ከሌሎች ወንጌላት ይልቅ ጠፍቶ ስለመገኘት ሉቃስ ብዙ ምሳሌዎችን
ይሰጠናል፡፡“ጠፍቶ የተገኘው” ህጻኑ ኢየሱስ(ሉቃ.2፥46)፣ ጠፍቶ የተገኘው በግና ድሪም (ሉቃ.15፥3-11) ሉቃስ የዘገባቸው
እውነትና ምሳሌዎች ናቸው፡፡በእርግጥ በኃጢአት ጠፍቶ ለበጎነት እንደመገኘት ያለ ፍጹም ሰማያዊ ደስታ የለም፡፡(ሉቃ.15፥10)
የጠፋው ልጅ የአባቱን ሀብት ለመካፈል ሲነሳ ወደአባቱ ቤት ለመመለስ ፈጽሞ ያሰበ አይመስልም፡፡ከአባቱ ቁጥጥር ውጪ በመሆን
ያሻውንና የወደደውን ሊያደርግ በመፈለግ ወጥቶ የሄደ ነው፡፡“ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ የሄደው ወደሩቅ ሀገር ነው፡፡”(ሉቃ.15፥13)
በሄደበት ሀገር ግን ሀብቱን በተነ፡፡ እንዳይመለስም እጅግ ርቆ ሄደ፡፡ የኃጥዕ መንገድ ከእግዚአብሔር የተለየ ነውና ሩቅ ነው፡፡
ከእግዚአብሔር የተለየው አዳም መልካም በሚመስለው መንገድ ሲጓዝ ፤በገነት እያለ ከእግዚአብሔር ሩቅ ነበር፡፡(ዘፍ.3፥6) በተመሳሳይ
መንገድ ዮናስ ከእግዚአብሔር ፊት ወደተርሴስ የሄደው ዋጋ ከፍሎ፤ከስሮ ፤ርቆም ነው፡፡(ዮና.1፥3)
የጠፋው ልጅ ከመራቁ ባሻገር በረሃብ ምክንያት የሚጨነቅም ሆነ፡፡ የረሃቡን ጭንቀት ለማስታገስ “ … ሄዶም ከዚያች አገር
ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፥ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው።እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፥ የሚሰጠውም
አልነበረም።”(ሉቃ.15፥15) ይላል፡፡ የጠፋው ልጅ የእሪያ እረኛ በመሆን ያደረገው ይህ ድርጊት በአይሁድ ልማድና በኦሪት ህግ እጅግ ርኩሰት ነው፡፡(ዘሌ.11፥7) ይህ ብቻ አይደለም ለእንሰሳት
የሚሰጠውን የእህል ገለባ (አሰር) ሊበላ እየተመኘ እንኳ ሊያገኝ ያልቻለ ነበር፡፡