Thursday, 8 July 2021

ከፍያለው ቱፋ፤ እግዚአብሔር በምሕረት ያስብህ!

ሃይማኖተኛ ሲታወር፣ ከዓለማዊ ይልቅ ዓመጸኛ እንደሚኾን አውቃለሁ። ትኵረት ለመሳብና ሰውን ለማስከተል፣ እምነቴና መረዳቴ እንዲህ ነው ብሎ መውረድ እንዴት ያጸይፋል?! ጌታችን ኢየሱስ፣ “በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል።” (ማቴ. 11፥22) ብሎ ተአምራት አይተው የካዱትን ኮራዚዮንና ቤተ ሳይዳን በጽኑ እንደ ወቀሰው፣ ከደነደነ አማኝ ይልቅ ያላመነ አሕዛብ ተስፋ እንዳለው በግልጥ ነግሮናል።

ከፍያለው ቱፋ ሆይ፤

1.   “አገልጋይ” ነኝ ብሎ ዘፈንን የሚያደምጥና ዘፋኝን የሚያደንቅ፣ ከሐዋርያት መካከል ማንን ልትጠቅስ ትችል ይኾን?

2.   ዘፋኝ ከ“pastor” በላይ መንፈስ ተሞልቶአል ስትል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘፋኝ ኾኖ፣ ከአገልጋይ በላይ መንፈስ ተሞልቶ አጋንንትን ያወጣ አንድ አገልጋይ ልትጠቅስልኝ ትችላለህን?

3.   የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት ለራስ መጥቀስም ጤናማነት አይደለም። እግዚአብሔር ሉዓላዊ ስለ ኾነ ክፉውንም ጭምር ለክብሩ ይጠቀምበታል። ልክ ናቡከደነጾርን፣ ቂሮስን፣ አርጤክስስን እንደ ተጠቀመው። እግዚአብሔር ሉዓላዊ ኾኖ ክፉውን ለክብሩ ይጠቀምበታል ማለት፣ እኛ ክፉውን እንተባበራለን ማለት አይደለም። በግልጥ ቃል፣ “ለኃጢአት የሞትን እኛ ወደ ፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን?” (ሮሜ 6፥2) ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ እኛ ኀጢአትን ልንጠየፍና ልንጠላ እንጂ በማናቸውም መንገድ ልንተባበረው አልተባለልንም።

4.   ስለ እስራኤል ተዘምሮአልና ለኢትዮጵያ መዝፈን አለብን የሚል ሰባኪ፣ በትክክል የብሉይ ኪዳንና የአዲስ ኪዳንን የኪዳን ዝምድናና ልዩነት የማያውቅ፣ የቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣንና እውነትን በትክክል ያልተረዳ ሰው ንግግር ነው። የቀደመው ኪዳን በኪዳን ተተክቶአል፤ አሮጌው ኪዳን በአዲሱ ኪዳን፣ እስራኤል ዘሥጋ በእግዚአብሔር እስራኤል ተተክቶአል። ዳዊት ስለ ጽዮንና ኢየሩሳሌም የዘመረው፣ በጉ የሚነግሥባትን አማናዊት ጽዮንን አስቦ እንጂ፣ እኛ ለምንኖርበት አገር እንድናቀነቅን አብነት ሊኾን አይደለም።

5.   ድኀ አደግ የምንረዳው የዘፈን ካሴት ሽጠን ነውን? እንኪያስ ቤተሰባቸውን በሴተኛ አዳሪነት ገንዘብ የሚረዱ ትክክል ናቸዋ? እየሰረቁ እየገደሉ ሌላውን የሚረዱ ታድያ ምን አጠፉ? ወይስ “ስለ ምንስ መልካም እንዲመጣ ክፉ አናደርግም? እንዲሁ ይሰድቡናልና አንዳንዱም እንዲሁ እንድንል ይናገራሉና።” (ሮሜ 3፥8) የሚለው ቃል ሐሰት ነውን? ድኃን ስለ መርዳትና ራስን ስለ መቻል ኀጢአት እንሥራን? ነገ መልካም እንዲኾን ዛሬ ኀጢአት እንሥራን?

6.   እግዚአብሔርና ሰይጣን ልዩነታቸው የዐሳብ ነውን? እግዚአብሔር እውን ፖለቲከኛ ኾኖ ነው እኔን ምረጡኝ የሚለው? እግዚአብሔር ምን ሥጋት ኖሮበት ይፖተልካል? “ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።” (ይሁዳ 25) የተባለለትን፣ “ንጉሣችንንና ጌታችንንም ብቻውን ያለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ምነው ካድከው? (ይሁዳ 4)። ዐሳብና ፖለቲካ ሳይኖር በፊት እግዚአብሔር ነበረ፤ እግዚአብሔር ከቶውንም የደጋፊ ስጋት ኖሮበት ምረጡኝ ብሎ አያውቅም፤ ጌታችን እንዳስተማረን፣ “እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤” (ዮሐ. 15፥16)። እግዚአብሔር ማንም ሳይመርጠው ብቻውን ገናናና ታላቅ አምላክ ነው!

ኢትዮጵያን እንደ ኢየሱስ የሚሰብኩ ሃይማኖተኛ “ሰባኪዎች” አይቻለሁ፤ ሰዎች ከእምነት መንገድ፣ ከኢየሱስ ሕይወት እንዴት በቀስታ እንደሚወጡ ማሳያ ከሚኾኑት መካከል፣ እንደ ከፍያለው ቱፋ ያሉቱ ደግሞ፣ “ሃጫሉ ሑንዴሳ በዘፈኑ አጋንንትን ያወጣል!” የሚል የትዕቢት ቃል ሲናገር እንሰማዋለን! ዘፈንንና የራስን ብሔር ማምለክ ፍጻሜው ይኸው ነው! ነገር ግን እንኳን ዘፈንና መዝሙርም እግዚአብሔርን ካላከበረና ቤተ ክርስቲያንን ካላነጸ፣ ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነው! ከፍያለው ቱፋ ሆይ፤ ለዚህ የአደባባይ ዓመጽህ እግዚአብሔር በምሕረት ያስብህ፤ ከክፉ መንደግህ እግዚአብሔር ይገስጽህ፤ አሜን።

5 comments:

  1. አንተን ብሎ ስለ ኢየሱስ ተናጋሪ

    ReplyDelete
  2. እነዚህን ማፈሪያዎች ምን እናድርግ

    ReplyDelete
  3. የለየለት ዘረኛነቱን አሳየን

    ReplyDelete
  4. GOD bless you Abeny. You know this is the fruit of "NEW AGE" "NEW TAUGHT" teachings, May the LORD have mercy on Kefyalew.
    May the SPIRIT be your guide & strength for days to come!!!!!!

    ReplyDelete
  5. ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መሆን እራሱ መታደል መመረጥም ነዉ ሮሜ,12_2 በልባችዉ መታደስ ተለወጡ ነዉ,የሚለዉ,ተሀድሶ,መናፍቅ ወረብ ፀናፅል ከበሮ,,የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ነዉ,,ድሮም,ከዝንብ ማር,እንዴት,ይቀሰማል

    ReplyDelete