Saturday, 27 August 2016

ዘረኛነት - ብሔርተኛነት - የዘመናችን ፈተና (ክፍል ሦስት)

በእኛ መካከልስ ምን ይመስል ነበር?
   ዘረኛነትን በተመለከተ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ብንነሳ፥ ኢትዮጲያ ከሰማንያ አራት በላይ ብሔረሰቦች የሚኖሩባትና በተለያየ ብዙ ቋንቋዎችም የሚነጋገሩ ሕዝቦች ያሉባት አገር ናት፡፡ አንዱ አንዱን ለመብለጥ ምክንያት የሚመስሉ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ሰዎች ከአንድነት ይልቅ በየራሳቸው ነገር ላይ ትኩረት ሲያድርጉ ሳያውቁት ሌላውን በመጻረር የሚቆሙበት ጊዜም ብዙ ነው፡፡ ሰዎችን ወደሌላ የክህደት መንገድ ለመምራት መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠኑ በዚያው የመጽሐፍ ቅዱስ አማኝ ሆነው የቀሩ ሰዎች ያሉትን ያህል፤ መጽሐፍ ቅዱስን ተጠግተው ለራሳቸው ምስክርነት እየፈለጉ በዘረኛነት ክፉ ኃጢአት የተያዙ ብዙ ናቸው፡፡
    መጽሐፍ ቅዱስን ተገን ተደርጐ የሚሠራ ኃጢአት እጅግ አስከፊ ኃጢአት ነው፤ በእኛ መካከል ያለው የዘረኛነት መንፈስ እንዲህ ያለ ነው ብንል ማጋነን አለበት አያስብልም፡፡ አንድ ሃይማኖት የተወሰኑ ወይም የአንድ ብሔር እስኪመስል ወይም እስኪባል ድረስ በመካከላችን የሚታየው ነገር አስነዋሪ ነው፡፡ ይህንን በአንድ ጽሑፍ፦
“ … አሁን አሁን ነገራችን እንደዖዝያን ለምጽ ሊሸፈንበት ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ራሱ ችግሩም “አለሁ፣ አለሁ” ብሏል፡፡  የለህም ብንለውም ራሱን በራሱ ያስመሰክራል፡፡ ሙስናው ፣ የዘመድ አሠራሩ …ወዘተ አግጥተው ወጥተዋል፡፡” [1]

Monday, 22 August 2016

በአዲስ አበባ፥ ምነው በሰበበ “ሰላማዊ ሰልፍ” ሁከት አልተቀሰቀሰም?!

Please read in Pdf 
የኢዮአታምን ምክር የማይሰማ ሕዝብና መሪ መጨረሻው ጥፋት ነው!!!
     ትላንት ማምሻውን ስልኬ ከወደብዙ ቦታ በተደረገላት ጥሪዎች ስትንጫረር ነበር፡፡ ከ“ክፍለ አገር” እና ከውጪው ዓለም፡፡ “አዲስ አበባ ሰላም ዋለችን? ከመገናኛ ብዙኃን ምንም መረጃ አጣን? ምንም ሁከት ወይም ሰላማዊ ሰልፍ አልነበረም? ... ምንም ምን አልነበረም? ... ” የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን የሚጠይቁ ወንድሞችና እህቶች፡፡
     ከዚህ የጥያቄ ግርፍ በኋላ ለረጅም ሰዓት ቆም ብዬ ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ ሰው ከሰላም ይልቅ “ሰላማዊ ሰልፍ” ለምን ተጠማ? ከጸጥታ ይልቅ ግርግርና ሁከት ለምን መረጠ? የማያስማማ፣ የማያነጋግር፣ የማያወያይ፣ ጅምር ላይ ሆነን ፍጻሜ መተለም የማያስችል ክፉ መንፈስ ከወዴት ይሆን የተጣባን? የቀደመው ዘመን ታሪክ ስለምን መማርያ አልሆነንም? ከዚህ ቀደም የ“ንጉሠ ነገሥቱን” ሥርዓት ሰለቸን ብለን፥ ከአርባ ዓመት በላይ “የመራንን” ንጉሥ አዋርደን፣ ከሰውነት ተራ አውጥተን፣ “ለባዕድ” የማይነፈገውን የቀብር ቦታ እንኳ ለ“ንጉሠ ነገሥቱ” ነስተን፣ ስም አጠራሩን አጥፍተን ... ወታደራዊውን መንግሥት “በእልልታ በሆታ” በራሳችን ላይ ሾምን፡፡
እርሱም የዘራነውን አሳጨደን፡፡

Thursday, 18 August 2016

በዓይናችን አይተን!

