Monday, 29 July 2013

በልክ የሚገስጹንን አስነሳልን

     Please read in PDF:- belik yemigesitsunin asnesalin
            ሁል ጊዜ ጣፋጭ ነገሮችን መመገብ ጤናን የሚያናጋ መሆኑን ከመረጋገጡም በላይ፥ በተለይ ወጣትነትንየዘለሉ እንዳይጠቀሙም በሕክምና ባለሙያዎች ሲመከር እንደሰማሁት፥ ተመካሪዎቹም ተጠንቅቀው ሲርቁ ደጋግሜ አይቻለሁ፡፡ ይህ ማለት ሰውነታችን እየጨመረ በሄደ ቁጥር ኮስተር ወደሚያደርጉና ጣፋጭነታቸው ወዳልበዛ ነገሮች መቅረብና መውደድ መጀመር መቻል አለበት ማለት ነው፡፡ ይህንን ወደሕይወት ትርጉም  ስናመጣው ጣፋጭ የሆነን ነገር ሁል ጊዜ መሻት፣ ቀለል ያሉ ነገሮችን ብቻ መርጦ መኖር፣ ሁል ጊዜ እሽሩሩ እየተባባሉና በምክር እያባበሉ መጓዝ፣ ልምምጥና ቁልምጫ፤ ወተት እንደሚጋት ሕጻን መጋት፣ እየተመሰጋገኑ፤ እየተንቆለጳጰሱ  … ለመጓዝ ማሰብ ፈጽሞ የማይቻል መሆኑን ነው፡፡ በሕይወት ጉዞ ምክር አስፈላጊ የመሆኑን ያህል የሚመረውም ተግሳጽ የዚያኑ ያህል ያስፈልገናል፡፡

