Wednesday, 30 April 2014

መስቀል ላይ ያላችሁ!

Read in PDF: Meskel Lay yalacheu

 ሥቁል ነኝ ለዓለም የማልረባ ባዶ
እርሷም በእኔ ፊት ፍሬ የሌላት ነዶ
የዓለምን አምሮት ቋቅ እንትፍ አድርጌ
በሞት ኢየሱስን ደግሞም በመቃብሬ
አንድ ሆኛለሁ ሎሌው በእርሱ በዝቶ ክብሬ፡፡

Sunday, 27 April 2014

ደቀ መዛሙርት የጌታን ትንሳኤ ለምን ተጠራጠሩ?(ክፍል - 1)

    “ትንሳኤ ሙታንስ ከሌለ ክርስቶስ አልተነሳማ፤ክርስቶስም ካልተነሳ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ከንቱ ናት፤ደግሞም ክርስቶስን አስነስቶታል ብለን በእግዚአብሔር ላይ ስለመሰከርን ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል … ፡፡”(1ቆሮ.15፥13-16)
   “የክርስቲያን የሃይማኖት ትምህርት መነሻና መድረሻ፣በሞትና በትንሳኤ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው ቢባል ከእውነት የራቀ አይሆንም፡፡” (አበራ በቀለ(ሊቀ ጉባኤ አባ)፡፡(1996)፡፡ትምህርተ ሃይማኖት እና ክርስቲያናዊ ህይወት፡፡አዲስ አበባ፡፡ንግድ ማተሚያ ድርጅት(ማህበረ ቅዱሳን)፡፡ገጽ.209)

   “የክርስቶስ ትንሳኤ ለክርስቶስ አምላክና ለክርስቲያናዊ ትምህርታችን እውነተኛነት ከፍተኛ ምስክር ነው፤ምክንያቱም ክርስቶስ ሲገረፍ፤ሲዋረድ፤ሲሰቀል እንደዕሩቅ ብእሲ ተቆጥሮ ነበር፤ደካማም መስሎ ተገምቶ ነበርና፤ በመለኮታዊ ሥልጣኑ ሞትን አሸንፎ ሲነሳ ግን አምላክነቱን ኃያልነቱን ገልጧልና፡፡ እንዲሁም ክርስቶስ የተናገረው ያስተማረው ሁሉ ማጠቃለያው ትንሳኤው ስለሆነ ነው፡፡” (መልከጼዴቅ(አባ)፡፡1984፡፡ትምህርተ ክርስትና ፪ኛ፡፡አዲስ አበባ፡፡ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ድርጅት፡፡ገጽ.59

     ከመሠረታውያን የክርስትና ትምህርት አንዱና ዋናው የጌታን ትንሳኤ ማመንና መቀበል ነው፡፡የጌታን ትንሳኤ አለማመን ወይም መጠራጠር በጠቅላላ ክርስትናን እንደመካድ ይቆጠራል፤ከመናፍቃን እንደአንዱም ያስደምራል፡፡“ክርስቶስ ካልተነሳ እምነታችን ከንቱ ናት እስከአሁን ድረስ በኃጢአት አለን” ማለትን ያስደፍራል፡፡(1ቆሮ.15፥17) የክርስትና እምነት መገለጥ ነው፤እግዚአብሔር ራሱን በልጁ ገለጠልን፤ራሱ እግዚአብሔርም ከእኛ እንደአንዱ ሆኖ በእኛ መካከል ለእኛ ተገለጠ፡፡የዚህ ትምህርትና እምነት መደምደሚያ የተስፋውን ነገር ስናምን ነው፡፡ትልቁ የተስፋ ትምህርት ደግሞ የክርስቶስን ትንሳኤ በማመን የሙታንን ትንሳኤ ተስፋ ማድረግ ነው፡፡“የሙታንንም መነሳት ተስፋ እናደርጋለንና”፡፡(አንቀጸ ሃይማኖት)

Tuesday, 22 April 2014

"ዘፋኝ" ለኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ምኗ ነው?

