Tuesday, 3 September 2013

ልከኛው ጳውሎስ - 2

  Please read in PDF     
    ከአዲስ ኪዳን አገልጋዮች የተደነቀ የንግግር ችሎታ የሌለውና ነገር አቅንቶ መናገር የማይችለው (ከብሉይ ኪዳኑ ጥልቅ አዋቂና ልዩ ተናጋሪው አጵሎስ አንጻር ሲታይ) በጸጋው ያገለገለ ሐዋርያ እንደጳውሎስ ያለ አይመስልም፡፡ ጸጋውን፣ አለዋጋ የተሰጠውን ሐብትና መልካም ስጦታም አስቦ በሥጋ ለመመካት ለአንዲት ሰዐት በመዘናጋት ያዋለ አይደለም፡፡
      የጌታ የትንሣዔውን ኃይል ለእርሱ እንዴት እንደተገለጠ ሲናገር፥ " …  ከሁሉም በኋላ እንደ ጭንጋፍ ለምሆን ለእኔ ደግሞ ታየኝ።እኔ ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ ነኝና፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ስላሳደድሁ ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም ከሁላቸው ይልቅ ግን ደከምሁ፥ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም(1ቆሮ.15÷8-11)፡፡

     ደግሞም፦ " እንደ ኃይሉ ሥራ እንደ ተሰጠኝም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ስጦታ መጠን የወንጌል አገልጋይ ሆንሁለ፡፡ ፍለጋ የሌለውን የክርስቶስን ባለ ጠግነት ለአሕዛብ እሰብክ ዘንድ፥ ሁሉንም በፈጠረው በእግዚአብሔር ከዘላለም የተሰወረው የምሥጢር ሥርዓት ምን እንደሆነ ለሁሉ እገልጥ ዘንድ ይህ ጸጋ ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ ለማንስ ለኔ ተሰጠ፤…"(ኤፌ.3÷7-9)
     አሁንም "ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ።"(ፊሊ.4÷13)፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ በልዩ አጠራሩ እርሱን የጠራውና (ሐዋ.9÷15-17)፣ጥሪው በቤተክርስቲያን ታሪክ እጅግ የተወደደና አስፈላጊ መሆኑን በሐዋርያት ሥራ ላይ ብቻ ሦስት ጊዜ ተጠቅሶም እናገኛለን፤ (ሐዋ.9÷1-322÷3-1626÷4-18)፡፡ ይህ ልከኛና ውድ ሐዋርያ መጠራቱንም ሆነ አገልግሎቱን ግን ለቅጽበት እንኳ በእርሱ ብቃት ወይም ቅድስና እንዳደረገ በፍጹም አልጠቀሰም፡፡
     በአገልግሎቱና በጉዞው ሁሉ ኃይልና ጸጋን የሰጠው ክርስቶስ ኢየሱስ ብቻ እንደሆነ ደግሞ ደጋግሞ ይገልጠዋል፡፡ ይህ እንደዘመኑ የስብከት አባባል ትህትና አይደለም፡፡ የጳውሎስ የትምክህት ድፍረቱ  ብቃትና ቅድስናው በክርስቶስ ጸጋ በኃይሉም ችሎት ፊት እንዲሁ እንደተወደደና እንደተመረጠ ማሰቡና ማመኑ ነው፡፡
     ሁሉን መቻያው ብቃቱና የራሱ ፍጽምና ሳይሆን ኃይልን በሚሰጠው በክርስቶስ ልቡን መደገፉ ነው፡፡ በአንድ ወቅት እንዲህ ሆነ፤ በኤፌሶን ላሉ የቤተ ክርስቲያን ባላደራዎች የተወደደ ምክርን ሰጥቶ አብሮ በእንባ ተንበርክኮ ከጸለየ በኋላ ፊቱን ወደኢየሩሳሌም አቀና፤ (ሐዋ.20÷17-38)፡፡
    ይህ የተወደደ ልከኛ ሐዋርያ ወደኢየሩሳሌም ሲመጣ "እሰይ መምህራችን መጣህልን!" የሚል ድምጽ እንደሌለ የተረዱ ሁለት ወገኖች
