንዲያደምጡ፣ ሥርዓቱንም ሁሉ እንዲጠብቁ እንጂ እንዲ ፊጋ በሬ መረን አልባ እንዲሆኑ ወይም እንደ መቃኞ በሬ ከሚነዳቸው ሁሉ ጋር እንዲነዱ አይደለም።  

  በሌላ በኩል፣ግዚብሔር በግብፃውያን ላይየመጡባቸው” “በሽታዎች” እስራኤልም ካልታዘዙትና ካመፁበት፣ ግብጻውያንን ያገኘው ያው ሕማምና ደዌ እስራኤልንም እንደሚያገኝ ተናግሯል፤ “የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ሁሉ ባትጠብቅ ባታደርግም፥ እነዚህ መርገሞች ሁሉ ይመጡብሃል ያገኙህማል። … እግዚአብሔር ፈውስ በሌለው በግብፅ ቍስል በእባጭም በቋቁቻም በችፌም ይመታሃል … ” (ዘዳ. 28፥15፤ 27) እንዲል። ድውይነት፣ መጻጉእነት፣ በሽተኛነት፣ አለመፈወስ … እስራኤልን ሊያገኛት የሚችለው በሕጉ ካመጸችና በሥርዓቱ ካልሄደች ነው። ብትጠብቅና በመንገዱ ብትሄድ ግን እስራኤል “በግብፃውያን ላይ ያመጣሁትን በሽታ አላደርስብህም” እንዲል፣ አንዳች ነገር አይደርስባትም፤ አያገኛትምም። ምክንያቱም እግዚአብሔር እርሱ ፈዋሽ ነውና!!!
  ያህዌ ራፋ! እግዚአብሔር ፈዋሽ! እግዚአብሔር ከማናቸውም በሽታ ገላጋይ! እግዚአብሔር ከየትኛውም ደዌ አሳራፊ! እግዚአብሔር ከኹሉም ሕማም ፈዋሽ ነው!!! እስራኤልን በሽታዎች እንደሚያገኟት የተነገረው በኃጢአቷ ምክንያት ነው፤ ልክ ጳውሎስንና ኢዮብን እንዳገኘው፣ በሽታ ከኀጢአት ውጭ በኾነ መንገድም ሊመጣ ይችላል፤ እግዚአብሔር ግን እስራኤልን እየተናገረ ያለው እንደ ኢዮብና እንደ ጳውሎስ ላለው በሽታ አይደለም፤ በኃጢአት ምክንያት ስለሚያገኛት በሽታ እንጂ። እግዚአብሔር ከማናቸውም በሽታ “ይፈውሳል”፤ ኀጢአትን ግን ሳይቀጣ አይተውም። አለመታዘዝን ሳይገስጽ አያልፍም።
  መሲሑ ኢየሱስ የመንግሥት ወንጌልን ይሰብክ በነበረበት ወራቱ ብዙና ልዩ ልዩ መጻጉአንን ፈውሷል፤ (ማቴ. 4፥24፤ 9፥35) “እኔ ጤናህን እመልስልሃለሁ ቍስልህንም እፈውሳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር” (ኤር. 30፥17) ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ጌታ ኢየሱስ እንዲሁ የብዙዎችን ጤና መልሷል፤ (ሉቃ. 7፥10፤ ሐዋ. 3፥16)፤ ለየትኛውም በኀጢአት ለሚመጣ በሽታ መፍትሔና ፈውስ፣ ጤናና ሰላም፣ ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ ነው፤ “ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤” (ሉቃ. 5፥31) እንዲል፣ ዛሬ ለታመምንበት ኹለንተናዊ [መንፈሳዊ፣ አገራዊ፣ ቤተሰባዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ግላዊ …] በሽታችን፣ ደዌያችን፣ መጻጉእነታችን… መፍትሔው ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ለበሽተኞች የመጣው ውድና መድኃኒቱ ጌታ ብቻ ነው።
    እስራኤል ለሕጉና ለሥርዓቱ ብትገዛ ምንም በሽታና መቅሰፍት እንደማያገኛነት፤ እንደማይደርስባትም ቃል የገባላት ጌታ ዛሬም አልተለወጠም፤ ያው ነው፤ ፈዋሹ ጌታ ዛሬም ይሠራል፤ ስሙ ዛሬም ድንቅና አዳኝ፣ ሕይወትን የሚለውጥ፣ የኀጢአትን ቁስልና ጠባሳ የሚሽር፣ የበደልን መግልና እዥ የሚያደርቅ፣ የዓመታትን የደም ጅረት ቀጥ የሚያደርግ ድንቅና መካር ስም ነው! እርሱ እግዚአብሔር ፈዋሻችን ነው! መዳኛችን ነው! አሳራፊያችን ነው! ብንበድለው እንኳ ስሙን ጠርተን ደጅ እንጠናዋለን፤ በስሙ እንማጸናለን እንጂ ሌሎችን አንታመንም! ያህዌ ራፋ! እግዚአብሔር ፈዋሽ!!! ፈዋሹን ጌታ ስለምድራችን፣ ስለመንፈሳዊ ደዌያችን፣ ስለተጋለጥንበት ድርቃችን፣ ስለፖለቲካው መርከስና ስለመሪዎች አለመታመን፣ ስለፍትህ መጥፋት፣ ስለሰቆቃና እንባ ኹሉ … ወደ ፈዋሹ ኢየሱስ እንጩኽ፤ ከእርሱ በቀር ሐኪም፣ ከእርሱ በቀር መድኃኒት፣ ከእርሱም በቀር ፈዋሽ የለንም፤ ለዘለዓለሙ፤ አሜን።

1 comment: