አብ እንደ ወደደን፣ በክርስቶስ እንደ ዳንን፤ በመንፈስ ቅዱስም እንደ ታተምን በሥላሴ የድኅነት ሥራ
ፍጹም እናምናለን!
መጽሐፍ ቅዱስ መዳንን ወይም ዳግመኛ መወለድን ወይም የዘላለም ሕይወትን በቀጥታ የሚያያይዘው፣ ከአዲስ
ኪዳኑ ወርቃማ ቃል ማለትም፣ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን
እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና፤” (ዮሐ. 3፥16 ዐ.መ.ት) ከሚለው ጋር ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አለመጥፋትን
ወይም ከዘላለም ሞት ማምለጫው በኢየሱስ ማመን ነው ይለናል።
“እግዚአብሔር ፍቅሩን በመካከላችን የገለጠው እንዲህ ነው፤ እኛ በእርሱ አማካይነት በሕይወት እንኖር
ዘንድ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ላከ።” (1ዮሐ. 4፥9 (ዐመት)። እግዚአብሔር ሰዎች በሕይወት እንዲኖሩ
በመፈለጉ፣ አንድያ ልጁን ወደ ምድር ላከ። ከዚህም የተነሣ መዳን በክርስቶስ ኹለንተናዊ ማንነት ላይ ብቻ እንጂ፣ ኹኔታን
ማዕከል ወይም ተገን ያደረገ አይደለም።
ራሱ ጌታ ኢየሱስ እንዲህ አለ፣ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት
ይኖራል፤ በእኔ የሚኖር፣ የሚያምንብኝም ከቶ አይሞትም፤" (ዮሐ. 11፥25-26)፤ ጌታችን ተወዳጅ ደቀ መዛሙርቱንም
እንዲህ ብሎ አዘዘ፣ “ ‘... ክርስቶስ መከራን ይቀበላል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል፤ ከኢየሩሳሌም ጀምሮ ለሕዝቦች
ሁሉ ንስሓና የኀጢአት ስርየት በስሙ ይሰበካል፤’ እናንተም ለዚህ ምስክሮች ናችሁ።" (ሉቃ. 24፥46-48)፤ ቅዱስ
ጳውሎስም እንዲህ አለ፣ "አሁንም፣ ወንድሞች ሆይ፤ የሰበክሁላችሁንና የተቀበላችሁትን ደግሞም ጸንታችሁ የቆማችሁበትን
ወንጌል ላሳስባችሁ እወዳለሁ፤ የሰበክሁላችሁን ቃል አጥብቃችሁ ብትይዙ፣ በዚህ ወንጌል ትድናላችሁ፤ አለዚያ ያመናችሁት በከንቱ
ነው።" (1ቆሮ. 15፥1-2)። የደቀ መዛሙርት የአደባባይ የወንጌል ምስክርነትም፣ “ድነት በሌላ በማንም አይገኝም፤
እንድንበት ዘንድ ለሰዎች የተሰጠ ከዚህ ስም በስተቀር ሌላ ስም ከሰማይ በታች የለምና።”” (የሐ.ሥ. 4፥12 ዐ.መ.ት) የሚል
ነው፤ ስለዚህ ለመዳን ለሰዎች ኹሉ የተሰጠው ወንጌል ወይም ራሱ ኢየሱስ ብቻ ነው።
ክርስቶስን በእምነት በመቀበልና በማመን ብቻ የዳነ ሰው፣ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ነውና፣ መንፈስ ቅዱስ
በእርሱ ይኖራል። ምክንያቱም አማኝ በክርስቶስ ወርቀ ደም የተቤዠና የተገዛ ውድ ፍጥረት ነውና (1ቆሮ. 6፥19-20፤ 7፥23፤
1ጴጥ. 1፥18-19፤ የሐ.ሥ. 20፥28)። እንግዲህ በባለጠጋው በእግዚአብሔር ጸጋ ለመዳን ወይም የዘላለም ሕይወት
ለማግኘት በክርስቶስ ማመን ብቻውን በቂ ነው። ይህን የሚያምኑትና የሚቀበሉት የክርስቶስ ለመኾናቸው ማረጋገጫውም መንፈስ ቅዱስ
ነው። “እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል ይህም የድነታችሁን ወንጌል በሰማችሁ ጊዜ ወደ ክርስቶስ ተጨምራችኋል፤ አምናችሁም፣
