አንድ ሰው
ከወንድሙ ጋር ተጣልቶ ሳይታረቅ ለጸሎት ወደ እግዚአብ ሔር
ቢቀርብ፣ በራሱ የቀረቀረውን በር መልሶ የማንኳኳት ሥራን ነው የሚሠራው፤ ይህ ደግሞ ከንቱ ልፋትና ድካም ነው። በጠብና በቅያሜ
የሚኖር ሰውም ኾነ ቤተክርስቲያን ጸሎት የሚሰማውን የሰማይ ደጅና በርን የዘጋው ራሱ በራሱ ላይ ነው። ይቅር ለመባል፣ ይቅር ማለት
የሚቀድም ከኾነ፣ ይቅር አልልም በማለታችን ይቅርታችንን የገፋነው እኛው እንጂ ይቅር ባዩ ጌታ አይደለም። በጠብና በበቀል፣ በጥላቻም
መኖር ጸሎትንና በእግዚአብሔር ፊት የምናደርገውን ማናቸውንም “መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ያረክሳል”። ጌታችን ኢየሱስ ለዚህ ነው፦ “ስለዚህ
መባህን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር በምታቀርብበት ጊዜ ወንድምህ የተቀየመብህ ነገር መኖሩ ትዝ ቢልህ፣ መባህን በዚያው በመሠዊያው
ፊት ተወው፤ በመጀመርያ ሄደህ ከወንድምህ ጋር ተስማማ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን ለእግዚአብሔር አቅርብ” (ማቴ. 5፥23-24)
(ዐዲሱ መደበኛ ትርጉም) በማለት፣ ወንድምን አለመቆጣት፣ አለመሳደብ፣ አለመራገም፣ አለመናቅ፣ አለመግደል ብቻ ሳይኾን፣ ከወንድማችን
ጋር የማንስማማበትና የማንግባባበትም ነገር ሊኖረን እንደማይገባ ጭምር የነገረን። መሥዋዕትና ማናቸውም መንፈሳዊ ነገር ከማከናወናችን
በፊት፣ በመካከላችን ያለውን አለመስማማት፣ ክፉ መንፈስ፣ ቅራኔ፣ ቅያሜ ማስወገድ ይገባናል፤ በምትኩ መስማማት፣ ይቅርታ ፍቅር ምሕረት
ማድረግ ይገባናል።
ቤተ ክርስቲያን
ከራስዋ ጋር ተጣልታ ከሃያ ዓመታት በላይ በቅያሜ ውስጥ ነበረች [በእግዚአብሔር ፊት እንዴት አስፈሪ ነገር ነው!?]። ኹለቱም
“አንድ ዓይነት ዶግማና ቀኖና” ነበራቸው፤ ኹለቱም “የአንድ አገር ልጆች ተወላጆች” ናቸው፤ ኹለቱም በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
ጥላ ሥር የተጠለሉ ናቸው፤ ኹለቱም “ወንጌል ጨብጠው፣ ንስሐና የኀጢአት ይቅርታን ለሌሎች “ይሰብኩ” ነበር”፤ አንድ ዓይነት አስኬማ፣
ቆብ፣ ቀሚስ፣ መጾረ መስቀል፣ የቤተ ክርስቲያን አሠራር፣ መቋሚያ፣ ጸናጽል፣ ከበሮ፣ የዜማ ቅኝት፣ ቅዳሴ፣ … ቢኖራቸውም ለዓመታት
ግን አንድ ልብ አልነበራቸውም፤ [ግን በገዛ መንገዳቸው እየሄዱ ጌታ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ሲጥሩ ተመልክተናል]። አምላካቸው
የፍቅርና የርኅራኄ አባትነቱን ልጆቹም እንዲከተሉት፣ “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር
ይላችኋልና፤ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።” (ማቴ. 6፥14-15) ብሎ በግልጥ
የተናገረና በቤተ ክርስቲያኒቱም በየጊዜው “በጸሎት ሲጉተምተም” እንደ ምናስተውለው፣ “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደ ምንል
በደላችንን ይቅር በለን፤” (ማቴ. 6፥12) በማለት ይቅርታ ወዳድነት፣ ፍቅርና ምሕረት አድራጊነት ከምንም እንደሚቀድም በትክክል ያሳየናል። ነገር ግን ኹለቱም እህትማማቾች ተኳርፈው
