Sunday, 16 September 2018

ማኅበራዊ ድረ ገጾችን ለወንጌል አገልግሎት የመጠቀም አዎንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖዎች

  “ዘመናችን ከሸማኔ መወርወርያ ይልቅ በሚቸኩልበት” (ኢዮብ 7፥6) በዚህ ወራት ነገሮች፣ ክስተቶች፣ ሁኔታዎች … ካሰብነው በተቃራኒው ወይም ካሰብነው በላይ ወደሆነ ጫፍ መፍሰሳቸው አይቀሬ ጉዳይ ነው። ለዚህ ደግሞ “አለምን ወደ አንድ መንደርነት እያመጧት” ያሉት የማኅበራዊ ድረ ገጻት ማለትም የኢንተርኔት፣ የሞባይል፣ የሳተላይት ቴሌቪዥን ግንኙነቶችና ሌሎችም ማኅበራዊ ድረ ገጻት በጎም ይሁን አሉታዊ ተጽዕኖዎች መኖሩ ክርክር የሚነሳበት ጉዳይ አይደለም።
    ቤተ ክርስቲያን “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴ. 28፥19) የሚለውን ሐዋርያዊ ታላቁ ተልእኮዋን መጠበቅና መፈጸም የሚቻላት፣ የሚድኑ ነፍሳትን የምታገኝባቸውን እድሎች አሟጣ ስትጠቀም ነው። ለምሳሌ፦ ፌስ ቡክ ወደ አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊየን ገደማ አባላት ያሉት ሲሆን፣ ይህንን እውነታ ወደ እውነተኛው ዓለም ብናመጣው በ2016 ቆጠራ የተደረገለትን 1.2 ቢሊየን ገደማ የሚጠጋውን የአፍሪካን ሕዝብ ሽፋን ያካልላል ማለት ነው። ይህም የአድማሱን ሽፋን ብቻ ሳይሆን፣ በውስጡ የሚያስተላልፈው መልዕክት በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት “መደገፉ” አልያ ፍጹም መቃረኑ አይቀሬ ነው።

   ከዚህ አንጻር ቤተ ክርስቲያን በእነዚህ ማህበራዊ ድረ ገጻት “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል” (ማቴ. 2414) ተብሎ እንደ ተነገረ፣ ወንጌልንለዓለሙ ሁሉለማሰራጨት፣ ብዙ ክርስቲያኖች ቃለ እግዚአብሔርን በቤታቸው ተቀምጠው ለመማር፣ በተለያዩ አገራት ካሉ እህት አብያተ ክርስቲያናት አማኞች ጋር ለማምለክና የእምነታቸውን ጽናትና ብርታት ለመመልከት ማስቻሉ ይበል የሚያሰኝ ቀዳሚ ጥቅሙ ነው። በተጨማሪም ከማኅበራዊ ግልጋሎት አንጻር፣ ለብዙ ዓመታት የተለያዩትን ቤተሰቦች፣ ዘመዶች፣ ወገኖች የመገናኘት ምክንያት ሆነው፤ ለንግዱ ማኅበረሰብ ሥራዎቻቸውን በቀላሉ እንዲያስተዋውቁና እንዲያሻሽጡ፤ ለተጠቃሚውም ዝቅተኛ የገበያ ዋጋ፣ በጥራትና በዋጋ የተሻለውን እንዲመርጡ ማስቻሉ፣ በማኅበረሰቡና በአገራት መካከል ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ግንኙነትን ለመፍጠር፤ እጅግ ውል አልባ የሌላቸውን ሥራዎችንና ቀመሮችን በማሳጠርና በማቀላጠፍ ግለሰቦች ደንበኞቻቸውን በማስደሰት፣ መንግሥታት ደግሞ ለዜጎቻቸው ኋላ ቀር አሠራሮችንና ዘዴዎችን በማስወገድ መልካም አስተዳደርን ለማስፋፋት፣ የአንዱን ማኅበረሰብ መልካም እሴት ለሌላው ለማስተላለፍ፣ ለብዙዎች የሥራ እድል ለመፍጠር፣ ግብር ለመክፈልና የባንክ ሂሳብን