Thursday, 6 January 2022

መሲሑ ወደ ምድር የመጣበት ዋና ዓላማዎች!

Please read in PDF

በብሉይ ኪዳን ዘመን፣ እንደ ተናፈቀና እንደ ተቃተተለት የኖረ ታላቅ እውነት ቢኖር፣ ቅዱሱ መሲሕ ብቻ ነው። መሲሑን ሲፈልጉ ነቢያት አልታከቱም፤ አበው ፈጽሞ ዓይናቸው አልፈዘዘም፤ ያመኑ ሴቶች ሙታናቸውን በእምነት ለመቀበል አላመነቱም፤ ካህናት መሥዋዕትን ሲያቀርቡ ፈጽሞ አልተጠየፉም። እንደ ናፈቁት ኖረው፣ እንደ ናፈቁት ሞቱለት። ባያገኙት እንኳ፣ ምሳሌውን አገልግለው ለማለፍ ለቅንጣት እንደ ጉድለት አላሰቡም።

ከእኒህ መካከል፣ በፍጻሜው በመጋዝ ለኹለት ተሰንጥቆ ያለፈው፣ “የብሉይ ኪዳን ደረቅ አዲስ ኪዳን” የተባለውን የትንቢት መጽሐፍ የጻፈው ነቢዩ ኢሳይያስ፣ የመሲሑን መምጣት ትክ ብሎ ከማየትና የሚመጣበትንም ምክንያት ሲናገር፣ በመሲሑ ዘመን በአካል የነበረ እንጂ፣ “ትንቢት ተናጋሪ ብቻ” አይመስልም። የነቢያ ኑሮ በሰይፍ የታጠረና ምቹ እንዳልነበረ እንዲኹ፣ የመሲሑ አመጣጥም ሳቢና አጓጊ አልነበረም፤ እንኳን ከተስፋው ለራቁና በኀጢአት ጨለማ ለሚመላለሱ ይቅርና፣ የሕጉን መጽሐፍ ለጨበጡ፣ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ለነበሩ፣ ለካህናትና ለሕጉ ጸሐፍት መሲሑ አመጣጡ አንዳች የሚናፈቅና የሚስብ ነገር አልነበረውም፤ ምክንያቱም መሲሑ እንደ ሰው ፈቃድ ሰውን ሊያለግል አልመጣምና።

ናፋቂው ነቢይ፣ መሲሑ በቀዳማይ ምጽአቱ ሲመጣ የሚያደርጋቸውን ወይም የመጣበትን ዋና ዋና ዓላማዎች እንዲህ በማለት ይጠቅሳል፤ (ኢሳ. 61፥1-2፤ ሉቃ. 4፥17-19)። መሲሑ በፊተኛ መምጣቱ ምን ያደርጋል?

1.     ለድኾች ወንጌልን ይሰብካል፦ ከመሲሑ አስደናቂ ባሕርያት መካከል፣ ድኾችን እጅግ መውደዱ ነው። ኑሮውንና የሕይወቱን አብዛኛውን ክፍል፣ ድኾችና የተናቁ ሰዎች በሚኖሩበት በገሊላ፣ ከዮርዳኖስ ማዶ ወደ ነበሩት፣ በመገለልና በመረሳት ውስጥ ወዳሉት መሄዱ እጅግ ይደንቃል! ወንጌልን ለእነርሱ ይሰብክ ዘንድ ይገባዋል (ማቴ. 4፥13-16)። እርሱ ራሱ ወደ እነዚህ ሰዎች የመጣበት መንገድ፣ ሳቢና ደም ግባቱ በሚያምር መንገድ አልነበረም፤ ይልቁን ለአርባ ቀንና ሌሊት በመጾም፣ ሰውነቱ እጅግ ዝሎና ደክሞ አንዳች የሚወደድ ነገር ሳይኖረው ነበር።

