Sunday, 23 March 2025

በአጕል ትህትና ሥጋን አትጨቁኑ!

 Please read in PDF

መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ቃል፣

“… ለዚህ ዓለም መርሕ ከክርስቶስ ጋራ ከሞታችሁ፣ ታዲያ በዚህ ዓለም እንደሚኖር ለምን ትገዙላቸዋላችሁ? “አትያዝ! አትቅመስ! አትንካ!” እንደሚሉት ዐይነት፣ እነዚህ ሁሉ በሰው ትእዛዝና ትምህርት ላይ የተመሠረቱ ስለ ሆኑ በተግባር ላይ ሲውሉ ጠፊ ናቸው። እነዚህ ነገሮች በገዛ ራስ ላይ ከሚፈጥሩት የአምልኮ ስሜት፣ ከዐጕል ትሕትናና ሰውነትን ከመጨቈን አንጻር በርግጥ ጥበብ ያለባቸው ይመስላሉ፤ ነገር ግን የሥጋን ልቅነት ለመቈጣጠር አንዳች ፋይዳ የላቸውም።” (ቈላ. 2፥21-23)

ይላል።


ለአማኞች የተሰጠው ልከኛው የመመላለሻ መንገድ ወይም የኑሮ ዘይቤ መገለጫ፣ “ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ፤” (ቈላ. 2፥6) የሚል ነው። ጌታችን ኢየሱስ የሚኖር ሕይወትና የሚከተሉት ትምህርት ያለው ጌታና መምህር ነው። ቅዱስ ጳውሎስ፣ አማኞች ከክርስቶስ ጋር ባላቸው ግንኙነቶች፣ ፍጹም የተቀራረበና በመንፈስ አንድነት የጐለበተ ሊኾን እንደሚገባ ደጋግሞ ይጠቅሳል፤ “ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ”፣ “ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል።”፣ “ከዓለማዊ ከመጀመሪያ ትምህርት ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ…” (ምዕ. 2፥7፡ 10፡ 20) የሚሉትና ሌሎችም ንባባት የሚያመለክቱት፣ አማኙ ከክርስቶስ ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖረው ነው።

አማኞች ደግሞ ይህን ሕይወት ለመኖር ዋስትና አላቸው፣ ይኸውም፦ አማኞች የሥጋውን ሰውነት በመግፈፍ ወይም ፍጹም የኾነ የኀጢአትን ይቅርታ አጊኝተዋል (ቊ. 11)፣ ከመንፈሳዊ ሞት ነቅተው ከክርስቶስ ጋር ብቻ ለመኖር ይቅርታን በማግኘት ሕያዋን ኾነዋል (ቊ. 12-13)፣  ጨቋኝና ተቃዋሚው፤ የክፍት ተጽዕኖ አድርጊው በመስቀሉ ሥራ ተጠርቆ ተወግዶላቸዋል (ቊ. 15)፣ ከዚህም ባሻገር ከዓለማዊና ከመጀመሪያ ትምህርት ወይም እንደ ሕግ ካሉ ዕዳዎች ኹሉ ነጻ ናቸው (ቊ. 15 እና 22)። አማኞች ይህን በክርስቶስ በማግኘታቸው፣ በጽድቅ ለመመላለስ ትልቅ ዋስትና አላቸው።

ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒ ይህን እንዳናስተውል፣ የሐሰት ትምህርት በባህርይው ሳቢ ኾኖ ይቀርብልናል፣ ማስተዋል ያለብን እውነት፣ የሐሰት ትምህርት ምንም ሳቢ ቢኾን ምንጩ መለኮት አይደለም። ቅዱስ ጳውሎስ ከላይ የተጠቀሰውን ሕይወት አማኞች እንዳይኖሩት፣ ሐሰተኛ አስተማሪዎች በሚያስደንቅ መንገድ ትህትናን በማሳየት ሥጋቸውን የመጨቆን ትምህርት ያስተምራሉ በማለት ትምህርታቸውን ያጋልጣል (ቊ. 23)።  ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ያለ ትምህርትና ልምምድ ሥጋን በመቈጣጠር ወደ እግዚአብሔር እንደማያቀርብ ይናገራል፤ ነገር ግን ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መቅረቢያቸው ክርስቶስ፤ መጽኛውና መጽናኛው መንፈስ ቅዱስ እንደ ኾነና ጾም፤ ጸሎት፤ ምጽዋት … የዚህ ውጤት መኾኑን የመጽሐፍ ቅዱሱን ክርስትና ያስተምራል!

ብዙ ሃይማኖቶች ሥጋን መጨቆንና ፈጽሞ መጥላት ወደ እግዚአብሔር እንደሚያቀርብ ያስተምራሉ፤ ከዚህ የተነሣ እግዚአብሔር በክብር የፈጠረውን ሥጋቸውን ክብረ ቢስ እንደ ኾነ በመቊጠር፣ ሲያዋርዱ፣ ሲኰንኑ፣ ሲያስጨንቁ እናስተውላለን። በርግጥ ይህ የለበስነው ሥጋ ሙሉ ለሙሉ ያልተዋጀና ፍጹም ውጅትን ገና በመቃተት የሚጠብቅ ነው (ሮሜ 8፥22)፤ ይህ ማለት ግን ሥጋ ፍጹም ርኩስ፤ የማይረባ፣ ሊቀደስ የማይችል፤ ከቅዱሱ አምላክ ጋር ምንም ኅብረት ሊያደርግ የማይችል፤ ከሰይጣን ጋር ብቻ የሚጣበቅ … ነው ማለት አይደለም፤ ቅዱሱ መጽሐፍ፣ “ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ፤” (ሮሜ 6፥12)፣ “ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ” (ሮሜ 12፥1)፣ “በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ።” (1ቆሮ. 6፥20)፣ “…ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ” (1ተሰ. 5፥23) በሚለውና በአያሌ ንባባቱ ውስጥ፣ ሥጋችንን ለእግዚአብሔር ክብር በመቀደስ ማቅረብ እንዳለብን ይነግረናል።

ሥጋን ግን በማስጨነቅ ወይም በመጨቆን ወይም ፍጹም ትህትናን እያሳዩና በመልካም ሥራ በመትጋት፣ ያለ ክርስቶስ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ አይቻልም፤ “እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።” (1፥13-14) እንዲል፣ የዳንነው በልጁ በክርስቶስ ነው፤ ወደ አባቱ የምንቀርብበት ቀጥተኛውና የማያሳስተው መንገድና ጽድቃችን ክርስቶስ ኢየሱስ ነው!

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።

3 comments:

  1. ተባረክ የእግዚአብሔር ሰው ።እሰከ መጨረሻው በጽናት ያቁምህ።

    ReplyDelete
  2. ያቀበልkew መንፈስ ቅዱስ ተባረክ

    ReplyDelete
  3. ክብሩ ይስፋ የድንግል ማርያም ልጅ አማኑኤል...

    ReplyDelete