“ችጋረኛውን
የምትውጡ፥ የአገሩንም ድሀ የምታጠፉ እናንተ ሆይ፦ እህልን እንሸጥ ዘንድ መባቻው መቼ ያልፋል? የኢፍ መስፈሪያውንም እያሳነስን፥
ሰቅሉንም እያበዛን፥ በሐሰተኛም ሚዛን እያታለልን፥ ድሀውን በብር ችጋረኛውንም በአንድ ጥንድ ጫማ እንገዛ ዘንድ፥ የስንዴውን ግርድ
እንሸጥ ዘንድ ስንዴውን እንድንሸምት ሰንበት መቼ ያልፋል? የምትሉ እናንተ ሆይ፥ ይህን ስሙ።” (አሞ. 8፥4-6)
ታሪካዊ ዳራ!
ነቢዩ አሞጽ ያገለገለበት
ጊዜ፣ በዳግማዊ ኢዮርብዓም የኋለኛው አጋማሽ ዘመን አከባቢ ነበር። በዚህ ዘመን ደግሞ የነበረው ብልጽግና፣ በማኅበራዊ ንቅዘት የተነወረ
ነበር፤ ንቅዘቱና መበስበሱም እጅግ ተስፋፍቶ ነበር። በሌላ መልክ ደግሞ፣ እስራኤል በእግዚአብሔር መመረጥዋን ተገን በማድረግ፣ ብዙ
በደልን ፈጽማ ነበር። እግዚአብሔርም በአሞጽ አንደበት በርግጠኝነት መመረጥዋን ተናገሮ (3፥2) ነገር ግን መመረጥዋ ብቻውን፣ ለእውነተኛው
በረከትና መትረፍረፍ ዋስትና አለመኾኑንም ሲናገር እንሰማዋለን። ምክንያቱም ለተስፋው ቃልና ለተሰጣቸው ትእዛዝ መታዘዝና መጽናት
አለባቸውና፤ “አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤”
(ዘጸ. 19፥5) እንዲል።