Friday, 18 July 2025

ጋብቻና ሕመሙ

 Please read in PDF

እግዚአብሔር አምላክ በፍጥረት መጀመሪያ ያስቀመጠው እውነት፣ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ።” (ዘፍ. 1፥31) የሚል ነው። ስለዚህም የእግዚአብሔር ፈቃድ በመልካም ነገር ደስተኞች ኾነን እንድንኖር ነው። ነገር ግን በብዙ ጥንዶች መካከል፣ ይህ መልካም ደስታ ጨንግፎና መክኖ ይስተዋላል። በተለይም ደግሞ በዚህ ዘመን ፍቺና “ከፍቺ በኋላ ያለ የብቻ እናትነት” እንደ በጐ ነገር ሲቈጠር ይስተዋላል። የሠርጉ ቀን “ኪዳን” እንደ ዋዛ ተሰብሮ ወይም ኾን ተብሎ ተሰብሮ ወይም ከልክ ባለፈና በተደጋገመ ቸለተኝነት ተሰባብሮ፤ ሠርጉ ብቻ ደስታ፤ ትዳሩ ግን “የልቅሶ አውድማ” የኾነባቸው ቊጥራቸው ቀላል አይደለም።

በዚህ አደጋ ላይ፣ “የማይፈውሱ አማካሪዎች፤ ተከታትለው የማይመግቡ መጋቢዎች” ሲጨመሩበት፣ ነገሩን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ያደርጉታል። ዘመናዊነት እየናጣት፤ የባህል ቀውስና የመልካም እሴት መንጠፍ በወረራት ምድር ላይ ጋብቻ መታመሙ፤ ትዳር ማቃሰቱ አይቀርም። ስለዚህም ጋብቻን ከራሱ ከእግዚአብሔር መማርና መረዳት እንደ ረሞጫና ሚራዥ ከሚጋረፈው “የትዳር ወላፈን” ለማምለጥና ለመዳን ዕድል እናገኛለን።

እግዚአብሔር ሰውን በመልኩና በአምሳሉ የመፍጠሩ ምስጢር አስደናቂና ውብ ነው፤ (ዘፍ. 1፥26)። ከሰው ልጅ መፈጠር ጋር እግዚአብሔር በአምላካዊ መግቦቱ ለሰው ልጆች ኹሉ ስጦታ አድርጎ ከሰጣቸው ስጦታዎች አንዱ፣ ጋብቻ ነው። ይኸውም ጋብቻ የመሰጠቱ አንዱ ዓላማ፣ ቅዱሳንና አለነውር ኾነን እንድንኖር መኾኑ ግልጥ ነው። ማናቸውም የርስ በርስ ግንኙነት መሠረቱ፣ ልክ በሥላሴ መካከል እንዳለ የኅብረት አንድነት ሰዎች ኹሉ በተለይም አማኞች ኅብረት እንዲያደርጉ ይፈልጋል። ሰው ግን ይህ ግንኙነቱ ከእግዚአብሔርም፤ ከሰውም ጋር በኀጢአት ምክንያት ተሰበረ፤ ጎደፈም።

ጋብቻ በተቃራኒ ጾታዎች መካከል የሚመሠረት ኪዳናዊ ግንኙነት እንደ መኾኑ፣ ግንኙነቱ ጠንካራና የሕይወት አስተማሪ ኾኖ የተሰጠን ነው። ጋብቻ ተራ ግንኙነት ስላይደለ፣ እንደ አያያዛችን በእኛ ላይ የሚያስከትለው የበጎም ኾነ የክፉ ከፍ ያለ ተጽዕኖ ስለ መኖሩ እሙን ነው።

የጋብቻ አጋርን በትክክል አለመቀበል ዕዳውና ዳፋው ብዙ ነው። አጋራችንን ለጥቅማችንና ለዕድገታችን እንደ ተሰጠን ማየትና መቀበል ብጽዕና ነው። በዚህ መንገድ ሠላምና ዕረፍት፤ መጽናናትና ደስታ አለ።  የትዳርን አጋርን ከዚህ በተቃራኒው መመልከት ግን ለማያባራና ጥዝጣዜ ለተሞላበት "የወዳጅ ቁስል" መጋለጥ ነው። አንዳንዴ እኛ በጎና ቀና ኾነን ነገር ግን አጋራችን "የባለንጣ ያህል ጎንታይ" ቢኾንም እንኳ፣ "መምህርና ሐኪም" መኾናችንን መዘንጋት የለብንም!    

