Please read in PDF
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ
ዘይት ተራራ ተቀምጦ ሳለ፣ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው መጥተው የነገረ ዳግም ምጽአቱን ምልክቶች ጠይቀውታል፡፡ ጌታ ኢየሱስና ደብረ
ዘይት እጅግ “የተሳሰሩ” ናቸው፤ “እንደ ልማዱ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ” (ሉቃ. 22፥39) በተደጋጋሚ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ደብረ
ዘይት ተራራ ለጸሎትና በዚያውም ለማደር ይሄድ ነበር፤ (ዮሐ. 8፥1-2)፡፡ በዚያ አድሮ ማለዳ ማለዳ ከደብረ ዘይት ተነሥቶ አገልግሎትን
ይጀምራል፡፡ “ድኃው” ኢየሱስ፣ ቤት ያልነበረው ኢየሱስ (ሉቃ. 9፥58) የጸሎት ስፍራውንና ማደሪያውን ያደረገው በደብረ ዘይት
ነበር፡፡
በዚያም ብቻቸውን ያገኛቸው ደቀ መዛሙርቱን ነበር፤ ጌታ ኢየሱስ አርብ ሊሰቀል፣
ሐሙስ ማታ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የተገናኘው በዚሁ በደብረ ዘይት ነበር፤ አኹንም የዳግመኛ መምጣቱን ነገር ሊነግራቸው ለብቻቸው ደቀመዛሙርቱ
የተጠጉት በዚሁ በደብረ ዘይት ተራራ ነበር፤ ደብረ ዘይት በብዙዎች ትኩረት የተነፈገው ስፍራ ቢኾንም፣ ኢየሱስ ግን በዚህ ስፍራ
ደቀ መዛሙርቱ ዘወትር ሊያስታውሱ የሚችሉትን ነገር እየነገራቸው እያሳያቸውም መኾኑን እንመለከታለን፡፡
ደቀ መዛሙርቱ ስለመቅደሱ ከተናገረው ነገር ተነስተው እጅግ በመቆጨት፣ የኹለተኛ
መምጣቱን ምልክት ተጠግተው “ንገረን” በማለት ጠየቁት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ በዚህ ክፍል የተናገራቸው “የደብረ ዘይት ንግግሮች” ተብለው
ይታወቃሉ፡፡ የደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ ላይ በመንተራስ የተናገረው ንግግር ጥያቄውን የሚያብራራ አይደለም፡፡ ጥያቄው “መቼ ይኾናል?
እና “የመምጣትህ ምልክት ምንድር ነው?” የሚሉ ኹለት ታላላቅ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ጥያቄዎቹ ኅሊናን ወጥረው የሚይዙና መልሱን እጅግ
አጓጊ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ዛሬም ድረስ የእነዚህ ጥያቄዎች መልሶች አጓጊ ብቻ ሳይኾኑ እጅግ ብዙ ሐሰተኞችን ለማስነሣት፣ የተለያዩ
ቤተ እምነቶችን ለመመሥረት ምክንያት የኾኑ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
የተጠየቀው መሲሑ ኢየሱስ፣ መልሱም ያለው ከዚያው ከተጠየቀው ጌታ ኾኖ ሳለ ብዙዎች ግን ጌታችን ኢየሱስ
የተጠየቀውን ጥያቄ ራሳቸው ቤተ እምነት በመመሥረት፣ የቤተ ክርስቲያን ቀኖና በመቀነን፣ ዶግማ በመደንገግ፣ አንቀጸ ሃይማኖት በማርቀቅ
…ሲኳትኑና መጽሐፉ ያልተናገረውን አስጨንቀው በማናገር ጥያቄውን ለመመለስ ሲጥሩ እንመለከታለን፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ጥያቄውን የመለሰው ኹለቱን ጥያቄዎች ነጣጥሎ በማብራራት
አይደለም፤ ይልቁን በአንድነት አዛምዶ እንጂ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ የመምጣቱን ጊዜ እቅጩን ወይም ቁርጥ ያለውን እንዲናገር ደቀ መዛሙርቱ
የፈለጉ ይመስላል፤ ጌታችን ኢየሱስ ግን ይህን ለማድረግ አልወደደም፡፡ ይልቁን አመጣ በብዙ ምልክቶች የታጀበ መኾኑን፣ ምልክቶቹም
በምጥ ተምሳሌትነት የተነገሩና እጅግ አስጨናቂ፣ አስደንጋጭና ከባድ መኾናቸውን በመናገር ጭምር ነው፤ (ማቴ. 24፥6፤ 8)፡፡
የመከራውና የማስደንገጡ ታላቅነት፣ “ሥጋ የለበሰ ኹሉ ላይድን እስከማይችልበት
ደረጃ” እጅግ አስጨናቂና አስፈሪ መኾኑን የሚያመለክት ነው፤ (ማቴ. 24፥22)፡፡ እጅግ አስፈሪ፣ አስደንጋጭ፣ በብዙ ክስተትና
ድርጊቶች የታጀበ፣ ግርማዊ መኾኑ ክርስቶስ እነርሱን እየተናገረ ባለበት ኹኔታ ሳይኾን እጅግ ታላቅና ክርማን በለበሰ መንገድ የሚመጣ
መኾኑን አመልካች ነው፡፡
ደግሞም ይህ ኹሉ ሲኾንም ሉዓላዊ በኾነ አምላካዊ ማንነቱ ዓለምን የሚመራ፣
የሚቈጣጠር፣ የሚመራና ከእርሱ አስተዳደር ውጭ አለመኾንዋን አመልካችም ነው፡፡ “ይህ ኹሉ እየኾነ እግዚአብሔር ለምን ዝም አለ?፣
ለምን ዘገየ? መሲሑ የሚመጣው መች ነው?፣ ይህ ኹሉ ሲኾን አይገደውምን? …” የሚሉና ሌሎች ግትልትል ጥያቄዎችን ልናነሳ እንችላለን፡፡
ደግሞም ጥያቄው አግባብና ትክክል ይመስላል፤ ደቀ መዛሙርቱም ቤተ መቅደሱ የሚፈርስ ከኾነ የዓለም ፍጻሜ ይኾናል፤ ስለዚህ የመቅደሱ
መፍረስና ያንተ ዳግመኛ መምጣት መች ይኾናል?
