የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን መካከል ሙስና መቃብርን
አጥፍቶ መነሣት የክርስትና መሠረት የቆመበት ጽኑ ዐለት ነው፡፡ አሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ደም በጸጋ ድነናል፤ ወደፊት ደግሞ ፍጹም
እንድናለን፤ (ኤፌ.2፥8) ብለን ደፍረንና ጨክነን ጮኸን የምንናገረውና ቤተ ክርስቲያንም አሰምታ የምትሰብከው እርሱ ዝጉን መቃብር
ሳይከፍት፤ የታተመው ድንጋይ ሕትመቱ ሳይፈታ፤ ሞትን ድል አድርጎ ከሙታን መካከል ስለተነሣ ነው፡፡
የጌታ ትንሣኤ የስብከቶች ሁሉ ዋናውና የመጀመርያው፤ ትልቁም ርዕስ ነው፡፡ አንድ
ሰባኪ የእግዚአብሔርን ቃል ሊናገር በወጣበት አውደ ምሕረት ላይ “ብዙ ቃል” ሰብኮ የጌታን ትንሳኤ ሳይናገር ቢወርድ፤ በእውነት!
እውነተኛ ሰባኪ መሆኑ ያጠራጥራል፡፡ ምንም እንኳ ጥቂት እንከኖች ቢኖርባትም ያቺ በተራራ ላይ የተሠራችውና ታበራ የነበረችው የሐዋርያት
ቤተ ክርስቲያን በአስቆሮቱ ይሁዳ ፈንታ ሌላ ሐዋርያ ሊመርጡ ባሉ ጊዜ ያስቀመጡት የመጀመርያው መስፈርት “ … ከእነዚህ አንዱ ከእኛ
ጋር የትንሣኤው ምስክር ይሆን ዘንድ ይገባል”(ሐዋ.1፥22) የሚል ነው፡፡
ደቀ መዛሙርቱ
ያልተደራደሩበት እውነት “ከእኛ ጋር የትንሣኤው ምስክር” የሚሆን ብቻ እርሱ እውነተኛ የጌታ ሐዋርያ ነው ብለው ማመናቸው ነው፡፡ ጌታ
ከሙታን መካከል መነሣቱን የሚያምኑና የሚያውቁ ብዙ ሰዎች በዚያን ጊዜ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ የተፈለገው፤ ጌታ “እንደ
ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ ”(ሮሜ.1፥4) መሆኑን ሳይፈራ ሳያፍር በአደባባይ የሚመሰክር ሐዋርያ ነው፡፡