በእርሱ በመሆን ተስፋ ሆኖ በተሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ማኅተም ታትማችኋል።” (ኤፌ. 1፥13 ዐ.መ.ት)፣ ደግሞም፣
"በክርስቶስም ከእናንተ ጋር የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው፥ ደግሞም ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን
የሰጠን እርሱ ነው።" (2ቆሮ. 1፥21-22) እንዲሁም (2ቆሮ. 5፥5) ያንብቡ።
ጰሰዎች ለመዳናቸው ማረጋገጫው የጸጋ ስጦታዎች ባለቤት የኾነው መንፈስ ቅዱስ ራሱ እንጂ፣ የጸጋ ስጦታው
አይደለም። ልሳን መናገር ወይም ልሳንን መተርጐም[ኹለቱም የተለያዩና አንድ ሰው ዘንድ ላይገኙ የሚችሉ ጸጋዎች ናቸው] ከብዙ
የመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታዎች መካከል ናቸው (1ቆሮ. 12፥10፡ 28-30፤ ማር. 16፥17)። በልሳን መናገር የጸጋ ስጦታ
እንጂ፣ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ዋስትና አይደለም። እውነት እንናገር ከተባለ፣ በየአደባባዩ በብዛት የምንሰማው "የተቀጣጠሉና
የተደጋገሙ ቃላትን"፤ ልሳን ብሎ መጥራት እጅግ የሚቸግር ነው። ነገር ግን የተሳሳተ የልሳን ከንቱ ልምምድ ስላለ፣
እውነተኛውንና መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የልሳን ጸጋ አንጥልም፤ የመዳን ማረጋገጫም ነው ብለን የመዳናችንን ማኅተምና ዋስትና መንፈስ
ቅዱስን አናሳዝንም።
የጸጋ ስጦታዎች በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ እርሱ እንደ ወደደ የሚሰጡ ናቸው። የሚሰጡትም ለእግዚአብሔር
ክብርና ለቤተ ክርስቲያን መታነጽ ብቻ ነው እንጂ፣ ለግለሰቦች መደነቂና መመጻደቂያ አይደሉም። አንድ ነገር መዘንጋት የለብንም፤
ድነንም "የሚታይ የጸጋ ስጦታ" ላይኖረን ይችላል። ስለ መጥምቁ ዮሐንስ የተነገረውን እናንሳ፣ “ብዙ ሰዎችም
ወደ እርሱ[ኢየሱስ] መጥተው፦ ዮሐንስ አንድ ምልክት ስንኳ አላደረገም፥ ነገር ግን ዮሐንስ ስለዚህ ሰው የተናገረው ሁሉ እውነት
ነበረ አሉ።” (ዮሐ. 10፥4) ዮሐንስን ተመልከቱ፤ ስለ ኢየሱስ የመሰከረው ኹሉ እውነት ነበረ፣ ግን ምልክት አላደረገም፤
ይደንቃል! የዮሐንስ ምስክርነት እንደ ሂንዱ አልያም እንደሌላው ቤተ እምነትም አልነበረም፤ እንደ ቃሉ ብቻ እንጂ።
እንደ ኤፍሬም ያልተገላበጡ ቂጣዎች (ሆሴ. 7፥6) ታድያ፣ “የእምነት እንቅስቃሴ አማኙን በጋሻው
ደሳለኝን ወድደው፣ እኛን ለምን ጠሉን?” ብንል፣ መልሱ ግልጽ ነው፣ የዳንነውና ያዳነን ክርስቶስ ነው፤ ለመዳናችን ዋስትናው
መንፈስ ቅዱስ ነው፣ ጸንተን የምንቆመው ደግሞ በወንጌል እውነት ብቻ እንጂ በሌላ አይደለም ማለታችን ነው። እንዲህ ብሎ
ከእውነቸኛው ክርስትና በቀርም፣ ሌላ የሚያስተምር እንደሌለ እናምናለን። አሜን። እናም ልሳን ባንናገርም በክርስቶስ ለመዳናችን
ቅንጣት አንጠራጠርም! የልሳን መናገርና መተርጐም ጸጋ ያላቸውም እንደ መንፈስ ፈቃድ ቢመጡ፣ መርምረን እንደ
ቃሉ ከኾነ ልሳናቸው አሜን ለማለትም አንቸገርም!
ኢየሱስ ጌታ ነው!
GOD bless you for sharing Abiny. May the HOLY SPIRIT be your guide and strength for days to come, till your last breath.
ReplyDelete