Thursday, 30 June 2016

ከእረኛህ ጋር ጽና!


ሰርጐ ገቢው ፤
ተመሳስሎ በቀስ አድቢው ፤
የበግ ለምዱን አለስልሶ -
                  አለሳልሶ ፤
የዝማሬ ድምጸት ገርቶ ፤
የስብከቱን ቃና ለምዶ ፤
የጽሑፉን ዝፍቱን ቀብቶ ፤  
በበግ መሐል አንገት ደፍቶ ፤
ተኩላ ክፉ በዚህ ብቻ መቼ ረክቶ?

Sunday, 26 June 2016

ቢረፍድም፥ ለወንጌሉ ደወል ለመደወልና ትውልዱን ለማንቃት አሁንም ዕድል አለን!!!

Please read in PDF


 የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በስምዋ በባለቤትነት የምትመራውን የቴሌቪዥን ሥርጭት ከሰሞኑ ከፍታልናለች፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩም፦
“እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም” (ዮሐ.5፥24)፡፡
የሚለውን ቅዱስ ቃል በማንበብ መክፈቻዊ ንግግር በማድረግ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ወደር የለሽነትና የበላይነት ፍንትው አድርገው ሲናገሩ፥ ፍጥረታት ያለቅዱስ ቃሉ ሕያዋንና ነዋሪዎች መሆን እንደማይቻላቸው በአጽንዖት አስቀምጠዋል፡፡ በዚህ መንፈሳዊ ለዛ ባለው ውብ ንግግራቸውም የቴሌቭዥን ሥርጭቱ መከፈቱን በመባረክ አብሥረዋል፡፡
     በመቀጠል ሊቃነ ጳጳሳትም አጫጭር ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ ንግግር ካደረጉት መካከል ብጹዕ አቡነ ገብርኤል ለዚህ ትልቅ ሥራ “ማርፈዳችንን” ምንም በማይሸነግል ንግግር ተናግረዋል፡፡ እውነታውን ላስተዋለው ካለን አማኝ ቁጥር ብዛትና ካለን አቅም አንጻር እጅግ በጣም ቢረፍድም፥ “ዘግይቶ መከፈቱ በራሱ” እጅግ ደስ የሚያሰኝና ለወንጌሉ ሥርጭት መልካም እድል እንደሆነ እናምናለን፡፡ 

Friday, 24 June 2016

“የ‘ፌስቡክ’ ትውልድ” (ክፍል ሁለት)

3. ስድብና ስም ማጥፋት
    ተሰምተው የማታውቋቸውን ስድቦች ወደፊት ገጽና(Facebook) ሌሎችም ድኅረ ገጻት  ስትመጡ ነፍሳችሁ እስክትጠግብ ልትሰሙ ፣ ልታዩ ትችላላችሁ፡፡ አጅግ የምታከብሩት ሽማግሌ ፣ ባልቴት ፣ ወጣት ፣ ልጅ … ድንገት የስድብ ናዳ ሲወርድበት ታያላችሁ፡፡ ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነው የሃይማኖት መልክ ያላቸው በዚህ ነገር የተጠመዱና የተለከፉ መሆናቸው ነው፡፡
   ስድብ የአንደበት ኃጢአት ነው፡፡ ዲያብሎስ ተሳዳቢ ነው፡፡ ልጆቹም እንዲሁ(ራእ.13፥6)፡፡ ከእግዚአብሔር የሆነ ግን ክፉ ከአንደበቱ አይወጣም (ማቴ.15፥11)፡፡ ከአንደበት የሚወጣ ክፉ ነገር መላ ብልትን ያረክሰዋልና፥ የእግዚአብሔር የሆነ ሰው ስለሚናገረው ይጠነቀቃል፡፡ ይልቁን እንዴት መናገር እንዳለብን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የሞቱ ዝንቦች የተቀመመውን የዘይት ሽቱ ያገሙታል እንዲሁም ትንሽ ስንፍና ጥበብንና ክብርን ያጠፋል” (መክ.10፥1) እንዲል፥ ቃላችን በስንፍና የተመላ እንዳይሆን “ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን” (ቈላ.4፥6) የሚለው ቃል ሊገዛን ይገባል፡፡

