Wednesday, 15 August 2018

በሥጋ የተገለጠ አምላክ


    የክርስትና ትምህርት የመገለጥ ትምህርት ነው። የመገለጡ ምንጭ መለኮት ከኾነው ከራሱ ከእግዚአብሔር እንጂ፣ በሰው ወይም ከሰው አይደለም። ይህ መገለጥም “ከጥንት ጀምሮ በብሉይ ኪዳን ታሪክ እግዚብሔር በልዩ በልዩ መንገድ ለአበውና ለነቢያት በቃልም ሆነ በድርጊት፣ በራእይም ሆነ በሕልም በተአምራዊ ሁኔታ የገለጠላቸውን ሁሉ ያካትታል፤ በተለይም በኋለኛው ዘመን በሥጋ የተገለጠውን ክርስቶስንና የማዳን ሥራውን ሁሉ ይመለከታል።”[i]

ከዋናው መገለጥ በፊት የነበረው “መገለጥ”
     ብሉይ ኪዳን ታላቁን መገለጥ ፍለጋ ብዙ የመቃተት ድምጾች፣ ሕልሞች፣ ራእዮች፣ ትንቢቶች … የተሰማበት የምጥ መጽሐፍ ነው። እኒህ ብዙ መቃተቶችና ፍለጋዎች ለረጅም ዓመታት የተደረጉ ናቸው። በእኒህ ረጅም ዘመናት መላእክት ሊያዩት የሚመኙትንና ሰዎች ሊያገኙት ያላቸውን መዳን፣ ቅዱሳን ነቢያት “…ተግተው እየፈለጉ መረመሩት፤” (1ጴጥ. 1፥10-11)፣ ታላቁ ነቢይ ሙሴ፦ “የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ነቢያት ቢሆኑ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ መንፈሱን ቢያወርድ አንተ ስለእኔ ትቀናለህን?” (ዘኊል. 11፥29) በማለት፣ ታላቁ መገለጥ ለሕዝቡ ኹሉ እንዲገለጥና እንዲያገኛቸውም አብዝቶ ተመኘ። እጅግ የሚደንቀው ነገር የዘኊልቅ መጽሐፍን ሲጽፍ እንኳ፣ እጅግ የበዛውን ትውልዶች በመቁጠር ሲደክም ትልቁ ዓላማው ሊያርፍበት ያለውን ዋናውን መሲህ ፍለጋ ነበር። እርሱን ስላላገኘም በብዙ ፍለጋ ውስጥ ማለፉን እናስተውላለን።
    አንድ አባት ይህን እውነት በመጽሐፋቸው እንዲህ ብለው ገልጠዋል፦