ድኾችም፤ ጌታን መስማታቸውና መከተላቸው ሌላው እጅግ አስደናቂ ነገር ነው። በርግጥም ዓሳ አጥማጆች፣ አመንዝሮችና ቀራጮች እርሱን እንጂ ማንን ሊመርጡ ይችላሉ?! በርግጥም መሲሑ የድኾች ኹሉ ተስፋና መጠጊያ ነው። በኢየሩሳሌም ልብ ለተዘነጋችው ገሊላና አከባቢዋ፣ ከኢየሱስ በቀር ማን ሊፈልጋቸው ይችላል?! እና መሲሑ ለሃብታሞች አያስፈልግም?! አዎን፤ ለሚወዱትና ለሚታዘዙት ሃብታሞችም ያስፈልጋቸዋል። በግልጥ ቃል ግን፣ ይህን አንዘነጋም፤ አዎን በመንፈስ ድኾች ለኾኑት መሲሑ ያስፈልጋቸዋል፤ (ማቴ. 5፥3)። አዎን፤ በመንፈስ ድኾች ለኾኑ ድኾችና ባለጠጎች የመሲሑ ወንጌል ያስፈልጋቸዋል!

2.    ለታሰሩት መፈታትን፦ ከአካል እስራት ይልቅ፣ የመንፈስና የነፍስ እስራት ጽኑ፤ ከጌታ በቀርም ማንም ሊፈታው አይችልም። ከአዳም ጀምሮ የነበሩት አያሌ ቅዱሳን፣ ሰውን ከእስራት ሊፈቱት አልተቻላቸውም። እስራት ልብን ከሚሰብሩት ነገሮች እጅግ ጠንካራው ነው። እንኳን በጌታ ዘመንና፣ ዛሬም ድረስ እስር ቤቶች እጅግ አሰቃቂ ቦታዎች ናቸው። አካላዊው ይህን ከከፋ፣ የነፍስና የመንፈስ እስራት ምን ያህል ሊከፋ እንደሚችል ማስተዋል አያዳግትም። እንዲህ ያለ እስራትን ከጌታ በቀር ሊያይ የሚችል ማን አለ?! እኔን ጨምሮ ብዙዎቻችን የተፈታነው እንዲህ ካለ እስራት ነው፤ ለኢየሱስ ክብር ይኹንለት! አሜን።

3.    ለታወሩት ማየትን ማወጅ፦ ብርቱ ጨለማ፤ ጨለማ ብቻ አይደለም፤ ዓይንን ያሳውራል። ሰዎች በቂ ብርሃን በሌለበት ስፍራ፣ ለረጅም ጊዜ ቢቀመጡ የማየት ብቃታቸው ይቀንሳል፤ የማየት አቅማቸውም ይጎዳል። ከዚህ የሚከፋ ዓይንን የሚያሳውር ብርቱ ጨለማ አለ፤ የኀጢአት ጨለማ፤ ያለ ማመን ጨለማ፤ ያለ መታዘዝ ጨለማ፤ በዲያብሎስ ፈቃድ ሥር የመኖር ድቅድቅ ጨለማ። በርግጥ መሲሑ፣ “የዕውሮችን ዐይን ይከፍታል፤ ምርኮኞችን ከእስር ቤት፣ በጨለማ የተቀመጡትንም ከወኅኒ ያወጣል" (ኢሳ. 42፥7)።

በኀጢአት ዓለም የሚኖሩ ኹሉ፣ በጨለማ የሚኖሩና የሚመላለሱ ናቸው። ይህን ጨለማ ደግሞ ሊገልጥና ሊገፍፍ የሚችለው መሲሑ ብቻ ነው። የመሲሑ ቀዳማዊ ምጽአቱ ዓላማውም፣ በኀጢአት ጨለማ ለሚርመሰመሱና ለሚመላለሱ ኹሉ፣ ማየት፣ መዳን፣ አርነት ይኾን ዘንድ ነው።

