Sunday, 18 August 2024

የ“ታቦር” ስብከቴን ቀይሬአለኹ!

 Please read in PDF

ጌታችን ኢየሱስ ክብረ መንግሥቱን የገለጠበት፤ ማንነቱን ለደቀ መዛሙርቱ ያሳየበት የክብሩ ተራራ እውነት እጅግ አስደናቂ ነው። ጌታ፣ በፊልጶስ ቂሣርያ፣ “ለብቻውም ሲጸልይ ደቀ መዛሙርቱ ከእርሱ ጋር ነበሩና፦ ሕዝቡ እኔ ማን እንደ ኾንሁ ይላሉ? ብሎ ጠየቃቸው።” (ሉቃ. 9፥18) ደቀ መዛሙርቱ ሲመልሱ፣ የነቢያትን ስም በመጥራት እንዲኹም ከነቢያት አንዱ ነህ ይላሉ ብለው መለሱ። ቀጥሎም፣ “እናንተስ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው።” (ሉቃ. 9፥20) “ጴጥሮስም መልሶ፦ ከእግዚአብሔር የተቀባህ ነህ አለ።”ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን ታላቅ እውነት በመመለሱ፣ “ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።” (ማቴ. 16፥17) በማለት የጴጥሮስን ዕድለኝነት ጌታችን መሠከረለት።

ኢየሱስ ሥጋ ለብሶ በመገለጡ፣ በአይሁድ ዘንድ ብዙ ክርክር አስነስቶአል፤ ሥጋ በመልበሱ ብቻ አይደለም፤ ይልቁን መከራ በመቀበል ስቁይ ሎሌ እንደሚኾንና ተላልፎ እንደሚሰጥ በተረዱ ጊዜ፣ የተቀባውን መሲህ በዚህ መንገድ አልጠበቁምና ሊቀበሉት አቃታቸው። ለዚህ ነው ቅዱስ ጴጥሮስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅነቱን ከመሰከረ በኋላ፣ ጌታ ኢየሱስ እንደሚሞት በተናገረ ጊዜ፣ “ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ፦ አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገሥጸው ጀመረ።”(ማቴ. 16፥22) የሚለን። ጴጥሮስ የመሲሑ ን መከራ መቀበል ለማመን ተቸገረ።

ኢየሱስ ይህን የጴጥሮስን ያለመቀበል ዐሳብ የሰይጣን ዐሳብ ነው በማለት ተቃውሞአል (ማቴ. 16፥23)። ይህን ዐሳብ በክብሩ ተራራ ላይም፣ “... ጴጥሮስ ኢየሱስን፦ አቤቱ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ ...” (ሉቃ. 9፥33) በማለት ደግሞታል። ጴጥሮስ መከራንና ሞትን ጠልቶ፤ ግን ደግሞ ደስታንና ክብርን ከመከራ ውጭ መፈለጉ እጅግ የሚደንቅ ነው። እኔም ይህን የጴጥሮስን አባባል ወድጄ በተደጋጋሚ ሰብኬው ነበር፤ ትክክል አልነበርኹም።

ጌታ ሞቱን ለደቀ መዛሙርቱ ከተናገረ ከስምንተኛው ቀን በኋላ፣ በአንድ ከፍ ባለ ተራራ ላይ ክብሩን ለሦስቱ ደቀ መዛሙርት ገለጠላቸው። አገላለጡንም ቅዱሱ መጽሐፍ፣ “በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ኾነ።” (ማቴ. 17፥2) በማለት ይገልጠዋል። ጌታ ፍጹም መለኮታዊ ክብሩን ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም ማየት እስኪሳናቸው በደመናው ተጋረዱ። አንድ ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ ሰምተዋል፣ “እነሆም፥ ኹለት ሰዎች እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤

በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር።” (ሉቃ. 9፥30-31) ይህም ነገረ ሕማማቱና ሞቱ ነው። ነቢያት በብዙ ዓይነት መንገድና ጎዳና የተናገሩለት ሕማምና ሞቱን ነው። ሙሴና ኤልያስም ይህን ያወሩ ነበር። ለነጴጥሮስ ግን ይህ ነገር ለጊዜው ያልተብራራ ነበር። በዚህ መካከል እግዚአብሔር አብ፦ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት።” (ሉቃ. 9፥35) አለ። የሰውን ልጅ ለማዳን ለቤዝወት የተመረጠና አብ የወደደው፤ ደግሞም የአብን ምክርና ዘላለማዊ እውነት በትክክል የሚናገር ነውና ርሱን ስሙት አለ። ልንሰማ የሚገባን አንድ ድምጽ ቢኖር፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ድምጽ ብቻ ነው፤ እንከንም፤ እብለትም የለበትምና! ስሙ ይባረክ፤ አሜን።

ከዚህ መገለጥ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ሲነቁ ከኢየሱስ በቀር ማንንም አላዩም። ሙሴም፤ ኤልያስም አልነበሩም። ዘላለም ሕያውና ብቻውን ጸንቶ ኗሪው ጌታችን ኢየሱስ ብቻ ነበር። ከመንፈስ ቅዱስ መውረድ በኋላ ይህን ዘላለማዊ እውነት ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ገልጦታል፣ “የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ።” (2ጴጥ. 1፥16) የጌታችን መገለጥ የዘላለም ሕያው እውነት ነው። የቱም የሰው ተረትና ብልሃት በዚህ መገለጥ ፊት ከገለባ ይልቅ የቀለለ እርባና ቢስ ነው። መገለጡና ክብሩ የትኛውንም መከራ መስቀል ድል የሚነሣ፤ እንድንታገሥም አቅም የሚሰጥ ብርቱ እውነት ነው። ክብሩም መስቀሉም አይነጣጠሉም፤ ሞቱም ትንሣኤውም ለመዳናችን የዘላለም ዋስትናችን ነው፤ አሜን ሃሌ ሉያ!

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወድዱ ሁሉ ጸጋ ይሁን።” (ኤፌ. 6:24) አሜን።

2 comments:

  1. ወደ ኦርቶዶክስ ተመለስ

    ReplyDelete
  2. እግዜአብሔር ዘመንህን ይባርክ!!

    ReplyDelete