   “ብሉይ ኪዳን በብዙ ሃብት ያጌጠ ነገር ግን በደበዘዘ ብርሃን የሚታይ አዳራሽን ሊመስል ይችላል። ጥሩ መብራት ሲበራ ቀድሞ ያልነበረውን ነገር ለአዳራሹ ምንም አይጨምርም፤ ሆኖም አስቀድሞ በጭንቅ የታየውንና ያልተለየውንም እንኳ ቢሆን በግልጥ እንዲታይ ያደርጋል። የቅድስት ሥላሴ ምስጢር በብሉይ ኪዳን ጐልቶ ባይገለጥም፥ ከብሉይ ኪዳን አስተርእዮ በስተጀርባ አለ፤ ዐልፎ ዐልፎም እንዲያውም ለመታየት የሚቀረው ትንሽ ብቻ ነው። እንግዲህ ስለእግዚአብሔር የብሉይ ኪዳን አስተርእዮ በሚከተለውም ዘመን ሳይለወጥ እንዲሁ ይፈጸማል፤ ይሰፋል፤ ይስፋፋልም።”[ii]
     እውነት ነው! በብሉይ ኪዳን እልፍ መሥዋዕቶች ቢቀርቡም ሰዉን ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ ስላልቻሉ ሰው ዋና አዳኙን፣ ቤዛውን፣ ቅዱሱን መሲሕ አብዝቶ በመጠማት እንዲናፍቅ አደረገዉ። የሚያድናቸውን ቅዱስ አምላክ በቅርብ እንደሚያዩት፤ ደግሞም በሩቅ እንዳለ በመናፈቅ ቃል፣ አሁን አድን (መዝ. 118፥25)፤ ፍጠን እርዳን (መዝ. 22፥19፤ 38፥22፤ 44፥26፤ 70፥1፤ 79፥9)፤ መቼ ትመጣለህ? (መዝ. 101፥2)… የሚሉ ብርቱ ጩኸቶችን አሰምተዋል (ዘኊል. 24፥17፤ ኢዮብ 19፥26-27)። እኒህ የፍጹም አድነንና የእርዳን የጣዕር ድምጾች ሊሠሙ የቻሉት ከሰማይም ከምድርም የሚያድንና ወደእግዚአብሔር የሚያቀርብ አንዳች አካል መገኘት ባለመቻሉ ነው።
የብሉዩ ኪዳን መገለጥ ምሉእ ያልኾነበት ምክንያት
    የሰው ልጅ የመጀመርያውን[ወንጌል] የኪዳን ተስፋ(ዘፍ. 3፥15) ባለማስተዋል በክፋት ጸንቷል፣ እግዚአብሔር ልክ እንደርሱ እንደኾነም ጠረጠረ (መዝ. 50፥21)፣ ከእግዚአብሔር ቅዱስ ሃሳብና ፈቃድ ይልቅ፣ “በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር” (መሳ. 21፥25)፣ “ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ፤ አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ የለም፤ ሁሉ ተሳስተዋል፥ … ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል” (ሮሜ. 3፥11፤ 23)፣ … እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን (ኤፌ. 2፥3) … እንደተባለ ፍጹም ከሕግ በታች ወድቀን ተገኘን። “ይህም ሲሆን የእግዚአብሔር ጸጋ በሰው ልብ ካልሠራ በስተቀር፥ የሰው አእምሮ በኀጢአት ከመበከሉ የተነሣ አስተርእዮን ለመቀበል ስለማይፈልግ ያዛባዋል፤ ወይም ሊያፍነው ይሞክራል፤ ወይም እስከመካድም እንኳ ይደርሳል።”[iii]
    ነገር ግን ምንም እንኳ ሰው ኃጢአተኛ ቢኾንም፣ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ፣ በብሉይ ኪዳን ያገለግሉ በነበሩ ነቢያት “አድሮ” ይናገር የነበረው ክርስቶስ እንደኾነ፦ “በእነርሱም(ትንቢትን ይናገሩ በነበሩ ነቢያት) የነበረ የክርስቶስ መንፈስ፥ ስለ ክርስቶስ መከራ ከእርሱም በኋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሰከረ፥ …” (1ጴጥ. 1፥11) በማለት ሲናገር፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በራሱ አንደበት የኤማሁስ መንገደኞችን በወቀሰበት ንግግሩ፣ “ … ክርስቶስ ይህን መከራ ይቀበል ዘንድና ወደ ክብሩ ይገባ ዘንድ ይገባው የለምን? አላቸው። ከዚያም ራሱ ያናገራቸውን የቀደመውን ኪዳን ምስጢር ኹሉ ፈታላቸው። “ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጐመላቸው።” እንዲል፤ (ሉቃ. 24፥26)።
     በቀደመው ኪዳን ምንም ክርስቶስ ቢገልጥላቸውም ግን አገላለጡ ውሱን እንጂ ምሉእ አልነበረም፤ ገና ስለኃጢአት ሥርየት አልተገኘምና። ደግሞም ያ የቀደመው ኪዳን ሊሻር ያለ፣ ጥላ፣ ምሳሌ፣ … (ዕብ. 8፥5-13)፤ 9፥9፤ 18፤ ቈላ. 2፥16) ነበርና፣ በራሱ ሰውን ወደፍጹም መዳን ማድረስ አይችልም ነበር።
የመገለጥ ኹሉ ዳርቻ
