አውቃለሁ ፤ ክርስትና የመገለጥ ጉዳይ
እንጂ የእውቀት ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህን የምለውም በግኖስቲካዊ አቋም ዕውቀትን ከሚያመልኩ ጐን በመሰለፍ ወይም አምርረው ከሚጠሉትም
ጐራ ራሴን በመደመር አይደለም፡፡ ክርስትና በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የሆነውን ቤዛነትና ውጅት ማመንና ይህንንም መንፈስ ቅዱስ በፍጹም
መገለጥ የሚያስተምረን ሕያው እውነት ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ላመኑትና ለተቀበሉት ብቻ ነው (ዮሐ.1፥12)፡፡
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን አምኖ መቀበል ማለት፥ በሕይወታችን ፣
በትዳራችን ፣ በሥራችን ፣ በሁለንተናችን እርሱን ማመንና በተገለጠ ቅዱስ ሕይወት እርሱን ጌታችንን በኑሮአችን መመስከር ማለት ነው፡፡
ጌታ ኢየሱስን ለማመንና ለመቀበልም ሆነ ለማገልገል ፍጹም መሞት ያስፈልጋል፡፡ በትክክል ሳንሞት በትክክል መኖር አንችልም ፤ በትክክል
ሳንኖርም በትክክል መሞት አንችልም፡፡ መስቀል ባልፈተነው ጉብዝና እንደመኖር ባዶ ክርስትና የለም፡፡