በሰሙነ ሕማማቱና በትንሣኤው ወቅት የነበረውን እውነት ካሰላሰለ በኋላ፣ ጴጥሮስ ክርስቶሎጎስ የተባለ አንድ አባት እንዲህ ብሎአል፤ “ሴቶቹ የክርስቶስን ትንሣኤ ለማክበር ቀዳሚዎች ናቸው፤ ደቀመዛሙርቱ ደግሞ ስለ ክርስቶስ መከራን ለመቀበል የመጀመሪያዎች ኾኑ። ሴቶቹ ሥጋውን ሽቱ ለመቀባት አዘጋጁ፤ ደቀ መዛሙርቱ ደግሞ ለቅጣት መሣሪያዎች ሰውነታቸው አዘጋጁ። ሴቶቹ ወደ መቃብር ገቡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ እስር ቤት ሊገቡ ነው። ሴቶቹ ምስክርነታቸውን ለመግለጽ የተፋጠኑ ኾነዋል፤ ደቀ መዛሙርቱም ስለ እርሱ የሰንሰለት እስራትን ለመቀበል የማይፈሩ ኾነዋል።” ብሎአል።
ከዓለም ርኩሰትና
ከኀጢአት ኃይል ነጻ አውጥቶ የጠራንና ያዳነን፣ ስቁልና መከራ ተቀባይ መሲሕ እንዲህ ብሎናል፣ “እኔን
አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው እንደ ኾኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ።” (ዮሐ. 15፥20)። እኛ ኢየሱስን መቀበላችንና ማመናችን የሚያመለክተው፣ ከእግዚአብሔር
ዐዲስ ሕይወትን እንደ ተቀበልን ነው። ይህ ዐዲስ ሕይወት ደግሞ፣ ክርስቶስን ካሳደደውና ከሰቀለው ዓለም በተቃራኒ ያቆመናል እንጂ፣
ከዓለሙ ጋር እንድናብርና አንድ እንድኾን አይጋብዘንም። በሌላ ንግግር አማኞች ከክርስቶስ የተነሣ፣ ከዓለም ስላይደሉ ዓለም በሙሉ
ኃይሉ በእነርሱ ላይ ስደትን፣ መከራን፣ ተቃውሞን ማስነሣቱ አይቀሬ እውነታ ነው።
ቅዱስ ጳውሎስ
እንዲህ ብሎአል፤ “በእርግጥም በክርስቶስ ኢየሱስ በእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት መኖር የሚወዱ ኹሉ ይሰደዳሉ።” (2ጢሞ. 3፥12 ዐመት)፤ ይህ እውነት በየትኛውም ዘመን ለሚኖሩ አማኞች የሚለወጥ መርኅ
አይደለም፤ (ማቴ. 10፥22፤ ፊል. 1፥29፤ 1ጴጥ. 4፥12)። ዓለሙ በሙሉ በእውነተኛ ኣማኞች ላይ የመነሣቱ ዋነኛ ምክንያት
ደግሞ፣ ጌታችን እንዳስተማረን እንዲህ የሚል ነው፤ “ይህንም የሚያደርጉባችሁ አብንና እኔን ስላላወቁ ነው።” (ዮሐ. 16፥3)። እንግዲህ መከራና ስደት ቢያገኘን፣ እንደ አንድ አገር ዜጋ የመኖር
ነጻነት ብንገፈፍ፣ በምድር ኹሉ ፊት የተገባን ባንኾንና በኹሉ ፊት እንደ ጉድፍ ብንቆጠር፣ እኛ መጤ ስለ ኾንን፣ ለመብታችን ተሟጋች
አካል ስለሌለን፣ ከሌላው አንጻር በቍጥር አናሳ ስለኾንን አይደለንም፤ የሚያሳድዱን ኹሉ የሚያሳድዱን አብንና ልጁ ኢየሱስን ስለማያውቁ
ነው።
እናም ለዚህ ነው፤
እንደ ቀደሙት የእምነት አባቶችና እናቶች፤ ወንድምና እህቶች፤ የተሻለውን ትንሣኤና ሕይወት በመናፈቅ፣ ለሞት በሚዳርግ ስቃይ ውስጥ
ብናልፍም፣ ከዚያ ከመውጣት ይልቅ በዚያ ውስጥ ለማለፍ በብርቱ የምንቃትተውና የምናምጠው። ከመስቀሉ ወዲያ ታላቅ ክብር አለ፤ ከክብሩ
ወዲህ ደግሞ እናልፍበት ዘንድ የተጋበዝነው መከራና መስቀል አለ፤ “እንግዲህ በጌታችን
ምስክርነት ወይም በእስረኛው በእኔ አትፈር፥ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔር ኃይል መጠን ስለ ወንጌል አብረኸኝ መከራን ተቀበል፤” (2ጢሞ. 1፥8) እንዲል።
መንፈስ ቅዱስ
ከመምጣቱ በፊት፣ ደቀ መዛሙርት መከራ ተሰቃቂ፤ ፈሪና ድንጉጥ ነበሩ፤ መንፈስ ቅዱስ ከመጣ በኋላ ግን፣ “ወደ
እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል” እያሉ በደስታ
የሚዘምሩ ነበሩ። ሙሽራ ለኾነውና እንደ ባሪያ በማገልገል ላለፈው መሲሕ አገልጋይ[አማኝ] የምንኾን ኹላችን፣ በትንሣኤ ክብሩ ብቻ
ያይደለ፣ በመስቀሉም ቀነዋት አብረን መከራ በመቀበል እንመስለው ዘንድ ይገባናል። አብረን ከብረናል የምትሉ ኹሉ፣ አብራችሁ መከራውን
በመቀበል የጽዮንን መንገድ ትጓዙ ዘንድ እጋብዛችኋለሁ፤ መንትዮቹ አይለያዩም፤ መስቀሉና ክብሩ!
“ጌታችንን
ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።
No comments:
Post a Comment