    የመገለጥ ኹሉ ዳርቻና መደምደሚያው ጌታችን ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ይኸውም እርሱ በልዩ ኹኔታ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን ነሥቶ በመወለድና በመገለጡ ምክንያት ነው። “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን፤” (ዕብ. 1፥1-2) እንዲል፣ በባሕርይው የማይታየው፣ “በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን የተናገረው” እግዚአብሔር፣ “የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ” (ገላ. 4፥4) በትሥጉት ልጁ ተገለጠ። 
     በድንቅ መገለጡም ክርስቶስ ነቢይና፣ የነቢያት ኹሉ በላይ መኾኑን ገልጧል፤ ደግሞም የባሕርዩ ልጁ ስለኾነም ከእርሱ በቀር እንደእርሱ ሌላ የሚነሣ ነቢይ እንደሌለ አሳየ፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ጌታችን የመጨረሻውን አስተርእዮ ሰጠ፤ ዳርቻውም በእርሱ ተደመደመ። እናም እኛ ዛሬ አንድን ትምህርት የምንመዝንበት መመዘኛችን የጌታችን ኢየሱስን ትምህርት እያብራራ ሲመጣ እንጂ፣ ጌታችን ኢየሱስ ከገለጠልንና ካስተማረን የተለየ ማናቸውንም “መገለጥና ትምህርት” ይዞ ቢመጣ ፈጽሞ አንቀበለውም፤ በክርስቶስ ዳርቻው ተወስኗልና።  
    ወንጌላትን የጻፉት ኹለቱ ቅዱሳን ሰዎች፣ [ማቴዎስና ሉቃስ] እንደሙሴ የትውልድ ዘሮችን ሲዘረዝሩ በፍለጋ አልተንከራተቱም፤ ልክ የሚፈልጉትን ተናፋቂውን “ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስ” መሲህን ሲያገኙ፣ እርፍ ከማለታቸውም ባሻገር ከዚያ በኋላ መቁጠርን አልፈለጉም፤ (ማቴ.1፥16፤ ሉቃ. 3፥38)፤ “ … ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ” (ሉቃ. 2፥12) እንደተባለ፣ “እነሆ፥ በኤፍራታ ሰማነው፥ በዱር ውስጥም አገኘነው” (መዝ. 132፥6) የተባለው ትንቢት ተፈጽሞ አይተዋልና።
   ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን፣ “በሥጋ የተገለጠ” በማለት፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋን በመንሣት ሰው ኾኖ በሥጋ ስለተገለጠው አምላክ ይናገራል። ቃሉ በ1ጢሞ. 3፥16[iv] ላይ የተጠቀሰ ሲኾን፣ በግጥም መልክ የሰፈረና የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን መዝሙር ወይም ቅዱስ ጳውሎስ ራሱ የደረሰው ግጥም እንደ ኾነ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል። የክርስቶስ ኢየሱስ በሥጋ ሰው ኾኖ መገለጥ የትምህርትም፣ የመዝሙርም፣ የስብከትም፣ የትንቢትም፣ የራእይም፣ የሕልምም፣ የመዳንም፣ ከእግዚአብሔር ጋር የመታረቅም … ዋና ማዕከል ነው። የመጀመርያይቱም ቤተ ክርስቲያን ያደረገችወም ይኸንኑ ነው። ከአበው አንዱም እንዲህ አለ፦
   የእግዚአብሔር ቅዱስ ዓላማ ሰው ኹሉ እንዲድን ሰው ኹሉ የመንግሥቱ ወራሽ እንዲኾን የታለመ ነው። ለዚህም ኹሉ መምህር ኾኖ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመጣ የስብከቱ ጠባይ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥራ የሚከተል ራሱን ኢየሱስ ክርስቶስን ማዕከል አድርጐ የሚሄድ ይኾናል። ስለሰው ድኅነት ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ሞቷል። እንግዲያውስ የስብከቱ ይዘት የስብከቱም ጠባይ የተሰቀለውን ኢየሱስን የሚመለከት መኾን አለበት። ሰባኪው በፈቀደው ርእስ ሊናገር ይችላል። ኾኖም ዋናው ዓላማ የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት ለመናገር መኾን አለበት። ምንም የስብከት ምንጩ ቅዱስ መጽሐፍ ቢኾንም ጥቅሱም ከእርሱ ቢወጣም ሐተታውና አገላለጡ ስለአዳኙ ኢየሱስ ክርስቶስ መኾን አለበት። ኢየሱስን ማዕከል ያላደረገ የእርሱንም አዳኝነት የማይገልጥ ስብከት ሊኾን ሊባልም አይችልም።” [v]