Please read in PDF


ተረት መች ሆነና ብልሐታዊ ንግርት፣
የምሰብከውና የምንዘምርለት፣
አጉል ፍልስፍና ጥበብ መሰል ነገር፣

Tuesday, 16 August 2016

የኢትዮጲያ የ“ማስተዋል” ጸሐይ ምነው አዘቀዘቀ?



Please read in PDF


መንግሥት ሆይ! እባክህ ከማሰር ፤ ከማጐር ይልቅ፥ ራራ! ይቅር በል! ማር!!!
     በምዕራቡ ዓለም በተደላደለ መኖሪያ ቤታቸው ተቀምጠው እንደሰበኩን፥ “ጨካኝ ፣ እብሪተኛ ፣ አምባገነን ፣ አረመኔ ፣ ጉበኛ ፣ ዘረኛ ፣ ሴሰኛ ፣ አድርባይ ፣ አፋኝ …” ያሉት ይህ የአገር ቤቱ መንግሥት ወረደ እንበል፤ ግን እኒህ ዲያስፖራ ፖለቲከኞችና ፈሪሳውያን ሃይማኖተኞች ያልመለሱልን ጥያቄ፥ “ማን እንዲመራን ነው ያቀዱት? ፣ ማንን ይሆን ያዘጋጁልን? እነርሱ ራሳቸው ከአውሮፓና ከአሜሪካ ሊመጡና ሊመሩን? ፣ ወይስ ከዚሁ አገር ቤት የሚያሰናዱልን ነገር ኖሮ ይሆን?”
     አንድ ሌላ ጥያቄ አለኝ? እኒህ “ዲያስፖራውያን የፖለቲካና የሃይማኖት ዲስኩረኞች” ለመሆኑ ስለአንድነትና ስለመንፈስ አንድነት ለማውራት በእውኑ ሞራሉና ብቃቱ አላቸው? በአንድ ነገር አምናለሁ ፤ የአገር ቤቱ መንግሥት ብዙ ነውር ፣ ዕድፍ ፣ ርኩሰት ፣ ልክፍት ፣ በደል … አለበት ፤ ይህን አምናለሁ፥ አልጠራጠርም፡፡ አንድ ብርቱ መከራከርያ ግን አለኝ፡፡ ከአገር ቤቱ መንግሥት ይልቅ “የአሁኑን የነውጥ እንቅስቃሴ እየመራ ያለው የዲያስፖራው ጐልማሳ” ግን ነውሩና ርኩሰቱ ከአገር ቤት መንግሥት ይበልጣል ባይ ነኝ፡፡

Monday, 8 August 2016

ዘረኛነት - ብሔርተኛነት - የዘመናችን ፈተና (ክፍል ሁለት)

በአለም ላይ የነበረው ገጽታ
“ኹሉም የሰው ዘር የተፈጠረው በእኩልነት ነው”
(የነጻነት አዋጅ ፤ ሐምሌ 4 1776 ዓ.ም)
    Please read in PDF

በአለም ላይ የነበረው ገጽታ
“ኹሉም የሰው ዘር የተፈጠረው በእኩልነት ነው”
(የነጻነት አዋጅ ፤ ሐምሌ 4 1776 ዓ.ም)
     ይህ አለም አቀፍ አዋጅ በዘረኛ ጠባይና ድርጊት በሚከተሉ ሰዎች በግልጽ ከመሻሩና ከመጣሱም በላይ፥ በአለም ላይ ዘረኛነት በግልጥ የታየበት ጊዜም ብዙ ነው፡፡ በሥልጣኔ ከመጠቁት እስከ በሥልጣኔ ወደኋላ በቀሩት ሕዝቦች መካከል ከሚታይ ጥላቻ እስከትውልድ መደምሰስ የሚያደርስ የዘረኝነት ተክል በአለም ሁሉ ፊት  በቅሏል ፤ አብቧል ፤ ፍሬውም ሆምጣጤ ሆኖ በክፉ ምሳሌነቱ ታይቷል ፤ አሁንም ድረስ እየታየ ነው፡፡ ዘረኛነት ድንበር ሳይከለክለው በጸሐፍት፣ በባዕለ ሥልጣናት፣ በምሁራን [1] ፣ በጳጳሳት ፣ “ለምድር የከበዱ በሚባሉ ብዙ ሕዝቦች” ዘንድ ተገልጧል፡፡
       ሄሮዶተስ (Herodotus) [2] በሊብያ በረሃ ደቡብ ምዕራብ ጠረፍ ስለሚኖሩ ሕዝቦች ማንነት ሲናገር፥ “… ከአደገኛ አውሬዎችና ልዩና አስገራሚ ፍጥረታት ጋር የሚኖሩ ፣ ጭንቅላት የሌላቸው ፣ ዓይናቸው በደረታቸው ላይ የሚገኙ ወንዶችና ሴቶች ናቸው” [3] በማለት ለአፍሪካና አፍሪካዊ ማንነት የሰጠው ተፈጥሮን ተቃራኒ ንግር ነበር፡፡ [4] ጥቁር በመሆን ብቻ አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ፥ ሌሎች የእስያና የሌሎችም አህጉራት ሕዝቦች እጅግ ከባድ ውርደትና አጸያፊ ጥላቻን ለመቀበል ተገደዋል፡፡ ምናልባት ይህ እጅግ በራቀው ክፍለ ዘመን ፤ ሥልጣኔና አመለካከት ባልዳበረበት ዘመን ነው ብለን ብንሞግት እንኳ፥ አሻራው ሳይደበዝዝ በዚህ በዛሬው ጊዜ ፍንትው ብሎ ፤ በመካከላችንም ጭምር እናስተውለዋለን፡፡

