አማንያን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ
በትክክል እንዲሰሙ፣ ክርስቶስን ሳይኾን ራሳቸውን የሚያገለግሉ አገልጋዮችን ከመስማት ተከልክለው ለቃሉና ለፈቃዱ እንዲታዘዙ ለማድረግ፣
ቤተ ክርስቲያን የራሷን ጠባይ እንደቃሉ ማረቅና ዘወትር በቅዱስ ቃሉ መስታወትነት ራሷን መመልከት ይገባታል፡፡ ንስሐ ራስን
ለእግዚአብሔር በትክክል ማቅረብና አራቁቶ ማቅረብ ብቸ ያይደለ፣ ድርጊታዊ ምላሽን ይሻል የምንለውም ከዚህ ተነሥተን ነው፡፡ ቤተ
ክርስቲያን ሌሎችን ከክፋታቸው እንዲመለሱ ለመምከር ከመዘጋጀቷ በፊት፣ ከምትወቅስበት ወቀሳ ለራሷ ንጹህና በዚያም ነውርና ክፋት
ያልተያዘች፤ ፈጽማም የጠራች ልትኾን ይገባታል፡፡
የራሳችንን ክፉ ጠባይ ሳናስተካክል፣
ሌሎች ትክክለኛውን ነገር እንዲያደርጉና ወደትክክለኛው እውነት እንዲመጡ ጫና ከማድረግ መከልከል አለብን፡፡ ከዚህ ነገራችን
ንስሐ ሳንገባ ይህንን የምናደርግ ከኾነ ግን ቅዱስ ቃሉ፦ “አንተ የምትፈርድ ሰው ሁሉ ሆይ፥ የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው በምትፈርድበት ነገር ራስህን
ትኰንናለህና፤ አንተው ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና” (ሮሜ.2፥1) እንዲል፣ “በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለምን
ታያለህ፥ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም?” (ማቴ.7፥3) በማለት በጽኑ ወቀሳ ሁላችንን ይወቅሰናል፡፡