Thursday, 30 August 2018

ቤተ ክርስቲያንም ከደቦ ገዳዮች እንደ አንዱ ስትኾን!

   Please read in PDF

ቤተ ክርስቲያን እንኳን የተፈጸመን ያልተፈጸመን ኀጢአት ማየት የምትችልበትን ነቢያዊ ችሎታ በመንፈስ ቅዱስ ተችሯታል። ኀጢአትን ለመቃወምና ለመጠየፍ፤ አለማዊነትንም ለመካድ ጭምር በክርስቶስ ኢየሱስ የተገለጠ የእግዚአብሔር ጸጋ ለቤተ ክርስቲያን ተገልጧል፤ (ቲቶ 2፥11-13)። ቤተ ክርስቲያን ይህን የተገለጠ ጸጋ በእውነት በመቀበልና በማመንም ጭምር፣ የሰማይ መንግሥት እንደ ራሴነቷን ማስቀጠል ይኖርባታል። ቤተ ክርስቲያን ይህን ዘላለማዊ አደራ ይዛ ለመሄድ ግን የሞተላትንና አንድ ቤዛዋን ክርስቶስ ኢየሱስን ትኵር ብላ መመልከት የዘወትር ተግባርዋ ሊኾን ይገባል።
  ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችንን እንደ ተሰቀለ ኾኖ ትኵር ብሎ አለማየት ለድንዛዜና ለክፋት፤ ለእውነት ለማያሳዝዝ አዚም ሳያጋልጥ አይቀርም፤ (ገላ. 3፥1)፤ አዚም የአእምሮ ችግር አይደለም፤ ራስንም የመሳት ጉዳይ አይደለም፤ ፍጹም አለማወቅና አለመረዳትም አይደለም፤ ነገር ግን መረዳት እየቻሉ አለመረዳት፣ ማስተዋል እየቻሉ ተላላ በመኾን አለማስተዋል፣ ማየት እየቻሉ መታወር፣ መጠንቀቅ እየቻሉ ፍጹም ቸለተኛ የመኾን ጉዳይ ነው። የገላትያ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊቷ ያለውን እውነት በዝንጉነትና በቸለተኝነት ባለማስተዋል በአዚም ተያዘች። እናም የተሰቀለውን ክርስቶስን ባለማየት ስንፍና ተያዘች።