ለመከታተልና ለማወቅ፣ ስለተለያዩ ነገሮች የተለጠፉ “አስፈላጊ” የሆኑ መረጃዎችን “ለመጠቀ”፣ በተለይም ደግሞ በሠለጠኑት አለማት ባሉ ማኅበረሰቦች የበረራ ቀጠሮ ለማድረግ፣ የሕክምና ቀጠሮ ለማስያዝ፣ መኪና የሚያሽከረክሩ ከሆነም የመኪና ፍሰት እንቅስቃሴው አናሳ የሆነበትን መንገድ ለመምረጥና ለሌሎችም ሥራዎች ጉልበትንና ጊዜን ቆጥቦ ወዳቀዱበት ፍጻሜ መድረስ አስችለዋል እያልን ሌሎች ብዙ ነገሮችን መጥቀስ እንችላለን።
    ነገር ግን የሐሰት ወንድሞች መከማቻ መሆናቸው ደግሞ የመጀመርያና ዋና አሉታዊ ገጽታቸው ነው። የጠለቀ ጥናት የሚያስፈልገው ቢሆንም በሁለት መልኩ ብናየው የተሻለ መስሎ ይታየኛል፤ አንደኛው ከማኅበራዊና ከመንፈሳዊ ተጽዕኖ አንጻር። ማኅበራዊ ድኅረ ገጻት የብዙዎችን አገራትና ባህሎቻቸው ላይ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ወረራን ከማስከተላቸውም ባሻገር ማንነትን እስከማስለቀቅ ወይም እስከ ማደብዘዝ ደርሰዋል። ከመንፈሳዊ ይዘት አንጻር ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃወሙ፣ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ የሚንቁ፣ የተቀደስንበትን የኪዳኑን ደም ከፍጡር ሥራ ጋር የሚያስተካክሉ፣ የጸጋውን መንፈስ የሚያክፋፉ፣ የትንሣኤ ሙታንንና ዳግመኛ መምጣቱን እንደ ተረት የሚቈጥሩ፣ ትምህርተ ሥላሴን የሚሳደቡከፊት ይልቅ በዝተው በየማኅበራዊ ድረ ገጹ መረባቸውን ጥለውያለ ድካም” ነፍሳትን ሲያጠምዱ እናያለን።
     በሌላ መልኩ ደግሞ ኃጢአትን ዓለማቀፋዊ(ኩላዊ) ማድረጉ እጅግ አስፈሪነቱን ያሳያል። ዓለም አንድ መንደር ሆናለችበሚባለው በሉላዊነት ዓለም፣ አንዱና አስከፊው ነገር የኃጢአትና የዓለማዊነት ፈጣን ስርጭትና በአንድ ሥፍራ የተለመደንና የተሠራን ነውርና ኃጢአት፣ ሽርፍራፊ በሆኑ ደቂቃዎች ፍጥነት በአንድ ጊዜ በእኒህ ማኅበራዊ ድረ ገጻት በሁሉ ዘንድመድረሱ ነው። በዚህም አንድን ኃጢአትእንደኖህ ዘመንበዓለሙ ሁሉ እንዲሠራ ማድረጉ ነገሩን ይበልጥ ያከፋዋል። አስተውሉ! የኖህ ዘመን ሰዎች ሙሉ ኃይላቸውን በተመሳሳይነት ለኃጢአት አውለውታል። ጌታ ኢየሱስም ይህን እውነት እጅግ አጽንቶ ተናግሯል፤ (ሉቃ. 1726-27) በእኛ ዘመን መፈጸሙን የሚያሳይ ብዙ ነገር አለ። በኃጢአት አንድ እንደመሆንና እንደመስማማት እጅግ መራራ ነገር ይኖር ይሆንን? ለምሳሌ፦ በጎግል ድረ ገጽ ላይ ብቻ ከ3.5 ሚሊየን በላይ የዝሙት ቪዲዮዎችን የሚለቁ ቻናሎች እንዳሉና በየቀኑም በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ጣቢያዎች እንደሚከፈቱ ይናገራል። በዚህም ደግሞ እጅግ ተጠቂዎቹ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ጨቅላ ወጣቶች መሆናቸውንም ጨምሮ ይናገራል። ከዚህ ጋር በተያያዘ በጥንቆላ አሠራር መጠመድ(Horoscope), ከማናውቃቸው ሰዎች ጋር በጋብቻ መተጫጨት፣ ከአሸባሪዎች ጋር መሻረክ፣ ከግብረ ሰዶማውን ጎራ መሰለፍ፣ ዕፅ አዘዋዋሪዎችና ሌሎችንም ጥፋቶች ወዳልታወቁት ዓለማት በአጭር ቅጽበታት ሲተላለፉ እናያለን።