ደጆቻቸውን በየራሶቻቸው ዘግተው ዓመታትን አሳልፈዋል።
በወንድማችን ላይ ማናቸውም የኀጢአት ስሜት ካለብን አስቀድመን መናዘዝ ይኖርብናል፤
መንፈሳዊ ነገሮችን በማድረግ ይቅርታ እንደ ምናገኝ በማሰብ፣ በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ መዘባበትና የእግዚአብሔርን ቁጣ መቀስቀስ
የለብንም። ኀጢአትን ሰውሮ በእግዚአብሔር ፊት ለመቅረብ ማሰብ ጸሎትንም የጸሎትንም መልስ ያስከለክላል፤ “ኀጢአትን በልቤ አስተናግጄ ቢሆን ኖሮ፣ ጌታ ባልሰማኝ ነበር።” (መዝ. 66፥18) እንዲል። ደግሞም፣
“ባልንጀራንም እንደ ራስ መውደድ በሙሉ ከሚቃጠል መሥዋዕትና ከሌላው መሥዋዕት ሁሉ የሚበልጥ ነው” (ማር. 12፥33)።
ወንድማችንን በፍቅር አለመያዝ በደል ነው፤ ስናስበውም ራስን እንደ መውደድ
ባለፍቅር ባናስበው ፍጹም ኀጢአት ነው። ጥላቻ ነፍስን የሚያነቅዝ ኀጢአት ነው፤ ሌላውን ሰው እንደ ራስ አለመውደድ ነፍስን ከገለባ
ይልቅ ከሚያቀልሉ አስከፊ ኀጢአቶች አንዱ ነው። በዚህ መንገድ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ዓመታትን ተሻግራ ሄዳለችና ልብሷን ቀድዳ ሳይኾን
ልቧን ቀድዳ(ኢዩ. 2፥13)፣ ፍጹም ተዋርዳ ንስሐ መግባት ይገባታል።
በዚህ ዙርያ አንድ ሌላ አስደናቂ ነገር እንስተውላለን፤ የኹለቱ ሲኖዶሶች
“ዕርቅ” ቅቡል የኾነ፣ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የማያውቀውን ዶግማ ሽሯል። ኹላችንም እንደ ምናውቀው “ቤተ ክርስቲያን አትሳሳትም”
የሚል ጽኑ እምነት “በኦርቶዶክሳውያን [በእኛ መካከል]” አለ። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ይኸው ከስህተቷ ታረመች ወይም ለመታረም
ፈቀደች፤ እጇን ዘርግታ ለመቀባበል ወደደች ማለት እንወዳለን። ይህ በሰማይ ታላቅ ደስታን የሚፈጥር መልካም ተግባር ነው። ይህን
ነገር ገፍተን ወይም እንደ ማይመለከተን አድርገን፣ “ለቤተ ክርስቲያን መሳሳትና ተቀያይሞ ለዓመታት መዝለቅ”፣ ምክንያቶቹ የገዢው
መንግሥት የቀድሞ ባለ ሥልጣናት ናቸው” ማለት አንችልም። ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥትም፣ ከምድር ኃይላትም፣ ከአጋንንትም፣
ከገሃነምም ደጆችም … የበለጠ “ሥልጣንና ዕውቀት፣ ጥበብና ሞገስ” ታድሏታልና፤ አለመጠቀሟ ግን እንዲህ ያለ ቀውስ ውስጥ እንድትገባ
እንዳደረጋት ማስተዋሉ አያጠያይቅም።
ደግሜ
እላለሁ፤ መታረቃቸው በሰማይ ትልቅ ደስታ ነው፤ ተጣልተው፤ ተቀያይመው ነበርና፤ (ሉቃ. 13፥10)። በቤተ ክርስቲያን እርቅ ግን
የማይደሰቱ አካላት ትላንት ነበሩ፤ ዛሬም አሉ። እኒህ አካላት ግለሰቦች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ብቻ ሳይኾኑ “በመንፈሳዊነት ስም
የተደራጁ ማኅበራትና ቡድኖች ናቸው” ዕርቁን ያዘገዩት የቤተ መንግሥት ሰዎች ብቻ ሳይኾኑ፣ የቤተ ክህነትም ሰዎች ናቸው፤ ስለዚህም
ለዕርቁ ፍጹምና መንፈሳዊ ስሙርነት እኒህ ነገሮች በተደጋጋሚ እጅግ ቢታሰቡ መልካም ይመስሉኛል፦
1.