Tuesday, 2 August 2016

“27 አባቴ” የሚባል አባት የለንም!

Read in PDF

    አባት የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላቸው ሲፈቱት፥ “የግብርና የክብር የማዕረግ ስም፡፡ አባት መባል በብዙ ወገን ስለኾነ ከግዜር ዠምሮ ያባትነት ሥራ ለሚሠሩ ለመንፈሳውያን አባቶች ለቄስ ለመነኵሴ ለአእሩግና ለሊቃውንት ለመምህራን ኹሉ ይነገራል፡፡ … (ሐተታ) አብ በጥሬነቱ ዘርፍ ይዞ ሲቀጸል ምስጢሩ ካባትነትና ከጌትነት ከባለቤትነት አይወጣም፡፡” [1] በማለት በግልጥ አስቀምጠውታል፡፡
     የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላትም፥ “ የወለደ፥ በሥርዓት ኮትኩቶ ያሳደገ፥ በሥጋና በመንፈስ የአባትነትን የፈጸ ሁሉ አባት ይባላል፡፡ … ምእመናን ከእርሱ በመንፈስ ቅዱስ ስለተወለዱ “አባ አባት” ብለው ይጠሩታል ፤ ማቴ.6፥9 ፤ ዮሐ.1፥12 ፡ 13 ፤ ገላ.4፥6” በሌላ ሥፍራም፥ “አብ ፤ አባት ማለት ነው፡፡ ይህ ስም ከዘለዓለም ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ለነበረው ለእግዚአብሔር አብ የሕላዌ(የአንዋንዋር) ስሙ ነው(ማቴ.28፥19 ፤ 1ጴጥ.1፥1-2)፡፡ ኢየሱስ ስለሰማያዊ አባት ሲናገር ብዙ ጊዜ አብ ብሎ ጠራው፡፡” በማለት ቄስ ኮሊን ይገልጡታል፡፡ [2]

     በሌላ ትርጉምም “አባት ፤ (አብ) ወላጅ አስገኝ ፤ አሳዳጊ ፤ ሞግዚት ፤ መነኵሴ፡፡ (የነገር አባት) ፣ ጠበቃ ነገረ ፈጅ፡፡ (ያገር አባት) ፤ ሽማግሌ መካር ዛሬ አንዱ ቤት ነገ እሌላ ቤት እያደረ የሚጦር፡፡ … (የድኻ አባት) ድኻ ሰብሳቢ፡፡ (የንጀራ አባት) ፤ የናት ባል እንጀራ እያበላ ያሳደገ፡፡ … ” [3] በማለትም አስፍተው መተርጉማን ያስቀምጡታል፡፡
    ከእነዚህ የፍቺ መዝገበ ቃላት የምናስተውለው ትልቅ ቁም ነገር አባትነት ከጽንሰት እስከ ልደት ፤ ከልደት እስከእውቀት በሁለንተናው ከተወላጅ ልጅ ጋር ፍጹም ሥጋዊ ፣ ነፍሳዊ ፣ ዕውቀታዊ … ትስስርን የሚያሳይ ትልቅ ምስጢርን ያዘለ ትርጉም መሆኑን ነው፡፡