    ከዚህም ባሻገር የሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ የቤተሰብ ጸሎቶች፣ የሠርክ መርሐ ግብሮች … ሲብስ ደግሞ የቅዳሴና የኪዳን ጸሎቶችን በአገር ቤት፣ በአሜሪካና በአውሮፓ እንደቃና ባሉ ተከታታይ የፊልም መርሐ ግብሮችን በሚለቁ የሳተላይት ቻናሎች፣ የእግር ኳስ ዲሽ ቤቶች፣ ዓይን ያወጡ የሐሰት ትምህርቶች … በማየትና በመከታተል በከባድ መንፈሳዊ ዝለቶች መመታታቸውን የዓይን እማኞች ነን። ከዚህም ከፍቶ አገልጋዮች ጭምር ለጉባኤ ተጋብዘው ስለእግር ኳስ ጨዋታ የተጠሩበትን ዘንግተው ሰዓት ሲያሳልፉና የእግዚአብሔርን ጉባኤ ሲበድሉም እናያለን። ቤተ ክርስቲያን በዚህ ረገድ ከነገሩ ስፋትና ከጊዜው ጥፋት አንጻር በብዙ ወደ ኋላ መቅረቷን መታዘብ ይቻላል። የድረ ገጻት ሩጫ የሸማኔ መወርወርያ ያህል ፈጣን ነው፤ እኛ ደግሞ “ከዚህ ጠማማ ትውልድ ዳኑ” (ሐዋ. 2፥40) የሚለውን ጽኑ ምክር ለመናገርና የመዳኑንና የጸጋውን ወንጌል ለመስበክ ጉዟችን የማዝገም ያህል ነው።
          ስለዚህ በእኒህ ማኅበራዊ ድረ ገጻት ላይ የሚጠቅመንንና መንፈሳዊ ነገሮቻችንን ብቻ ልናስተላልፍበት፤             እንዲሁም የምናየውን፣ የምናደምጠውን፣ የምናነበውን ... ከእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል ጋር የሚያቃርነን ነገር እንዳይሆን በብርቱ ልንጠነቀቅ ይገባናል። የተጠራነው በቅድስና ሕይወት እንድንኖር ነው፤ እርሱ የጠራንም ቅዱስ ነውና(1ጴጥ. 114-16)አባታችን ሆይ ብለን እግዚአብሔርን በጸሎት ከጠራን፥ እንደእግዚአብሔር ልጆች ለፈቃዱ ብቻ ልንታዘዝ ይገባል። እርሱ ፈቃዱ ቅድስና ነው። ቅድስና ከኃጢአት ከርኩሰት ተለይቶ ለእግዚአብሔር ብቻ መሆንን የሚፈልግ ዓቢይ ጉዳይ ነው። ሁላችን በየትኛውም ጉዟችንቅድስና ለእግዚአብሔርየሚል አዲስ ኪዳን በክርስቶስ ኢየሱስ ገብተናል፥ ለዚህ ኪዳን ታማኞች በመሆን ሁሉን እንደቃሉ ልንመረምር ይገባናል። በየሚድያው የሚቀርቡትን የዝሙት ምስልና ድምጸቶችን አጥብቀን ልንሸሻቸው፤ ልንርቃቸው ይገባናል። የሚያዳልጡ ሥፍራዎች ጐበዛዝትን ጭምር ይጥላሉና በራሳችን ከመመካት እጅግ መሸሽ ይገባናል። ይህን በማድረጋችንም በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአትን ባለማድረግ ለአምላካችን ክብር እንቀናለን። ቆሞ ከሚጋፈጥ ብርታት ቀሚሱን ጥሎ የሚሸሽ እርሱ መልካምን አድርጓል።
