Wednesday, 21 March 2018

ታማኝ ባርያ


Please read in PDF

ማኅሌታይ ያሬድ የዓቢይ ጾምን ኹሉንም ሳምንታት ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትና ትምህርት እንዲኹም ማንነት ጋር በማዛመድ ስያሜ ሰጥቷቸዋል፡፡ ከዚህም የተነሣ ይህ አሁን ያለንበት ሳምንት ስያሜ ገብር ሔር ይባላል፤ ትርጉሙም መልካም ባርያ ማለት ነው፡፡ የስሙ ትርጉም የተወሰደው ከማቴ.25፥23 ላይ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ በዚያ ክፍል በመልካምነትና በታማኝነት ስላገለገሉ አገልጋዮች ስለሚሰጠው ታላቅ ሽልማትና ክብር እንዲሁም ደግሞ፣ ላልታመኑት አገልጋዮች እንዴት ያለ ታላቅ ተግሳጽና ዘለፋ እንዲሁም ፍርድ እንደሚያገኛቸው ያስተማረበት ክፍል ነው፡፡
     የተሰጠን መክሊት በአግባቡ መጠቀም እጅግ አስተዋይነት ነው፡፡ መክሊቱ ልዩ ልዩ ሥጦታን የሚያመለክት ነው፤ ሥጦታዎቹ መንፈሳዊም ኾኑ ሥጋዊ ሥጦታዎች፣ የተፈጥሮ ወይም የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች ሊኾኑ ይችላሉ፤ (1ቆሮ.12፥7-11፤ ገላ.5፥22) ራሱ መንፈስ ቅዱስም ለሚያምኑ ኹሉ የተሰጠ ውድና ክቡር ሥጦታ ነው፡፡ ስለዚህም የሁሉ ሥጦታዎቻችን ምንጭ ራሱ እግዚአብሔር አምላክ እንጂ እኛ አይደለንምና በሥጦታዎቻችን ልንመካ አይገባንም፡፡ ከመጀመርያም የሥጦታ የመሰጠት ምክንያቱ ለእኛ ሳይኾን ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ነው፤ እኛማ ከፍጥረታችን እኛ የቁጣ ልጆች እንጂ ምንም መልካም ነገር ያልነበረንን ነን፤ (ኤፌ.2፥3)፡፡ ስለዚህ ታማኝነታችንን መግለጥ የሚገባን በተሰጠን መክሊት ልክ ነው፡፡