1.     ደቀ መዛሙርት በመንፈስ ተረድተው ወደኢየሩሳሌም እንዳይወጣ (ሐዋ.21÷5)
2.     የአጋቦስን ትንቢት የሰሙ እነሉቃስም (ሐዋ.21÷12)
እንዳይወጣ አጥብቀው በእንባ ለመኑት፡፡ በጣም በሚደንቅ ሁኔታ ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቶስን ስለመረጠ ብቻ የገዛ ወገኖቹ እንኳ ጠላት ሆነው ተነስተውበታል፡፡ እስጢፋኖስን ሲገድል ያልጠሉት ዛሬ ሰዎችን ከሞት ወደሕይወት በክርስቶስ ወንጌልና ጸጋ ስለመለሰ ጠልተውታል፡፡ በስካርና በዘፈን ስንኖር ብዙ ወዳጅ አለን፥ ወንጌል አምነን ኢየሱስ፤ ኢየሱስ ማለት ስንጀምር ግን ኩርፊያና ሐሜቱ ጥላቻና ስደቱ ከጎናችን ካለው ባልንጀራና ጎበዝ ይጀምራል፡፡ በዚህ አንዳች አትደነቁ፡፡
      ብዙም ተቀባይ እንደሌለው ቢያውቅም፥ ይህ ብርቱ ሐዋርያ የጨከነለትን ጌታ በመታመን ይጓዛል፡፡ ብዙ ተቃዋሚዎች ከፊቱ አሉ ግን የሚጋርደውን የክርስቶስን ደም ያያል፣ የተረጋገጠ መከራ እንዳለ ያውቃል ግን የኃይሉና የጸጋው ችሎት ነገርን ለበጎ እንደሚያደርግ ያውቃል፣ብዙዎች በእርሱ ጉዳይ(ወዳጆቹ ሳይቀር) ይወዛገባሉ እርሱ ግን ለውዱ ኢየሱስ የታመነ የፈቃድ ባርያ ነው፡፡በብቃቱና በቅድስናው ሳይሆን በጌታው የሚመካ ትጉህ ሎሌ ነው፡፡
     ዛሬ መድረክ ላይ ከሚሰብኩ አገልጋዮች መካከል አብዛኛዎቹ የራሳቸውን ጥንካሬና ቅድስና፣ብቃትና ዕውቀት ነው በደረቅ ወዝ የሚሰብኩን፡፡ የትልቁን ጌታ ኃይልና ችሎት ወዴት ረሱት አንዳንዶች ደግሞ ፈጽሞ ራሳቸውን ይጥላሉ? በሁሉን ቻዩ ክርስቶስ ሁሉን እንደምንችል አያስረግጡልንም፡፡ እባካችሁ አገልጋዮች! ከሁለቱም ውጡና የክርስቶስን ጽድቅ አጉልታችሁ አሳዩን፡፡
    ልከኛው ጳውሎስ ወደኢየሩሳሌም ሲመጣ ነገር ተለውጧል፡፡ሉቃስ ሲዘግብ "ወደ ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን"(ሐዋ.21÷17) በጉዞው የወንጌሉ መሪ የኢየሱስ መንፈስ ከፊት ቀድሟል፡፡ ስለዚህም ይህ ሐዋርያ ወደኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ፥ " … ሰላምታም ካቀረበላቸው በኋላ በእርሱ ማገልገል እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን በእያንዳንዱ ተረከላቸው፡፡እነርሱም በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ"(ሐዋ.21÷20)፡፡ ደካማው ሐዋርያ እንዲሁ በገነነለት ጸጋ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ አደረገ፡፡ ልከኛ አገልጋይ የአገልግሎቱ ቀስት ሰው ሁሉ ፍጥረትም ሳይቀር ወደጌታ ኢየሱስ እንዲያመራ አድርጎ ያገለግላል፡፡
   እንኪያስ ከጸጋ በታች ራሱን እንዴት ዝቅ ዝቅ እንዳደረገ እዩ፡፡ በራስ ጾምና ጸሎት፣ ምጽዋትና አገልግሎት የምትታበዩ እንግዲህ ንቁ፡፡ ያ በትልቅ ጸጋ የተሾመ ሐዋርያ እንዲህ አለ፡፡ እኛም አብረን እንዲህ እንበል፡፡
"እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ለሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ አሜን፡፡  




No comments:

Post a Comment