በመጽሐፍ ቅዱስ ካልተጻፉ ነገር ግን እንደተጻፉ ተደርገው በየመድረኩ ከሚጠቀሱልን ጥቅሶች መካከል አንዱና ዋናው ጥቅስ ቅዱስ ጳውሎስ ለቅዱስ ጢሞቴዎስ የጻፈው “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋ ጅቶልኛል፥ …” (2ጢሞ.4÷7) የሚለው ቃል ነው፡፡
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በህይወት ዘመናቸው በዙርያቸው ካሉትና ከሩቁ ብዙ ስድብ ፣ነቀፌታንና ትችትን የጠገቡ አባት ናቸው፡፡እንዳለመታደል እነዚያ ይጠሏቸውና በድብቅ በስድብ ይዘምቱባቸው የነበሩት ሰዎች ቅዱስ ፓትርያርኩ በቁም ሳሉ ያልተናገሩትን ሲሞቱ ቁጣቸውን፣ ተግሳጻቸውን፣ ምክራቸውን ወጣ ወጣ ሲያደርጉ አይተናል፡፡ (በእርግጥ እሳቸውም ሰው ናቸውና ይደክማሉ፤ደክመውም ይዝላሉ፡፡ ስህተት አይቶ ከመርገም፦ እንዲመለሱ ፣እንዲታነጹ ያኔውኑ ነበር በግልጥ መግለጡ … ሳይመክሩና መንገድ ሳያሳዩ ቁጣ እንዴት ያለ ስንፍና ነው?) ወደሐሳቤ ልመለስ፡፡
እሳቸው ባረፉ ሳምንት በ“ታላቁ” የአራት ኪሎው የሥላሴ ካቴድራል ላይ የተለጠፈው “ትልቅ ስቲከር” እንዲህ ይላል፦
“መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫዬን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን
ጠብቄአለሁ፤ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥” (2ጢሞ.4÷7)፡፡
ምናልባት እሳቸው ናቸው የጻፉት ወይም የፊደል ግድፈት ነው እንዳንል በየትኛውም ቤተ ክርስቲያን ጀርባ ዘወር ብላችሁ የተጻፉ የመቃብር ላይ የዚህን ክፍል ጽህፈቶች ብትመለከቱ ተመሳሳዩን ለማየት አትቸገሩም፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ “ሃይማኖትን ጠብቄያለሁ” የሚለውን ቃል ጭምር “ሃይማኖቴን ጠብቄያለሁ” ሲሉም ይደመጣሉ፡፡ (የእኔ ብቻ ለማለት ይሆን ክርስትናውን?)
ይህን ተመልክተን በመጨረሻ የምንደርስበት ድምዳሜ ከታላቁ እስከታናሹ ፣ከሰባኪው እስከተሰባኪው … ቃሉን በህይወት ከመተርጎም ባሻገር በንባቡ እንኳ ያለማስተዋል ከባድ ችግር እንዳለብን ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ልጁ ቅዱስ ጢሞቴዎስን በብዙ ምስክር ፊት የሰማውን ቃል እንዲመሰክርና መከራን በመቀበል ከሙታን የተነሳውን፣ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በማሰብ በትጋት እንዲያገለግል ሊመክረው ከተጠቀመበት ምሳሌዎች አንዱ ሩጫ ነው፡፡(1ጢሞ.2÷2-8)፡፡