    እንዲሁም፣  ከማናውቃቸው፤ እንዲህ ያለውን የክፋት ሥራ በመሥራት ከተጠመዱት ሰዎች ጋር መጣመድና መወዳጀት አይገባንም። አሸባሪዎች፣ ግብረ ሰዶማውያን፣ እንግዳ ትምህርት የሚያስተምሩ የሐሰት መምህራን ... በብዛት አባላትን የሚመለምሉት በእኒህ ማኅበራዊ ድኅረ ገጻት ነው። ስለዚህ ዘመኑን እያየን የመዋጀት ሥራ እንድንሠራ፥ “... እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ኾነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትኹኑ” (ኤፌ. 515-17ተብለናልና እግዚአብሔርን በመፍራት በትሁት ድፍረት ዘመኑን በሚዋጅና በሚነቅፍ ሕይወት ልንመላለስ ይገባናል። “ቅጥር እንደሌላት እንደ ፈረሰች ከተማ፥ መንፈሱን የማይከለክል ሰው እንዲሁ ነው” (ምሳ. 25፥28) እንዲል ለመንፈሳችን ቃለ እግዚአብሔር ቅጥር ልንገነባለት ይገባል። ለሕይወቱ ምንም ዕቅድ እንደሌለው እንደሰነፍ ሰው ልንኖር አይገባንምና።
    አባቶች ሊቃውንት ዘንድ ያለው ጥበብና የበዛው የሕይወት ልምድ፣ ከወጣቱ ፍጥነትና የቴክኖሎጂ ዕውቀት ጋር እንዲዋሃድ በአባቶችና በወጣቶች፣ በሊቃውንትና በሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች መካከል ልበ ሰፊነት ያወዛው ምክክር ሊደረግ ይገባል። ምዕመናንና ምዕመናትም፤ ወጣቶችና ለጋ ጨቅላዎችን የመከታተል፣ ጥቅሙንና ጉዳቱን ቀድሞ ግንዛቤ ማስጨበጥና ˝በሰው እጅ ሥራ˝ እንዳይጠፉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነትን ባለመሰልቸት ሊተጉበት ይገባቸዋል።
    ክፉ በሆነው ዓለም ለቅዱስ እግዚአብሔር ልንኖርበት የምንችልበትን አጋጣሚ ሳንጠቀምበት እንዳያመልጠን ድኅረ ገጻትን በእግዚአብሔር ቃል ልንመላቸው ይገባናል። የሐዋርያት ሥራን መጽሐፍ ስናጠና ቅዱሳን ሐዋርያት በተለይም ቅዱስ ጳውሎስ ወደ አሕዛብ ከተሞች ሄዶ ማስተማር የቻለው፣ በዚያ ዘመን የነበረው የሮማ መንግሥት በሠራው የከተሞች መንገድ ላይ እጅግ በመፍጠን፤ በዚያ ዘመን የተገኘውን ዕድል አሟጥጦ በመጠቀም ነው። አስተውሉእኒያ ጐዳናዎች ወንጌል፤ ወንጌል የሸተቱትና እልፍ አእላፍ ሰማዕታት በዚያ ዘመን የተነሡት የጌታ ባርያዎች ሞኝ ሳይሆኑ የተገኘውን ዕድል ሁሉ ለእግዚአብሔር ቃል ክብር ስላዋሉት ነው። እኛም እንዲሁ እግዚአብሔር በዘመናችን ለወንጌሉ እውነት ነፍሱን፣ ትዳሩን፣ ኑሮውን፣ ሥራውን የሰጠ ትውልድ እንዲያስነሣልን ድረ ገጻትን በእግዚአብሔር ቃል እውነት ልንመላቸው ይገባናል። በዝሙትና እርቃን ምስሎችን በማየት የተጠመዱና ለእኛም የሚልኩ ባልንጀሮች ያሉን ወገኖች ደግሞ አስቀድመን ራርተንላቸው ልንመክራቸው፤ ልንጸልይላቸው፤ ልንገስጻቸውምካልተመለሱ ደግሞ ልናስመክራቸው፤ እንቢ ካሉ ግን ለነፍሳችን ወጥመድ እንዳይሆኑብን ልንሸሻቸውና ልንርቃቸው ይገባል። “ክፉ ነገር ማድረግ ለሰነፍ ሰው ጨዋታ ነው፤ እንዲሁም ጥበብ ለአስተዋይ ነው” (ምሳ. 10፥23) የሚለው ቃል ልባችንን ይግዛው፤ አሜን።
    ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን፤ (ኤፌ. 6፥23)
 (ይህ ጽሑፍ ከኹለት ዓመት በፊት ለአንድ አኅጉር አቀፍ የሰንበት ትምህርት ቤት መጽሔት ላይ የወጣ ነው።)

No comments:

Post a Comment