    ስለዚህም በሥጋ የተገለጠውና ከቅድስት ድንግል ማርያም በመወለድ ሕጻንና ጌታ ኾኖ የመጣው ጌታችን ኢየሱስ፣ ነገረ ሚስጢሩ ከሰው ድርሰት፣ ልብ ወለድ፣ ፍልስፍና፣ አመክንዮ፣ ምርምር፣ ምድራዊ ከኾነው ከሰዎች “ሃይማኖታዊ እሳቤ” ኹሉ የተለየ ልዩ ነው። ምክንያቱም፣ “ያልፉ ዘንድ ያላቸው የዚህ ዓለም ነገሥታት፣ ፈላስፎች የሚያውቁት ጥበብ አይደለም። … ጥበብ ያልኹት ኅቡዕ [የተሰወረ ምስጢራዊ] ክሱት [የተከሰተ ወይም የተገለጠ] የሚኾን ሥጋዌ ነው” በማለት የኢትዮጲያ ሊቃውንት አብራርተውታልና።[vi]
     እርሱ ከድንግሊቱ በግብረ መንፈስ ቅዱስ የተወለደና በሥጋ የተገለጠ አምላክ ነው፤ “እንኪያስ ፈጽሞ አይታይ የነበረ ክርስቶስ በሥጋ ተገለጠ፤ አምላክ እንደኾነ ተናገረ፤ አምላክ እንደመኾኑ የአማልክትን ሥራ ኹሉ ሠራ፤ እርሱም በእውነት የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ነው፤”[vii] ቅዱስ ጳውሎስ ሥጋ ስለኾነው አምላክ ወይም ስለ ነገረ ትሥጉት ታላቅ ምስጢርነት አጕልቶ ይነግረናል። የእርሱ ሰው መኾንና እኛን ማዳን የቅድስናና የመንፈሳዊ ነገር ኹሉ መሠረት ነው።
ማጠቃለያ
    አንድ አማኝ ለመዳኑ አለኝታ የሚኾንለትና ስለመዳኑም ምስጋና ለማቅረብ በሥጋ የተገለጠውን አምላክ በትክክል ማወቅ ይገባዋል፣ ምክንያቱም ያላመኑት ያምኑ፤ ያመኑት ደግሞ ይጸኑ ዘንድ በክርስቶስ አስቀድሞ የታዘዘው ውዳዊ ግዴታ አለበትና። ከቅድስት ድንግል በመወለድ በሥጋ የተገለጠውን አምላክ በትክክል አለማወቅ መንፈሳዊ ማንነትን ከማቃወስ በላይ ለከፋ ኑፋቄ ይዳርጋል። ለዚህም ነው፦ በክርስቶስ መምጣት ወይም በመገለጡ ያገኘነውን ሊቀ ጉባኤ አበራ እንዲህ በማለት የሚገልጡት፦
     “እንደ ሕፃንም ተወልዶ ወደዚህ ዓለም በመምጣቱ የመዳናችን ምስጢር ተገልጧል። በትንቢቱም መሠረት ሕፃን ተወልዶልናል፤ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል፤ በሰውና በእግዚአብሔር መካከልም እርቅ ተወጥኗልና በእውነትም የሥግው ቃል ታሪክ የምሥራች ቃል ታሪክ ነው። ይህም የተስፋችንና የደስታችን ሁሉ መጀመርያ ነው። ስለሆነም ሰውና መላእክት በአንድነት ተገናኝተው እግዚአብሔርን አመሰገኑት(ሉቃ. 2፥8-14)። እንግዲህ በጽንሰቱና በልደቱ የተወጠነው እርቅ በመስቀሉ ተፈጽሟል። እርሱ በአዲስ ኪዳን ደሙ የአዲስ ኪዳን አስታራቂ በመሆን በሥጋ ተገልጧልና (ማቴ. 26፥28)። … ስለዚህም እርሱ የአዲስ ኪዳን፣ የአዲስ ሥርዓት መካከለኛ ማለት ለመንግሥተ ሰማያት አስታራቂ ሆኗል (ዕብ. 12፥24)። ለሁሉም ቤዛ አድርጐ ራሱን አሳልፎ ለሕማም ለሞት በመስጠት ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር በማስታረቁ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የሚገኝ አንድ መካከለኛ እርሱ ብቻ እንደሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ ያስተምረናል(1ጢሞ. 2፥5-6)።”[viii]

