ከማይጠፋ ዘር ተወልደን ወንድማማች
የሆንበት ምስጢር
ጌታ ኢየሱስ ከባሕርይ
አባቱ ከአብ የተወለደ ፍጹም ልጅ ነው፡፡ በእርሱ ልጅነት እኛ ደግሞ ልጆች ተብለናል፡፡ በዓመጽና ባለመታዘዝ ፊተኛው አዳም የእግዚአብሔር
ልጅነትን ሲያጣ ሁለተኛው አዳም እግዚአብሔር ወልድ እንደልጅ ፍጹም በመታዘዝ (ዕብ.5፥8) ሁላችን ለእግዚአብሔር ልጆች እንሆን
ዘንድ እርሱ በኵር ሆነ፡፡ እኛ ወደአባቱና ወደእርሱ ክብር የምንገባው የእርሱን “አማኑኤልነት” አብነት አድርገን ነው፡፡ የቀደመው
አዳም ከኃጢአት የተነሳ ለሞት ወልዶን ነበርና፡፡
ከማይጠፋ ዘር ስለመወለድ
ወይም ስለዳግም ልደት ስንናገር በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ መፈጠርን ወይም ፍጹም መለወጥን የሚያሳይ ነው፡፡ መፈጠር የሚለው ቃል
አዲስ ማንነትን ማግኘትን ያሳያል ፤ ከዚህም የተነሣ ከእግዚአብሔር የሆነ የዘላለም ሕይወት ሠርጾ በአማኙ ልብ ውስጥ ይገባል፡፡
(ዮሐ.3፥16 ፤ 2ጴጥ.1፥4 ፤ 1ዮሐ.5፥11) አማኙም በእምነት ጌታ ኢየሱስን ተቀብሎታልና ፍጹም የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል
(ዮሐ.1፥12 ፤ ሮሜ.8፥16 ፤ ገላ.3፥26) ፤ አዲስ ሰውነትን (2ቆሮ.5፥17 ፤ ቈላ.3፥9) የዘላለም ሕይወት (1ዮሐ.5፥20)
ያገኛል፡፡