   ቅዱስ ጳውሎስ፣ “አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?” ብሎ ገላትያውያንን ይሞግታል፤ ለገላትያ ቤተ ክርስቲያን አዚም ያደረጉት ምናልባት ወግ አጥባቂ የኾኑት የአይሁድ እምነት ተከታይ፣ በኋላ ግን ክርስቲያን የኾኑ አይሁዶች ሳይኾኑ አይቀሩም፤ ምክንያቱም በአደባባይ ለዓለም ኹሉ የተሰቀለው ክርስቶስ ኢየሱስ ለሰው ኹሉ እንዲታይ አይፈልጉምና፤ ክርስቶስ የተሰቀለው ለዓለሙ ከኾነ፣ መድኃኒትነቱና አስፈላጊነቱ ለዓለሙ ኹሉ ነው ማለት ነው፤ ነገር ግን ይህ ለኹሉ የኾነው ጌታ፣ ለኹሉ እንዳይታይ የሚተጉ፣ የክፋትን አዚም ተሸክመው የሚዞሩ ብዙዎች አሉ።
  ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን ሲሰቅል ኹሉ እንዲያየው ወድዶ ነው፤ በእርግጥ እግዚአብሔር አምላክ አዝዞትም ነው (ዘኊል. 21፥9)፤ ጌታም የተሰቀለው ኹሉ እንዲያየው፣ እንዲያምንበትና እንዲድንም ጭምር ነው፤ ክርስቶስን ትኵር ብሎ አለማየት ሥጋዊ ዳፋና መዘዙ ብዙ በው፤ በአጭር ቃል፣ ሰው አሮጌውን አዳም በራሱ ይሾማል፤ አሮጌው አዳም እርሱ ደግሞ ፍጥረታዊ ሰው ነው፤ እርሱም በክርስቶስ በመስቀል ላይ ካልተሰቀለ አደገኛና የጋኔን ሎሌ ነው። ኃጢአትና ርኩሰት እንጂ ሌላ ምንም አይገለጥለትም፤ እንዲህ ያለ ሰው ብዙ ጊዜ በአማኞች መካከል አማኝ መስሎ ሊቀመጥ ይችላል።
   ከሰሞኑ በቦሬዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅጥረ ግቢ የኾነው ይኸው ነው፤ ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ የተሰማችው “ጸጉረ ልውጥ” የምትል አንዲት የዋዛ ቃል፣ በቤተ ክርስቲያን ጆሮም ሽው ሳትል አልቀረችም፤ እናም በምዕራብ ጎጃም የቡሬዋ ከተማ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ ቤተ ክርስቲያን ሊያቃጥል ሲል አገኘኹት ብላ፣ በ“ቀሳውስቷ” ብይን አንድ “ጸጉረ ልውጥ” ሰው በድንጋይ ተወግሮ እንዲሞት ወሰነች፤ እናም የራሷን ልጅ በድንጋይ ወግራ ገደለች። በጅግጅጋ አሰቃቂ ግድያ በልጆቼ ተፈጸመብኝ የምትል እናት፣ በሌላ እጇ ደግሞ የራሷን ልጅ ደብድባ ትገድላለች።
   ጌታችን ኢየሱስ የታመሙት ልጆቹ ኹሉ እንዲድኑለት በአደባባይ ተሰቅሎ ይታያል፤ ከክርስቶስ ያልተማረችው “ቤተ ክርስቲያን” ግን ለክርስቶስ አልሞተችምና፣ ተስፋ ያለውንና ንስሐ ልትሰብከው፣ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ልታውጅለት የሚገባውን ክቡሩን የሰው ልጅ በአደባባይ በድንጋይ ወግራ ገደለችው። በእውኑ የማሰናከያን ድንጋይ በመንገድ ማኖር ፍርዱ የገሃነም ፍርድ አይደለምን? (ማቴ. 18፥6) የሰውን ደም የሚያፈስስ የእርሱስ ደም የሚፈስስ አይደለምን? (ዘፍ. 9፥6)።
  ሊሞት የሚገባው አሮጌው ሰው በአደባባይ ሰው ይገድላል፤ ሊኖር የሚገባው ክቡር ፍጡር ግን በአደባባይ በድንጋይ ተወግሮ ይገደላል። ቤተ ክርስቲያን በአዚም ስትያዝ እንዲህ ያለ እጅግ አሳፋሪ ነውርን ትፈጽማለች፤ ቤተ ክርስቲያን ሰውን ለማዳን እንጂ ሰውን ለመግደል ፈጽሞ አልተጠራችም፤ የተጠራችለትን ስትጥል ግን ያልተጠራችለትን ያውም የአጋንንትን ሥራ ሥራዋ አድርጋ ልትይዝ ትችላለች።
    እግዚአብሔር በምድር ላይ እጅግ የሚጠየፈው ነገር ቢኖር ሰውን የሚገድል ማናቸውንም አካል ነው፤ ለሰው እኮ እግዚአብሔር የመጨረሻ ዋጋ አንድያ ልጁን ነው የሰጠው፤ ሰውን የሚገድል ማንኛውም አካል እግዚአብሔር ለሰው የሰጠውን ዋጋ የሚያቃልል ነው። ቤተ ክርስቲያን በዓለሙ ኹሉ ፊት የሠራችው ሥራ እጅግ የሚያዋርዳትንና የሙሽርነት ልብሷን ያሳደፈና ያረከሰ ተግባር ነው። ቤተ ክርስቲያን ሰውን በአደባባይ ከገደለች ሰዎች ክርስቶስን ሳያዩ እንዲሞቱ ፈቀደች ማለት ነው፤ ይህ ደግሞ እጅግ ከባድና አስፈሪ ፍርድን ሳያመጣ አይቀርም!

" ስሙ፥ አድምጡ፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና አትታበዩ።  ሳትጨልም እግራችሁም በጨለመችው ተራራ ላይ ሳትሰናከል፥ በተስፋ የምትጠባበቁትን ብርሃን ለሞት ጥላና ለድቅድቅ ጨለማ ሳይለውጠው ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ። "
(ኤር. 13፥15-16)

ጌታ ሆይ! ለምድሪቱ ብቻ ያይደለ ለቤተ ክርስቲያንም ምሕረት አድርግላት፤ አሜን።

4 comments:

  1. amen geta yasben

    ReplyDelete
  2. Very well said

    ReplyDelete
  3. በአማራ ክልል ፖሊስ እና ፖሊስ ጣብያ የለም እንዴ? የአማራ ክልል በኦሪት ህግ እየተመራ ነው ያለው። ለ27 አመታት የአማራ ህዝብ በህገ መንግስቱ በጀት መጠየቅ እንጂ ህገ መንግስት ሳያውቅ የቀረ የቸጎዳ ህዝብ ነው። ጌታ ይማራችሁ። ሁሉም ነገር በሀይል ቢሆን ኖሮ የማራ ህዝብ ጣና ይውጠው ነበር። ያለማወቅ እዳ ማለት እንዲህ ነው!

    ReplyDelete
  4. በአማራ ክልል ፖሊስ እና ፖሊስ ጣብያ የለም እንዴ? የአማራ ክልል በኦሪት ህግ እየተመራ ነው ያለው። ለ27 አመታት የአማራ ህዝብ በህገ መንግስቱ በጀት መጠየቅ እንጂ ህገ መንግስት ሳያውቅ የቀረ የቸጎዳ ህዝብ ነው። ጌታ ይማራችሁ። ሁሉም ነገር በሀይል ቢሆን ኖሮ የማራ ህዝብ ጣና ይውጠው ነበር። ያለማወቅ እዳ ማለት እንዲህ ነው!

    ReplyDelete