  አዎን! በሥጋ የተገለጠው አምላክ እርሱ የመገለጥ ኹሉ ዳርቻ፤ ወሰንና መደምደሚያ ነው። ስለዚህም ከእርሱ የሚበልጥና ልንሰማው የሚገባን ሌላ አንዳች መምህር የለንም፤ “ከእኔ ተማሩ”(ማቴ. 11፥28) እንዳለን፣ ልንሰማውና ልናደምጠው የሚገባን አንድ ጌታ በሥጋ የተገለጠው አምላክና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን፤ (ኤፌ. 6፥24)።



    [i] አባ ጎርጎርዮስ(ሊቀ ጳጳስ)፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ፤ 1978 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ.7።
   [ii] ኮሊን ማንሰል(ቀሲስ)፤ ትምህርተ መንፈስ ቅዱስ፤ 1999 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ በንግድ ማተሚያ ቤት ታተመ፤ ገጽ.38
   [iii] ኮሊን ማንሰል(ቀሲስ)፤ ትምህርተ ክርስቶስ 2ኛ እትም፤ 1999 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፤ ገጽ.66
   [iv] እግረ መንገድ አንድ ነገር ማንሳት ግድ ይኾንብናል። የእምነት እንቅስቃሴ መምህራንና አማኞች “በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ” የሚለውን ቃል በመያዝ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጽደቁ በፊት [ክብር ይግባውና] “ተኮንኖ ወይም ሰይጥኖ (ወደ ሰይጣንነት ተቀይሮ ነበር” በማለት ይህን ጥቅስ የደገፈላቸው መስሏቸው ይጠቅሳሉ። ነገር ግን ተሰግዎቱን በተመለከተ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በተደጋጋሚነት በአንድነት ተጠቅሰዋል። ጌታችን ኢየሱስ “በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን አወጣ” (ማቴ. 12፥28)፣ “ለድሆች ወንጌልን እንዲሰብክ፤ ለታሰሩትም መፈታትን ለዕውሮችም ማየትን ይሰብክ ዘንድ፥ የተጠቁትንም ነጻ ያወጣ ዘንድ የተወደደችውንም የጌታን ዓመት ይሰብክ ዘንድ” መንፈስ ቅዱስ ለአገልግሎት ለይቶታል፤ (ሉቃ. 4፥17-19)፣ ከሙታን መካከልም ያስነሣውና (ሐዋ. 2፥32 ፤ ሮሜ. 1፥4) አገልግሎቱን ያጸደቀውና ያረጋገጠው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው። ራሱ ጌታችን ኢየሱስም ወደሰማያት በሄደ ጊዜና መንፈስ ቅዱስ ሲመጣ ክርስቶስ የተናገረውን ያንኑ ትምህርት ለደቀ መዛሙርቱ በማስተማርና በማስታወስ የእርሱን ሥራዎች ሁሉ እንደሚያጸና፤ እንደሚያረጋግጥ ተናገረ፤ (ዮሐ. 14፥25-27 ፤ 16፥13-15)። ዓውዱ የሚነግረንና የሚያስተምረን ይህን እንጂ የኢየሱስን መሰይጠን አይደለም። ክብር ይግባውና እርሱ ቅዱስና ነውር የሌለበት ጻድቅ አምላካችንና ቤዛችን ነው፤ አሜን።
[v] ሐብተ ማርያም ወርቅነህ(ሊቀ ሥልጣናት)፤ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ.ክ. የስብከት ዘዴ፤ 1980 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ትንሣኤ ማተሚያ ድርጅት፤ ገጽ.64
[vi]  1ቆሮ.2፥6ን ኢትዮጲያ ሊቃውንት እንዳብራሩት፤ የቅዱስ ጳውሎስ አንድምታ
[vii]   ሃይማኖተ አበው ዘአቡሊዲስ ምዕ.42 ክፍል 8 ቁ.15
[viii]  ሊቀ ጉባኤ አበራ በቀለ(አባ)፤ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት፤ 1996 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ማኅበረ ቅዱሳን፤ ገጽ.42


1 comment:

  1. አሜን እጅግ ታላቅ እውነት

    ReplyDelete