4.    የተጨቈኑትን ነጻ እንዲያወጣ፦ ሰይጣን ሰዎች የመግዛቱ ጥግ እስከ ምን አድርሶት ነበር? ብንል፣ “በአየር ላይ ላሉት መንፈሳውያን ኀይላት ገዥ ለሆነውና አሁንም ለእግዚአብሔር በማይታዘዙት ሰዎች ላይ ለሚሠራው መንፈስ እየታዘዛችሁ ትኖሩ ነበር።" እንዲል (ኤፌ. 2፥2)፣ ሰይጣን መጫወቻውና የራሱ አሻንጉሊቶቹ አድርጎን ሲጫወትብን ኖሮ ሳለ፣ ደግሞም በጭቆናው ሞት ፈርዶብን ሳለ (መዝ. 102፥2)፣ ሊያድነንና ሊቤዠን በቀዳማይ ምጽአቱ ፈጥኖ ደረሰልን።

ዲያብሎስ ስላልፈጠረን በፍቅር ሊገዛን አይችልም፤ ገንዘቦቹ አይደለንምና ፈጽሞ ሊራራልን አይችልም። መሲሑ ግን የእጁ ፍጥረት ነንና በስስ ልቡ ያስብልናል፤ ገንዘቦቹ ነንና ይራራልናል፤ ይወደናል፤ ፍቅሩን በመግለጥ ያድነን ዘንድ በበረት ግርግም በዝቅታ ስፍራ ተወለደ፤ በመስቀል ተሰቀለ፤ ከሙታንም መካከል ተነሣ፤ የምናምነውን ኹላችንን አዳነን፤ አሜን።

5.    “የተወደደችውን የጌታን ዓመት እንዲያውጅ የጌታ ዓመት የተወደደች የተባለችው እርሱ “ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸክሞ፤ በመገረፉ ቁስል ፈውሶን” (1ጴጥ. 2፥23) ብቻ ሳይኾን፣ የብዙዎች ሕሙማንን ድካምና ደዌ በመቀበልና በመሸከምም ነው (ማቴ.8፥16)፤ በእርግጥም ይህን ያየች ነፍስና መንፈስ ከጌታ የተነሳ ዘመኗ የኢዮቤልዩ፤ ዓመቷም የተወደደ ነው። ጌታ ለጠፉ ኃጥአን ደኅነንትንና ወንጌልን የምሥራች ብሎ ሰብኰ፤ ለተጣሉት፣ ከወገን ተገልለው ልባቸው ላዘነና ለተሰበረ የቀረበ አጽናኝ በመኾኑ፣ የራቁትን በፍቅሩና በርኅራኄው በማቅረቡ ዘመኑ የምሕረት፤ ዓመቱ የይቅርታ ተብሎልናል።

ምንም እንኳ ባለመድኃኒቱ ባደገባት በናዝሬት የተናቀ ቢኾንም፣ ለዓለሙ ግን የሚበቃና የተትረፈረፈ መድኃኒት ኾኖአል። በናዝሬት አድማጭና ተቀባይ ባይኖረውም፣ ኃጢአተኝነታቸውን አምነው የቀረቡትን ግን በዘመናት በዕረፍቱና መውደዱ ውስጥ አርፈዋል። የዚህን ሙሉ ማብራሪያ ( http://abenezerteklu.blogspot.com/2014/09/419.html ) በዚህ ሊንክ ገብተው ያንብቡ።

ጸጋና ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉትና በማይጠፋ ፍቅር ከሚወዱት ጋር ኹሉ ይኹን፤ አሜን።

3 comments:

  1. ዘመንህ ይባረክ

    ReplyDelete
  2. ጌታ ኢየሱስ ይባርክህ 💎💎

    ReplyDelete
  3. GOD bless you for sharing Abiny. May the HOLY SPIRIT be your guide and strength for days to come, till your last breath.

    ReplyDelete