Wednesday, 29 May 2024

የድል መንገድ!

 Please read in PDF

መስቀልና ትንሣኤ ሊነጣጠሉ የማይቻላቸው፣ የክርስትና የአንድ ሳንቲም ኹለት ገጽታዎች ናቸው። መስቀሉ ውርደትን፣ ሽንፈትን፣ አለልክ ዝቅ ማለትን በውስጡ የያዘ ቢኾንም፣ ድል መንሣትን፣ ሙሉ ለሙሉ የተፈጸመ ወይም የተጠናቀቀ የኅጢአት ክፍያን (ዮሐ. 19፥30)፣ ጠላትን ጠርቆ ከመንገድ ማስወገድን ኹሉ (ቈላ. 2፥14) አጭቆ የያዘ፣ የክርስትና እጅግ አስደናቂ መንገድ ነው።

መሲሑ መላ ዘመኑ በመስቀል የተከበበና የታጠረ ነው፤ ኢየሱስን ከመስቀል፤ ክርስቶስን ከሎሌነት ነጥሎ ማየት ምናልባት ኑፋቄነትን ወይም ጠላትነትን ሊያስከትል ይችላል፤ (ፊል. 3፥18)። ክርስትና ከመስቀል ከተነጠለ፣ ትርጕም አልባ ሃይማኖት ነውና። እግዚአብሔር መላለሙን ለማዳን ስቁይ ሎሌ፤ የሕማም ሰው (ኢሳ. 53፥3) የመስቀል መንገድ (1ቆሮ. 1፥23) መምረጡ እጅጉን ይደንቃል! ሊያድንና ሊቤዥ የመጣውም መሲሕ፣ በዚህ መንገድ መታዘዙ እጅጉን ይደንቃል!

እንደ ሰው ዐሳብ፣ የመስቀል መንገድ ፈጽሞ ሊወደድ አይችልም፤ እስከዛሬም እንኳ በብዙዎች ዘንድ አልተወደደም! በቀደመው ዘመን የመጨረሻው ዐመጸኛ ወንጀለኛ፣ የሚቀጣውና ቅጣቱንም የሚፈጽመው በመስቀል ተሰቅሎ ነው። ኢየሱስ እንደ ዋናና ዐመጸኛ ወንጀለኛ ታስቦና ተፈርዶበት መሰቀሉ፣ እንኳን ለቅዱሱ አምላክ ባሕርይ ይቅርና ለንጹህ ሰው እንኳ የሚመች አይደለም፤ እናም እግዚአብሔር፣ ሰው ጨርሶ ሊገምተው በማይችል መንገድ ሰውን በማዳን፣ ለራሱ ብቻ ክብርን ያመጣ ዘንድ ወደደ፤ በመስቀል ማዳንና መታደግ የእግዚአብሔር ብቻ እንጂ የሰው እጅ የለበትም የምንለውም ለዚህ ነው።

መሲሑ መታመሙ፣ መከራ መቀበሉ፣ መጨነቁ፣ መጠበቡ፣ ወዙ በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ መውረዱ (ሉቃ. 22፥44)፣ መፍራቱ፣ ንቀትን መጥገቡ፣ መጠላቱ፣ በገዛ ወገኖቹ ዕውቅናን ማጣቱ ... በቅዱሳት መጻሕፍት በምልአት ተነግሮአል፤ የሚያስደንቀው እውነት፣ በዚህ ኹሉ መከራ ውስጥ መሲሑ አልበደለም፤ አልዛተም፤ በአንደበቱ ሐሰት አልተገኘበትም፤ (1ጴጥ. 2፥22-23)። የያህዌን ውክልና የተቀበለችው የቀደመችዪቱ እስራኤል ዘሥጋ፣ በብዙ አለመታዘዝ ብትመላለስም፣ እውነተኛው የእግዚአብሔር የወይን ግንድና (ዮሐ. 15፥1) እውነተኛው እስራኤል ኾኖ  የተገለጠው መሲሕ ግን፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ፍጹም በመታዘዝ የአብን ልብ አርክቶአል፤ (ኤፌ. 5፥2)።

ለሰው ልጅ ፍጹም መዳን፤ ለእግዚአብሔር ክብር በፈቃዱ (ዮሐ. 10፥11) መሲሑ የተቀበለው መከራ፣ በትንሣኤ የፈካና እጅግ የተዋበ ነው! መስቀሉና መከራው ፍዳችንንና የእኛን የኀጢአት ቅጣት ለመቀበል በፈቃዱ ራሱን አሳልፎ መስጠቱን ሲያመለክቱ፣ ትንሣኤው ደግሞ የዕዳችን ክፍያ መጠናቀቁንና የእግዚአብሔርን ጽድቅ የሚያረካ ፍጹም መሥዋዕት መኾኑንም ያመለክታሉ። ይህን በማድረጉም፣ “ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፥ ዕድሜውም ይረዝማል፥ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል። ከነፍሱ ድካም ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፥ ኃጢአታቸውን ይሸከማል። ስለዚህም እርሱ ብዙዎችን ይወርሳል፥ ከኃያላንም ጋር ምርኮን ይከፋፈላል፤ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጥሮአልና እርሱ ግን የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸከመ፥” (ኢሳ. 53፥10-12) እንዲል ፍጹም ድል ነሥቶ አሸነፈ!

በዚህ አምላክ እጅግ ደስ ይበላችሁ፤ አሜን።

“በማያቋርጥ ፍቅር ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚወዱ ሁሉ ጸጋ ይሁንላቸው።” (ኤፌ. 6፥24)

1 comment:

  1. This concept is clearly reflected in the genuine literary sources of the Ethiopian Orthodox Church. For instance, the preparatory service of QEDDASE says: "who has seen a bridegroom who gives his flesh as a meal on the day of his wedding?" This unique bridegroom, is Jesus Christ, the only begotten Son of God, our Redeemer who has freed us from the bondage of the enemy.

    ReplyDelete