ዕርቁ በአደባባይ በዓለም ኹሉ ፊት የታወቀና የተገለጠ ነገር ነበር፤ ዓለሙ ጠባችንን ካወቀውና አውቆም ተዘባብቶበት
ከነበረ፣ የምናመልከው አምላክ “የጠብና የመለያየት” እስኪመስል ተሳልቀውበት ከነበረ፤ ይህን ምዕራፍ በፍጹም ተግባራዊ ንስሐ፣ በእውነተኛ
ፍቅር፣ በትህትና ዳግም እስከ ማይነሣ ድረስ፣ እንዲዘጋ ለዓለሙ ኹሉ ገልጠን ማሳየት አለብን። ንስሐ ገብተን በትክክል ካልታረቅን፣
የጠባችንን ምክንያት ከሥሩ መንግለን ለመጣል ካልጨከንን ነገም “የክፉ ምሳሌ ርዕስና መነጋገርያ” መኾናችን አይቀርም። ስለዚህ እንዴት
ተወጋግዘን፣ ተጠላልተን፣ ተረጋግመው እንደ ነበር አንዘንጋ፤ ኃጢአቱንና በደሉን በሠራንበት መንገድም ንስሐውን ለማድረግ እንጨክን፤
ወደ ክፋት መንገድ ስንገባ ካላፈርን፣ በትክክል በጽድቅ መንገድም እንደቅዱስ ቃሉ ለመውጣትም ለመውጣት መፍራትና ማፈር የለብንም፣
2.
ቤተ ክርስቲያን ከቀደመው ዘመን ውድቀቷ መማር ይገባታል። የመንግሥት ኅሊና ኾና ማገልገሏ ምን ያህል መራር መሥዋዕትነት
እንዳስከፈላት መዘንጋት የለባትም። እርሷ የክርስቶስ ሙሽራ ብቻ ናት፤ ሊያዛትም፤ ሊመራትም፤ ሊያወጣትም ሊያገባትም የሚቻለው ክርስቶስ
ኢየሱስ ብቻ ነው። ለዕርቁ “የታወቁ ከሚባሉ ሰዎች ይልቅ” መንፈሳውያንና በትክክል ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለባቸው[ያላቸው] ሰዎች
ቢሳተፉና ዕርቁ “አብቦ፣ ፍሬው ጎምርቶ እስኪበላ ድረስ” በቃለ እግዚአብሔር፣ በጸሎት፣ በጾም ... የሚተጉ ወንድሞችና አባቶች፣
እናቶችና እህቶች ሊሳተፉበትና አብረው ሊዘልቁም ይገባቸዋል። ስለዚህም የዕርቁ መልክ መንፈሳዊነትና መንፈሳዊ መልክ ብቻ ሊኖረው
ይገባል።
3.
“ከአገር ቤትም ይኹን በውጭው ሲኖዶስ ብዙ አጥቢያና አድባራት” በተለያየ ግፍና ክፋት፤ ጥላቻም የተባረሩ አገልጋዮች
“በውጭው ሲኖዶስና በውስጡ” ውስጥ አሉ። እኒህ የተሰደዱ አገልጋዮች በውጭው ሲኖዶስ እስከ ጳጳስ ደረጃ ድረስ ተሹመዋል፤ በአገልግሎትም
ላይ ናቸው። የአገር ቤት ሲኖዶስም ኾነ የውጭው ሲኖዶስ ያሳደዷቸውን ወይም እያሳደዷቸው ያሉትን፣ ከአንዱ ወደ ሌላው፣ ከሌላውም
ወደ አንዱ የሚሸሹትን አገልጋዮች ለመቀባበል ዝግጁ መኾን ይገባቸዋል። በእርግጥ አንዳንዶቹ “አገልጋዮች” ወደ ፖለቲካውና ወደስህተት
ትምህርት ውስጥ ጭልጥ ብለው ገብተዋል። ስለነዚህ ግን አልልም።
4.
ዕርቅና ዕርቅ እንጂ ሌላ ነገር ፈጽሞ መታሰብና እንደ ቅድመ ኹኔታ መቅረብ፣ መደራደርያም መኾን የለባቸውም። ሰማያዊ
ነገር ሊበልጥብን እንጂ ምድራዊ ነገር መሟገቻና መለያያ ሊኾነንም አይገባም። የአስተምኅሮና የቀኖና ልዩነቶቻችንን በፍቅርና በመቻቻል
መወያየትን እንደ መጽሐፍ ቅዱስና የጥንት አባቶች ትምህርት የሚጸናውን ልናጸና፣ የሚሻረውን ደግሞ ልንሽር እንደ ምንችል በሰከነና
በልበ ሰፊነት ልንወያይ፣ ልንመካከር ይገባናል።
5.