     የሚኮመጥጡና የሚያቃጥሉ ነገሮች (ምሳሌ፦ ሎሚ ፣ ቃርያ … ) ጥሩ የማይመስሉትን ያህል ለሥጋ ደኅንነታችን አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ የሚኮመጥጡ፤ የሚያቃጥሉ፤ የሚመሩ የሚመስሉ የጌታ የተግሳጽ ቃሎችም በሕይወት ጉዞ በጣም አስፈላጊዎች ብቻ ሳይሆኑ፥ እንዲህ ያሉ አገልጋዮችንም ጌታ እንዲያስነሳልን መጸለይም ይገባናል፡፡ እንደኤርምያስና ኤልያስ ያሉ የተግሳጽ ነቢያት እንደጳውሎስም ያሉ በልክ የሚገስጹ ወንጌላውያን ዛሬም ያስፈልጉናል፡፡
     በድላችኋል አልቅሱ፤ አጥፍታችኋል ተመለሱ፣ ነውራችሁ ተገልጧል በንስሐ ሸፍኑ፣ ጎበዛዝት በሴሰኝነትና ገንዘብን በመመውደድ፤ ወጣቶቹ በዝሙትና በርኩሰት፤ ዳኞቹ በጉበኝነትና ለድኻው ባለመፍረድ፤ ጳጳሳቱ ለመንጋው ባለመራራትና ለውግዘትና ለማባረር ብቻ በመሰብሰብ፣ ካህናቱ ለልማድ አገልግሎት እንጂ ለሕይወት ጉባኤ ደወል አትደውሉም፤ ሰባክያኑ ለትልልቅ ጉባኤ እንጂ ለጠፋው አንድ በግ ግድ የላችሁም፣ ምዕመናኑ ሐሰተኞችን ሸሽጋችሁ እየቀለባችሁ እውነተኞችን ግን ታሳድዳላችሁ … ብሎ ቆርጦ የሚናገር ብርቱ የተግሳጽ አገልጋይ ያስፈልገናል፡፡
     የትዳሩ ድንበር ተጥሷል፣ የቅድስናውም ካባ ወልቋል የሚል መጥምቀ መለኰት፣ መሪዎቹ ምክራችሁ ከጠንቋይ ጋር ሆኖ ሕዝብ እየበደላችሁ ነው የሚል ኤልያስ፣ አገልጋይ የእግዚአብሔር ሰው መሳይ ግና ንጉሥ ሆነህ የድኃውን በግና ሚስት የምትቀማ ሌባና ቀማኛ ነህ የሚል ናታን፣ ለታይታና አቦ አቦ ተብላችሁ የከበሬታ ወንበር ለማግኘት እንጂ መንጋውን ወደበረት ልታስገቡ አልተቀመጣችሁም የሚል እንደጌታ ኢየሱስ ያለ ልከኛ አገልጋይ፣ በእናንተ መካከል ያለው ዝሙት በአህዛብ ዘንድ እንኳ የለም የሚል ጳውሎስ ዛሬም ለመድራችን ፤ ዛሬም ለቤተ ክርስቲያንችን ያስፈልጋታል፡፡
      በአገራችንም ሆነ በቤተ ክርስቲያናችን የሕዝብን ልብ ለመመለስና ራሱን እንዲመለከት ለማድረግ የሚገስጹ ሰዎች አይቀጡ ቅጣ ሲቀጡ፣ ከዕዝብ ልብም እንዲወጡ ሲወገዙ በታሪክ ካነበብነው ባሻገር ዛሬም በአይናችን እያየን ነው፡፡ እኛ አገር የሚገስጹ ሰዎች እንደግትር ፣ ልክ ነኝ ባይ፣ የሰው ምክር የማይቀበሉ ፣ አሉታዊውን ነገር ብቻ እንደሚያዩ ሰዎች ይቆጠራሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ደግሞ በተለይ የበላዮቻቸውን የሚወቅሱና የሚገስጹ ከሆኑ ሕግ እንዳፈረሱ ቀኖና እንደጣሱ ከመቆጠሩም አልፎ ክህነት ያለው ከሆነ ከክህነቱም ሊሻር የሚችልበት አጋጣሚዎች እንደነበሩ ታዝበናል፡፡ ስለዚህም እርከን ተሰርቶለት ዲያቆን ቄስን፣ ቄስም ጳጳስን፣ ጳጳስም ፓትርያርክን ለመገሰጽ እንዳይቻል ውኃ ቁልቁል ብቻ እንዲፈስ ሲደረግ እናያለን፡፡ ብዙ ጊዜም እውነትን በተግሳጽ መልክ የሚናገሩ ሰዎች የሚታዩት እንደክፉና መልካምን ፈጽሞ ማሰብ እንደማይችሉ ሰዎች ነው፡፡ እውነታው ግን ተገላቢጦሽ ነው፡፡
       ቤተ ክርስቲያን እውነትን በምክር ቃል ብቻ ሳይሆን በተግሳጽ መልክ የሚናገሩትን በመንፈስ ቅዱስ ጉልበትና ገላጭነት ማፍራት ካልቻለች ጥፋትን በራሷ ላይ ታውጃለች፡፡ በልክ የሚወቅሱና የሚገስጹ ከሌሉባት ከምህረትና ከንስሐ ይልቅ በአልንካሀህ አትንካኝ ለብታ ሕይወት ትዋጣላች፡፡ ለሚያድግ ሕጻን ሁልጊዜ ወተት አይመከርም፤ ባደገበትና በደረሰበት የዕድገት መጠን ሌላ አቅሙን ያገናዘበ ምግብ ያስፈልገዋል፡፡ በደሙ ለምልማ በመንፈስ ቅዱስ ለምታፈራና ለምታድግ ቤተ ክርስቲያን ወተት የምክር ቃል ብቻ ሳይሆን ባደገችበት መጠን ልክ ተግሳጽም ያስፈልጋታል፡፡
     እናንተ “ታላላቆች” ሆይ! “ታናናሾች” በቅንነትና በእውነት በገሰጿችሁ ጊዜ አትቆጡ፡፡ ይልቁን ከበደል አትጠሩምና ራሳችሁን በመመርመር ንስሐ ግቡ ፤ በደሙም ታጠቡ ፤ የጽድቁንም መንፈስ እንደደሸማ ተጐናጸፉ፡፡በፊቱም ያለሐፍረት ትንጓደዱ ዘንድ፡፡
“የተገለጠ ዘለፋ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል” (ምሳ.27፥5)
ጌታ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! በልክ ለእውነትና ለጽድቅ እንድንነቃ የሚገስጹንን አስነሳልን፡፡ አሜን፡፡

3 comments:

  1. God bless you

    ReplyDelete
  2. Your article is amazing. God bless you

    ReplyDelete
  3. Hi do you have books?if you have can u tell me the title of UR books PS I want read more.PS when u posted UR articles PS try to dig deeply.

    ReplyDelete