በአንዳንድ ትዳሮች ውስጥ መርዛማ ቃላትን የሚረጩ፤ ጨፍጋጋ ፊትን ተሸክመው የሚኖሩ፣ ተግባሮቻቸው  ተንኳሽና ቁስልን የሚያመረቅዙ ...የትዳር አጋሮች አሉ። ጤናማው የትዳር አጋር ይህን በትክክል ለማከምና ለማስተማር፣ ብርቱ ጥንቃቄ እንደሚያሻው ለጥያቄ አይቀርብም። የሠርጉ ቀን በማግስቱ የሚመጣውን ተግዳሮት በምልክት ረገድ እንኳ አይተው ቢኾኑ፣ ግንኙነቱን እንደማይጀምሩ የሚናገሩ ወይም  “ያኔ ተዉ ስንባል አልሰማንም፤ ይበለን” የሚሉ አያሌዎች ናቸው። ዳሩ “ሕልም ተፈርቶ ...” እንዲሉ፣ ተግዳሮት አልባ፤ ሰልፍ የለሽ ኑሮ የለም።

የትዳራችን የስብራቱ ጅማሮ የቱ ጋ እንደ ኾነ ወይም ምክንያቱ ምን እንደ ኾነ ማወቅ ለጥንዶች ትልቅ ብስለት ነው።

ደስታችንን የነጠቀውን፣ ያላግባባንን ነገር ከሥሩ ማጥራት ጥሩ ነው። አለመቀባበል፣ አለመተማመን፣ የዐሳብ አለመስማማት፣ የቤተሰብና የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት፣ ገንዘብና አጠቃቀሙ ከኾነም ... ችግሩን በትክክል ተረድቶ ዕልባት መሻት እንጂ፣ ከዚህ ሸሽቶ ፍቺን ወይም መለያየትን ወይም አልተለያዩም ላለመባባል ብቻ በአብሮነት መኖርን ምርጫችን ብናደርግ ቃሉ፣ “እግዚአብሔር አንድ አላደረጋቸውምን? በሥጋም በመንፈስም የርሱ ናቸው። ለምን አንድ አደረጋቸው? ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለውን ዘር ይፈልግ ስለ ነበር ነው። ስለዚህ በመንፈሳችሁ ራሳችሁን ጠብቁ፤ ከወጣትነት ሚስታችሁም ጋራ ያላችሁን ታማኝነት አታጓድሉ።” (ሚል. 2፥15) ይለናል።

ችግር ስለ ገጠመን ብቻ ትዳርን የማፍረስ መብት ጨርሶ አልተሰጠንም፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ ለዘለዓለም አንድ ይኾኑ ዘንድ ነውና፤ (ማቴ. 19፥6) ይህ ብቻ አይደለም፤ ባል በክርስቶስ ሚስት ደግሞ በቤተክርስቲያን በተመሰሉበት ክፍል፣ ባል ሚስትን ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን በወደደበት ፍቅር እንዲወድድና ሚስትም ቤተክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛው እንዲኹ ለባል እንድትገዛ ተነግሮአል። ይህ ጨርሶ ጊዜያዌና የተወሰነ ጊዜ የሚከናወንና በኹኔታዎች የሚቋረጥ እንዳልኾነ መዘንጋት የለብንም።

ግና አብሮ የማያኖር ነገር ቢከሰትስ? ሐዘናችን እያየለ፤ ልቅሶአችን እየጨመረ፤ አጋራችን ከባላንጣነት ያልዘለለ ፋይዳ ባይኖረውስ? ስህተቱ ተደጋጋሚ፤ ጥፋቱ እየባሰ ቢሄድስ? ... እግዚአብሔር የፈውስን መንገድ እንዳዘጋጀ እናምናለን።

እግዚአብሔር በትዳራችን ውስጥ ያሉ ጉዳዮች ሲመጡ እውቅና እንድንሰጥ፣ እነሱን ለይተን ለማወቅ እና እንደ ቡድን ለግንኙነት እና ግላዊ እድገት እንድንሰራ ይፈልጋል።  ይህን ካደረግን እንደ ባልና ሚስት ማደግ እንቀጥላለን እና በጋብቻ ውስጥ የበለጠ ጉልህ የሆኑ ግንኙነቶችን፣ መቀራረብን እና ጥንካሬን እንድናዳብር እንፈቅዳለን።