ኹለቱ እህትማማች አብያተ ክርስቲያናት አንድ ከኾኑ በኋላ፣ እንደ ቀደመው ዘመን ተዘልለው መቀመጥ የለባቸውም፤ በዙርያቸው
ላሉ ጐረቤት አገራት [ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኹለቱን ሱዳኖች ...]፣ ወንጌል የመናኘትን ሥራ ለመሥራት መተባበርና መስማማት ይገባቸዋል። “እንግዲህ
ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ
መዛሙርት አድርጓቸው፤ ...” (ማቴ. 28፥19-20) እንዲል ቅዱስ ቃሉ።
6.
ማኅበራት፣ ግለሰቦች፣ መንግሥትም ጭምር እጆቻቸው ረዝሞ የዕርቁ ሂደት ውስጥ መግባት እንደ ሌለበት ማመን፣ መጨከን
“ለመንፈሳዊነቱና ለዕርቁ እጅግ መልካምነት” ወሳኝ መኾኑን በብዙ ማስተዋል እጅግ ጠቃሚ ነው።
ከጠብ
የሚያተርፉና ከመለያየት የሚበለጽጉ ይፈሩ፤ ወደኋላቸውም ይመለሱ፤ በፍቅርና በእውነት የሚዋደዱና የሚቀባበሉ ይለምልሙ፤ በቤተ ክርስቲያን
መታረቅ እጅግ ደስ ይለናል፤ በአባቶች መስማማት ሐሴት እናደርጋለን፤ የተሰናከሉ በመነሣታቸው፣ እንደ ወደቁ ባለ መቅረታቸው ከልብ
መንፈሳዊ ሳቅ እንስቃለን፤ ደግሞ ስሙር እንዲኾን የጸና ጥማትና ናፍቆት አለን፤ በጸሎታችንም እንማልዳለን። እግረ መንገዳችንን
“ለቤተ ክርስቲያኒቱ መለያየትና አለመስማማት የነበረውን የዘረኝነት ግንድ በመቁረጥና “ነገርን ገድለው በማዳን” ምክንያት ለኾኑት”
ለክቡር ዶክተር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዓቢይ አህመድ ያለንን ከፍ ያለ አክብሮት መግለጥ እንወዳለን።
የቤተ
ክርስቲያን ልጆችና አባቶች ለዚህ ዕርቅ ስሙርነት፣ ፍጹም መኾን ተግተን እንጸልይ፤ እንማልድ፤ ደግሞም የሰላሙንና የዕርቁን ወንጌል
እንናኘው፤ እናውጀው፤ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ጸጋና ሠላሙን ያብዛልን፤ ቤተ ክርስቲያንን የጽድቅ ኩል የሚኩል መንፈስ ቅዱስ ሠላምና
ጽድቁን ያብዛልን፤ አሜን።
ጌታ አብዝቶ ይባርክህ፤ ጸጋ ይብዛልህ
ReplyDeleteejg melkam menfesawi eyta Geta yirdah tebarek
ReplyDeleteታዳ መልስ ካላት እየሱስ እኔ ጌታ አይደለሁም አለ የጌታም ልጅ አይደለሁም የፈጣሪየ ባሪያና መልክተኛ ነኝ እኔ ከሱ ከፈጣሪየ ነው አቅምና ቅዋን የሚለገሰኝ ከኔ ከራሴ አንዳች ላደርግ አልችልም እስከ አለም ገናግን እነዚያ ሞኞች ጌታ ጌታ ነህ ይላሉ እኔም በመጪው አለም አላውቃችሁም ጥፉልኝ እላለሁ ይላል ምን መልስ አላችሁ ምንስ ሊውጣችሁ ነው ከቁርአን መረጃ ስትሰጡ መሀመድ ነው የፆፈው በማለት ታስተባብላላችሁ ታዳ መፀሀፍ ቅዱስን መሀመድ ነውን ያፆፈው?
ReplyDeleteThe most stagnant and stupid idea ever I had faced in my life.
ReplyDelete