በማለት ኢየሱስን ጠየቁት፡፡
ጌታ
ኢየሱስ ግን ምላሹ ልከኛና ዘመን ዘለቅ[ዘላለማዊ] ነበር፤ ምላሹን ክስተታዊና ድርጊታዊ ክንውኖች ላይ ብቻ አያተኵርም፤ ይልቁን
በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የምናስተውላቸውንም እውነታዎችን ያስቀምጥልናል፡፡ የአሳቾች መብዛት፣ የሐሰተኛ ክርስቶስና የሐሰተኛ ነቢያት
መነሣት፣ ከዓመጻ የተነሣ የፍቅር መቀዝቀዝ፣ የወንጌል በመላ ዓለም መሰበክና ሌሎችም የመንፈስ ቅዱስ አብርሆት ከሌለን በቀር፣ ምልክቶቹን
ብቻ በማየት [ቸነፈርን፣ ራብን፣ የምድር መናወጥን፣
የፖለቲካውን ውጥረት] የመምጣቱ ነገር እጅግ መቅረቡን አናስተውልም፡፡
ለዚህም
ነው ከዳግመኛ መምጣቱ ጋር በተያያዘ የስህተት መምህራን “በእናውቅላችኋለን አስባብ”፣ የጌታችን ኢየሱስን መምጣት አንዳንዴ እጅግ
በማቅረብ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ እጅግ በማራቅ ለብዙ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የኾኑት፡፡ አንድ እውነት እጅግ ማስተዋል አለብን፤
የኢየሱስ መምጫው አይታወቅም፤ ነገር ግን ፈጽሞ አይዘገይም፤ የሚመጣበት ቀኑም፣ ወሩም፣ ዓመተ ምሕረቱም፣ ክፍለ ዘመኑም አይታወቅም፤
ነገር አይቀርም፤ አይቀርም ብቻ አይደለም፣ በቶሎ ይመጣል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስን ዳግመኛ መምጣት፣ ዘመኑ ቀርቦአል፣ ቶሎ ይኾን
ዘንድ አለው፣ ይቸኩላል … በማለት ይገልጠዋል፤ ይህም አይቀሬነቱንና በፍጥነት የሚኾን መኾኑን ያመለክታል፡፡
ለእውነተኛ
አማኝ የሚመጣበትን ጊዜ ከማወቅ ይልቅ፣ እርሱ ስለመዘጋጀቱ አጽንቶ ይጨነቃል፤ ጌታው ሳይዘጋጅ ጌታው ድንገት እንዳይመጣበት ራሱን
በማዘጋጀት ያተጋል እንጂ “ዛሬ ይኾን ነገ የሚመጣው?” እያለ ራሱን በከንቱ አያስጨንቅም፤ የእውነተኛ አማኝ ናፍቆቱ ወደ ጌታ መሄድ
ነው፤ ስለዚህም መንገደኛ ደግሞ ዘወትር ስንቁን የሚያዘጋጅና ያዘጋጀም ነው፤ እንኪያስ “ቀኑ መች ነው? ቀርቦስ ይኾን? … አኹንስ
የቀረ ይመስላል … ይመጣል ከተባለ ራሱ ይኸው ክፍላተ ዘመናት ተቈጠሩ” እያሉ በከንቱ ከመጨነቅ፣ እጅግ አለሌ ኾኖ ከመዘናጋትም
ንቁና ትጉ መዘጋጀት ከእውነተኛ አማኝ የሚጠበቅ መንፈሳዊና ክርስቲያናዊ ድርሻ ነው፡፡ እንኪያስ ስንቶቻችን ተዘጋጅተን ይኾን? ክርስቶስ
ቢመጣ አብረን ለመሄድ የተዘጋጀን ነንን?
No comments:
Post a Comment