በአለማችን ላይ እጅግ
ታላላቅ ከሆኑ ችግሮች መካከል የመሪ እጦት የቀዳሚነቱን ሥፍራ ከሚይዙት አንዱ ነው፡፡ አለቃነት (አለ-ዕቃ ከመሆን ይሰውራችሁና!) ሁሉም የሚመኘውና አብዛኛው ሆኖ
ቢያገኘው የሚደሰትበት ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ወደብዙ ቢሮዎች ጎራ ያልን እንደሆነ ቅን ፍትህና መፍትሔ ሳይሆን በቅጥ ያጣ የጉበኝነት
አዘቅት ውስጥ የተዋጠን አሰራር አይተን ለመትፋት የሰው ምክር አንሻም፡፡
መሪነትን በተመለከተ ትልቁ አብነት ልዑል አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡
እርሱ በምሪቱና በመግቦቱ ውስጥ አደላዳይ ሆኖ ለጻድቁና ለኃጥዑ እኩል ፀሐይ ዝናብና ነፋስን … ይሰጣል፡፡እውነተኛ መሪ ነውና ሳያበላልጥ
ፍጥረቱን እኩል ይወዳል፡፡ከተፈጥሮ እውቀት እንኳ አንዳች ሳያጓድል ጥበብንና ማስተዋልን አብዝቶ ያጎናጽፈዋል፡፡
የተረጋጋና ሰላማዊ ሥርወ መንግስትን መመስረት የሚቻለው መሪዎች ለተፈጥሮ
ህግና ለህሊናቸው መገዛት እንዲችሉ ሲቀረጹ ነው፡፡የቅን ፈራጅ መንግስት መሰረቱ ቅን መሪዎች ናቸው፡፡ መሪዎች ለጉበኝነትና ለሴሰኝነት
ዙፋናቸውን አሳልፈው በሰጡ ቁጥር አጋንንት የጨበጡትን በትር በመጠቀም
ህዝብን ያስጨንቃሉ ድኻ አደጉንም ይበድላሉ፡፡
መልካምና ቅን መሪዎች ያመኑ ክርስቲያን ባይሆኑ እንኳ ለተፈጥሮ ህግና
ለህሊናቸው የታመኑ ከሆኑ በመልካም ስብዕና ታግዘው ለህዝቡ የሚሆነውን
ነገር አሻግረው ቀድመው ያዩለታል፡፡ከሥጋ ድካሙም ያሳርፉታል፡፡ እነማህተመ ጋንዲ ክርስቲያን አልነበሩም ነገር ግን ክርስቲያን ነን
ብለው ህዝብና ወገናቸውን በትዕዛዝ ከማረድ እስከማሳረድ ከደረሱ ከሐገራችንና ከአለማችን መሪዎች በተወደደ ስብዕና እጅግ የላቁ ተወዳጆች
ነበሩ፡፡