Sunday, 19 June 2016

ጰራቅሊጦስ - ሌላ አጽናኛችን


Please read in PDF

     “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤” (ዮሐ.14፥15-16)
     መንፈስ ቅዱስ ለሰው ልጆች የሚሰጥ የአብ ውብና ድንቅ ስጦታ መሆኑን በመጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመርያ ጊዜ የምንመለከትበት ክፍል ይህ ከላይ ያየነው ነው፡፡ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የመሰጠቱ ተስፋ ከኢየሱስ መሔድ ወይም ማረግ በኋላና እርሱም በዚያ ሆኖ በሚለምነው ልመና እንደሆነ፥ “እኔም አብን እለምናለሁ ... ” የሚለውን የጌታ ቃል አብነት በማድረግ ቅዱስ ያሬድ በድጓው፥ “ ... ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የእኔ ስለሆኑት ምሕረትን ወደምለምንበት ወደአባቴ ወደሰማይ ዐርጋለሁ አላቸው” በማለት በገጽ.113 ሲያሰፍር፥ እንዲሁም “ ... ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደአባቴ ዐርጋለሁ ስለእናንተ እለምነዋለሁ አላቸው” (ድጓ ገጽ 291) በማለት በግልጥ ይደግመዋል፡፡

Friday, 17 June 2016

ቤተ ክርስቲያን ሆይ! መንፈስ ቅዱስ ያጽናናሽ ፤ ኢትዮጲያንና ኤርትራን ደግሞ ጌታ ይማራችሁ!!!


ሰውን በማረድ ፣ በማዋረድ ፣ በመስደብ ፣ በማንጓጠጥ ፣ በማሰቃየት ፣ በማረድ … የሚረኩና የሚደሰቱ ከሥነ ምግባር የወረዱ “ሃይማኖት ለበስ” የሰይጣን ደቀ መዛሙርት እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ቤተ ክርስቲያን በግ ሳለች በተኩላ መካከል የተላከች ታማኝ መልእክተኛ ናትና እኒህን ልትታገሳቸው ፤ ወንጌልን ተግታ ልትመሰክርላቸው ይገባታል፡፡ አሠማሪው ጌታ በክፋትና በነውር በሚጨክነው ተኩላና የተኩላ ዓለም ላይ ቤተ ክርስቲያን ለእውነትና ለዘለዓለም ሕይወት እንድትጨክን የኃይልን መንፈስ ሰጥቷታል (ኢሳ.11፥3)
     “እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን” እንደሚለው፥ እግዚአብሔር የታመኑና የጽድቅ ምስከር የሆኑ ልጆቹን ከሞት በማዳን ፤ ከአንበሳ መንጋጋ በማላቀቅ ፤ ከሰይፍ ስለት በማስመለጥ ፤ በወኅኒ ከመጋዝ በመታደግ … ብቻ አይከብርም፡፡ እንዲሞቱ ፣ በአንበሳ እንዲበሉ ፣ በሰይፍ ስለት እንዲቀሉ ፣ በወኅኒ እንዲጋዙም በመፍቀድና በመውደድ ክብሩን ይገልጣል፡፡ ክርስትና መስቀል የመሸከም መንገድ እንደመሆኑ መጠን ለእውነተኛው የጌታ ወንጌል ፈጽሞ እንድንጨክን ተጠርተናል፡፡

Friday, 10 June 2016

ባታርግ ኖሮ … (እንኳን አረግህ!)

Please read in PDF


ሞትን ድል ነስተህ
ሲዖልን ረግጠህ
የገሃነምን፥ ደጆች አፍርሰህ
ላመኑህ ልጆች፥ ተስፋውን ሰጥተህ …
ባታርግ ኖሮ …

Monday, 6 June 2016

ከቤተ መንግሥቱ ፈተና መሰረቅ ይልቅ የቤተ ክህነቱ ሲኖዶሳውያን አንዳንድ ጳጳሳት ድርጊት ያሳፍራል!!! (የመጨረሻው ክፍል)


  

 “ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። … በእናንተ ዘንድ ጦርና ጠብ ከወዴት ይመጣሉ? በብልቶቻችሁ ውስጥ ከሚዋጉ ከእነዚህ ከምቾቶቻችሁ አይደሉምን? … ” (ያዕ.3፥16 ፤ 4፥1-2)