እግዚአብሔር ማንም ሰው በስሜታዊነትም ሆነ በአካል ደህንነቱ ባልተጠበቀ አካባቢ እንዲቆይ አይፈልግም።  ይሁን እንጂ በትዳራቸው ደስተኛ ያልሆኑ ወይም እርካታ የሌላቸው በጣም ብዙ ባለትዳሮች አስፈላጊውን እርዳታ ባለማግኘታቸው ወይም ችግሮቻቸውን በበቂ ሁኔታ ለመፍታት ቶሎ ብለው በመተው አምላክ ለእነሱና ለቤተሰባቸው የሚሰጠውን በረከት ይናፍቃቸዋል። እናም አንዳንዴ ጋብቻቸውን ቶሎ እንዴት መልሰው ማግኘት እንደሚችሉ ያስባሉ።

ትዳራችሁን መልሳችሁ ማግኘት የሚችሉባቸው ብዙ መንገዶች አሉ።  በመጀመሪያ፣ ለደስታችን ማጣት የትዳር ጓደኛችንን መውቀስ ማቆም አለብን።  ለደስታችን ተጠያቂው እኛው ብቻ ነን።  በትዳራችን ውስጥ በግላዊ እርካታ፣ ሐሴት ወይም ደስታ እጦት እየተሰቃን እንደ ሆነ ካወቅን በጣም ጉልህ የሆኑትን የደስታ ቦታዎችን እና መንስኤዎቹን ለመገምገም ጊዜ ልንወስድ ይገባናል።

ሌላው ትዳራችንን መልሰን ማግኘት የምንችልበት መንገድ እግዚአብሔር የልባችንን ክፍል እንዲያሳየን በመጠየቅ መጸለይ ነው።  ኃላፊነት መውሰድ ያለብንን ነገር እንዲገልጽልን መጠየቅ፣ እና እንዴት እንድናድግ እንደሚፈልግ እና ምን እንደምንማር የሚፈልገውን በእሱ አምሳል እንድንማር በግልጽ እንዲያሳየን በጸሎት መጠየቅ። 

ሌላው የታመነና የተመሰከረ ትዳር ያለውን መጋቢ መያዝ መልካም ነው። ይህ መጋቢና አማካሪ ትዳራችን ሊለወጥባቸው የሚችሉ አዳዲስ ክህሎቶችን እና ባሕርያትን ለማዳበር መንገዶችን እንድናስብ ይረዳናል።  ትዳራችንን ለማስመለስ የሚረዳው ሌላው ጠቃሚ መንገድ የትዳር ጓደኛችንን በሕይወታችን ውስጥ እንደ መጥፎ ሰው ማየትን ማቆም እና እንደ ጓደኛችን ማየት መጀመር ይኖርብናል። አንዳችን ሌላችንን በምናክምባቸው ወራት ርኅራኄን ማሳየትን እንዳንዘነጋ።  መጸለይን ማዘውተር፣ አንዱ አጋር በሌላው አጋሩ  ውስጥ የሚያደንቃቸውን ባሕርያት በዝርዝር አዘጋጅቶ እያስታወሰ እንደ ወዳጅ ቢባርከው እጅግ መልካም ልምምድ ነው።

ጥንዶች ዘወትር ስለ አብሮነታቸው መጸለይ አለባቸው፤ ለችግር እንዳይጋለጡ ቢጋለጡ ደግሞ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ከእግዚአብሔር ምሪትና ከቅዱስ ቃሉ ምክር ለመጠየቅ በትህትናና በጥበብ ይጸልዩ። የትዳር አጋሮች ዘወትር ልባየውን መጠበቅ እንዳለባቸው ከቶውኑ ሊዘነጉ አይገባም። በቂም እንዳይማረሩ፣ ተስፋ በመቁረጥ ደዌ እንዳይያዙ ሊተጉ ይገባቸዋል።

በትዳሮች ኹሉ ላይ እግዚአብሔር የደስታና የዕልልታ እንዲኹም ችግርን የመፍታት ጥበብና የጸጋ ዘይት ያፍስስ፤ አሜን።

2 comments:

  1. ዲያቆን ተባረክ ድንቅ መልዕክት

    ReplyDelete
  2. ጌታ ይባርህ አብዝቶ ❤❤❤🎉🎉

    ReplyDelete