    ጌታችን እግዚአብሔር ሥጦታን እንደወደደ ለወደደው ይሰጣል፤ የክርስቶስ መንፈስ አንድ ቢኾንም፣ “የጸጋው ስጦታ ልዩ ልዩ ነው” (1ቆሮ.12፥4)፤ የክርስቶስ መንፈስ ይህንን ልዩ ልዩ ሥጦታና ጸጋ ለተለያዩ ሰዎች በጥቂቱም በብዙም መስጠት ይችላል፡፡ አምስትም፤ ኹለትም፤ አንድም መስጠት መብቱ ነው፤ እርሱ የጸጋ ባለቤት ነውና፡፡ የተሰጠን ሥጦታ “መጠኑ” ምንም ይኹን ምን ሌሎችን እንድናገለግልበትና እንድንጠቀምበት የተሰጠን ነው፡፡ የተሰጠንን ያንኑ መመለስ አይገባንም፤ ይልቁን ብዙ ልናተርፍበት፤ ብዙዎችንም ልናገለግልበት ይገባናል፡፡ ጥቂትም ይኹን ብዙ ተሰጥቶን በተሰጠን ነገር አለማገልገልና ብዙዎችን አለመድረስ ሳያስወቅስ አይቀርም፡፡ ከተቀበልነው “አንዱም ሠላሳ አንዱም ስድሳ አንዱም መቶ ፍሬ” (ማር.4፥20) እንድናፈራ እንጂ አምስት ወይም ኹለት ወይም አንድ የተቀበልነውን ያንኑ እንድንመልስ አልተሰጠንም፡፡
     የታማኝነት መገለጫው የተሰጠን ሥጦታ ማነስና መብዛት አይደለም፤ አበላልጦ መሰጠቱ እኛን የሚመለከት ጉዳይ አይደለም፡፡ የእኛ ድርሻ በተሰጠን ሥጦታ የመጠቀምና ያለመጠቀም ጉዳይ ነው፡፡ ትልቁ ጥያቄ ሊኾን የሚገባው “ምን ያህል ተቀብለናል?” ሳይኾን፣ “በተፈጥሮም ይኹን በሥጦታ በተቀበልነው በማናቸውም ሥጦታና ጸጋ ምን ያህል ተጠቅመናል?” ነው፡፡ አንዳንዶች አንድ ብቻ አይደለም አምስትም ተቀብለው ከመቅበር፣ ካለማካፈል፣ ሌሎችን ካለማገልገል፣ ካለማብዛትና እንዲበረክት ካለማድረግ ፈጽሞ የማይመለሱ ናቸው፡፡ ይህ ከባድ ፍርድን ማስከተሉ አይቀርም፡፡
   በአገራችንም በቤተ መንግሥትም ኾነ በቤተ ክህነት አሁን ባለው ኹኔታ ሥጦታና ጸጋ ቀባሪዎችና አባካኞች በአግባቡ ከሚጠቀሙት ይልቅ ቁጥራቸው የትየለሌ መሆኑን ጥቂት ማስረጃዎችን ማቅረቡ በቂ ይመስላል፡፡ በቤተ ክህነትም በቤተ መንግሥትም የማገልገል ዕድል ገጥሞኛል፤ በቤተ መንግሥት ሳገለግል ያየኋቸው ብዙ ነገሮች ጆሮን ጭው የሚያደርጉ ናቸው፤ ባልተሠራ ትምህርት ቤት ስም እንደተሠራ አድርጎ ሂሳብ ማወራረድና ሚሊዮን ገንዘቦችን ለግል ኪስ ማደለቢያ መውሰድ፣ ምርጥ ዘር ተብሎ የበሰበሰን ድንች ለገበሬ ማቅረብና ገበሬው እንቢ ሲል ከከተማ ዳርቻ ጥሎ ከተማን “በዝንብ ማስወረር”፣ ሌላው አካል የሠራውን መንገድ ልክ ራስ እንደሠሩት አቅርቦ ገንዘብ መውሰድ… እንዲህ እጅግ አሳፋሪ ሥራ የሠሩት ሰዎች ለሕግ እንዲቀርቡ ሲደረግ በጎን ከእነዚህ ወንጀለኞች ጋር መደራረደርና ማስለቀቅ፣ በሥልጣን የሚያንሱትን መክሰስ፣ የመንግሥትን ፖለቲካ ያበላሻሉ በማለትና … በሌሎችም ምክንያቶች መዝገብ ማዘጋትና መጥፋት፣ በእርዳታ የመጣን መድኃኒት፣ እህል፣ … መስረቅና ሸጦ ለራስ ጥቅም ማዋል በሚገባ ያስተዋልኳቸው ናቸው፡፡ ለአገር ታማኝ ያልኾኑ ከፊት ይልቅ በዚህ ዘመንስ አልበዙ ይኾን?
      ቤተ ክህነትም ቢኾን እጅግ በአብዛኛው ከዚህ ጋር እጅግ ተመሳሳይ ነው፤ ለሕዝብ፣ ለገዛ አማኞቻቸው ምንም ግድ የማይሰጣቸው ጥቂት አይደሉም፤ በግ በሥጋም በነፍስም ከስቶ እየሞገገ ለራሳቸው ግን ሰብተው የወዙ በቤተ መንግሥት ብቻ ሳይኾን በመንፈሳዊው ዓለም ያሉ እረኞች ቁጥራቸው ጣሪያ ሳይነካ አይቀርም፡፡ ታማኝነት ከምድራችን ጎድሏል፤ በየትኛውም የሥራ መስክ የማጭበርበር ሕይወት ተንሠራፍቷል፤ ታማኝነት ለሚያየን፣ ልብና ኩላሊት ለሚመረምረው እግዚአብሔር አምላክ ሳይሆን፣ ፊት ለፊታችን ላለው ሰው ብቻ እንደኾነ ግብዛዊ ማንነታችንን ያሳብቅብናል፡፡
    ስንቶቻችን ለገዛ ራሳችን ታማኝ ነን? ከተጣባነው የልማድ ኃጢአት በክርስቶስ የደሙ ጉልበት ለመላቀቅ ስንት ጊዜ ቃል ገብተን ስንት ጊዜ እኛው አፍርሰነው ይኾን? እንድናገለግለውና እንድንጠቅመው ከተጠራነውና መክሊት ከተሰጠን ሕዝብ ጫንቃ ላይ ተቀምጠን አደራ የምንበላ፣ የጋን መብራት የኾንን ስንት ነን? የትዳራችንን ታማኝነት በብዙ ደጋግመን የበላንና የሸረከትን ስንት እንኾን? እግዚአብሔር አምላክ ምድሪቱን ሊጎበኝ፤ በይቅርታ ፊቱን ወደእኛ እንዲመልስ በታማኝነት፣ በንስሐ፣ በክርስቶስ በማመን ፊታችንን ልንመልስ ይገባናል፡፡
    ይህን ያለማድረግ ያስቀጣል፤ አያሸልምምም፡፡ በጥቂቱ መታመን ግን በብዙ ያሸልማል፤ ያውም በሰማያት በእግዚአብሔር አምላክና በመላእክቱ ፊት፡፡ በመክሊቱ ላለመጠቀማችን ምንም ዓይነት ምክንያት ተቀባይነት አይኾነንም፤ ምክንያት መክሊትን ከመቀበር ተካካይ ነው፡፡ ብዙ ተደርጎልን ወይም ተሰጥቶን ምንም ላለማድረግ መወሰናችን ወይም ችላ ማለታችን የተደረግልን መናቅና ለተደረገልን ተገቢውን ክብር አለመስጠት ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ እኛን ለማዳንና በብዙ ለመማርና ይቅር ለማለት በመስቀል ላይ በመንገላታት ታላቁን ነገር አድርጎልን፣ እኛ ለዚያ ፍቅር በመታዘዝ ሕይወታችንን መስጠት ካልቻልን እጅግ ምስኪኖች ነን፡፡ ታማኝነታችንን በመታዘዝ ሊገለጥ ይገባል፡፡ ታማኝ ባርያ ተብላችሁ ወደጌታችሁ ዘላለማዊ ደስታ መግባት ትፈልጋላችሁን? እንግዲህ እርሱ የተናገራችሁን በመውደድ ታዘዙት፡፡ የክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን ጸጋ ይብዛላችሁ፤ አሜን፡፡




1 comment:

  1. ጸጋ ይብዛልህ ተባረክ ወንድም

    ReplyDelete