     እንደማንኛውም ሰው ስናስብ፥ በአስተዳደር ጉዳይ መጣላት ሊኖር ይችላል፡፡ መጋጨት ስላለም ሁከት ፣ ጦርና ጠብ ውጭ ለሚያየው መገለጫ ሆነው ይታያሉ፡፡ ለመንፈሳዊ ሰው ግን የጦርና ጠብ መነሾ ዋና ምክንያቱን ቅዱስ ያዕቆብ እንደነገረን ስናስተውል፥ በብልቶቻችን ውስጥ ከሚዋጉ ምቾቶቻችን እንደሆነ በግልጥ ያስቀምጣል፡፡ ምቾት ብርቱ ስሜት ፤ ጠንካራ ውጊያ ፤ አደገኛ ምኞት ፤ ክፉ ቅንአትንም ጭምር ያሳያል፡፡ የዚህም መነሾው ሥፍራው ልብ ነው እንጂ የትም አይደለም፡፡ በልብ ብርቱ ሰልፍ አለ ፤ ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ፥ “ ሮሜ.7
   በዚህ ሳምንት በቅዱስ ሲኖዶስ የተፈጠሩትን ችግሮች ቀለል አድርጐ ማለፍ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ እግዚአብሔር ምድሪቱን ያለ ምስክር አይተውምና (ሐዋ.14፥17)፥ መጽሐፍ ቅዱስን ገልጦ እውነታውን በማንሳት መምከርና መገሰጽ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር ልብንና የመንገድን ቅንነት እንጂ ዕድሜን ወይም ታላቅ መሆንን ብቻ እንደማያይ ታላቁ ባለበት አቤልን ፣ ዮሴፍን ፣ ኤፍሬምን መምረጡን ፤ በእድሜ የሸመገሉቱ ዔሊና ሌሎች ካህናት ባሉበት ሕጻኑን ሳሙኤልን ፣ እንዲሁም [ወጣቱን] ሕጻኑን ኤርምያስን እንደመረጠው መጽሐፍ ቅዱስ በሚገባ ይነግረናል፡፡ 

Thursday, 2 June 2016

ከቤተ መንግሥቱ ፈተና መሰረቅ ይልቅ የቤተ ክህነቱ ሲኖዶሳውያን አንዳንድ ጳጳሳት ድርጊት ያሳፍራል!!! (ክፍል አንድ)


Please read in PDF
   የፍጥረትን አፈጣጠር የሚነግረን ቅዱስ ሙሴ የኦሪቱን መጽሐፍ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት መጻፍ ሲጀምር፥ “…ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ …” (ዘፍ.1፥2) ይለናል፡፡ እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን እስኪል ድረስ፥ ጨለማው በምድር ሁሉ ላይ ሰልጥኗል ፤ ማለትም፥ ምድር ለሥራ የማትመችና የማትታይ ፣ ቅርጽ አልባና ባዶ ፣ ሙሉ ለሙሉ በጨለማ የተወረሰች ነበረ ማለት ነው፡፡ “እግዚአብሔር ብርሃን ይሁን” ባለ ጊዜ ግን፥ ለሥራ የማትመቸዋ ምድር ታየች ፣ ተገለጠች ፣ ሕልውናዋ ታወቀ ፤ ቅርጽ አልባና ባዶ የነበረችው አዝርዕትን አትክልትን ዕፅዋትን ልታበቅል ዝግጁ ሆነች ፤ አስደሳችና ውብ ውበትን ለበሰች ማለት ነው፡፡ ጨለማዋን የእግዚአብሔር ብርሃን ገልጦላታልና፡፡
    ለተፈጠረችው ምድር ጨለማ ቀድሞ ሰልጥኖባት እንደነበረው እንዲሁ፥ ዋናው ብርሃን ዘእምብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ሊሰለጥንና በሕይወታችን ብርሃንን ከማብራቱ በፊት የኃጢአት ጨለማ በልባችን ለዘመናት ሰልጥኖ ነበር፡፡ ምድር ስትፈጠር ብርሃን ይሁን ያለው እግዚአብሔር ወልድ፥ አሁንም በአዲስ ኪዳን ልደት፥ “በክርስቶስ ፊት የእግዚአብሔርን የክብሩን እውቀት ብርሃን እንዲሰጥ በልባችን ውስጥ የበራ፦ በጨለማ ብርሃን ይብራ ያለ እግዚአብሔር ነውና” (2ቆሮ.4፥6) በማለት፥ በዚህ ቃል ቀድሞ ምድር ሕልውናዋ እንደተገለጠ፥ አሁንም ለእኛ በጽድቅ መኖርና መገለጥ ክርስቶስ መሠረትና ዋናችን ሆኖልናል፡፡ እርሱ በደሙ ቤዛነት ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን አውጥቶናልና፡፡