Please read in PDF :- zefagn lebetekiristiyan mnua new?
ከሰሞኑ አንድ ዘፋኝ “ከወንጌላውያን ህብረት አብያተ ክርስቲያናት አባል ነህ” ያሉትን ድህረ ገፆችና  መገናኛ ብዙሀን እንደሚከሰና እርሱ “ኦርቶዶክሳዊ” እንደሆነ ማረጋገጫ እንዲሰጡት፤ይቅርታ  እንዲጠይቁትም ሊያደርግ  እንዳሰበ ከመገናኛ  ብዙሀን  ሰምተናል፡፡“ተደንቀናልም”፡፡ ለመሆኑ “ዘፋኝ” ለኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን  ምኗ  ነው? አማት ወይስ ምራት? አጎት ወይስ  አክስት? “የወንጌላውያን ህብረት አብያተ ክርስቲያናት” ዓለም  ያከበረቻቸው  ሰዎች ሲመለሱላቸው “የሚደሰቱት”፤ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ዓለም ያከበረቻቸውን እርሷም አብራ በመመቻመች የሚዘልቁት እስከመቼ  ነው? (ምነው የትም በጭፈራ እያሳለፉ የዚህ እምነት ተከታይ ነበርኩ ዛሬ ጌታ “ተገለጠልኝ” ማለት አልበዛም እንዴ?)

    አንደራደርም ፤“ዘፋኝነት” (አዲሱ “የቤተ-ክርስቲያናችን  መጽሐፍ  ቅዱስ” ባይጠቅሰውም) የሥጋ ሥራ ነው፡፡(ገላ.5፥21) የሥጋን ሥራ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ የእግዚአብሔርን  መንግስት  አይወርስም፡፡ (1ቆሮ. 6፥11) በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግስትም ርስት የለውም፡፡(ኤፌ.5፥5)፡፡እርግጥ ነው በቀደመው ዘመን ሁላችን የኃጢአት ባርያዎች፤ የሞትም አገልጋዮች ነበርን፡፡ ነገር ግን ዛሬ ከዚያ ከምናፍርበትና ከምንፀፀትበት ህይወታችን ያተረፍነው ምንም ፍሬ ስለሌለን፤ መጨረሻውም ሞት እንደሆነም ስላመንን፤ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆነን አሁን ከኩነኔ ነፃ ነን፡፡(ሮሜ 6፥20፤8፥1) ባዕለጠጋው እግዚአብሔር  ‹‹ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩም የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ህይወትን ሰጠን፤ በፀጋውም አዳነን››፡፡(ኤፌ.2፥4-6)

Saturday, 19 April 2014

“ከጾመም በኋላ ተራበ፡፡”(ማቴ.4፥2)


Please read in PDF:- ከጾመም በኋላ ተራበ

      ጾማችንን የልማድና መለኮታዊ ኃይል አልባ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ከጾምን በኋላ የመብላትና የመጠጣት ፍላጎት እንጂ መንፈሳዊነትን በመራብ መሻትና ፍለጋ በውስጣችን አለመኖሩ ነው፡፡ጌታ ኢየሱስ የይፋ አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾሟል፡፡ጌታ እንደጾመም ተፈትኗል፡፡የተፈተነው በዲያብሎስ ነው፡፡የፈተናው መጀመርያ ደግሞ በመብልና በመጠጥ ነበር፡፡እኛ ለመብላትና ለመጥገብ ስንጾም ጌታ ኢየሱስ ግን ለመራብና “ለትልቅ መለኮታዊ ዓላማ” ጾመ፡፡
 ጌታ ኢየሱስ እንደዘመኑ አባባል ኃጢአት ስለነበረበት የኃጢአት ሥርየት ሊያገኝ አልጾመም፡፡ ጌታ ኢየሱስ ኃጢአት የማድረግ ፍላጎትም ሆነ ዝንባሌ የሌለው፣በተግባሩ፣በንግግሩና በመንፈሱ ፈጽሞ ኃጢአት ያልፈጸመ ነው፡፡እርሱ ኃጢአትን አያውቅም፤አላደረገምም፤ተንኮልም በአፉ ያልተገኘበት … (2ቆሮ.5፥21 ፤1ጴጥ.2፥22) ቅዱስና ያለተንኰል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለና(ዕብ.7፥26) በእርሱም ኃጢአት የሌለ ነው፡፡ (1ዮሐ.3፥5) ስለኃጢአት ማንም እርሱን መውቀስ አይቻለውም፡፡(ዮሐ.8፥46)፡፡ ይህ ንጹህና ጻድቅ ጌታ ግን ከጾመ በኋላ ተራበ፡፡መራቡ ደግሞ ግልጥ ፈተና ይዞ መጣ፡፡
  የጌታ ኢየሱስ በዲያብሎስ መፈተን ለአርዓያ የሆነ ወይም የቀረበ አይደለም፤በእውነትም እርሱ ተፈትኗል፡፡“ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደእኛ የተፈተነ …”(ዕብ.4፥17)፣ “ተፈትኖም መከራን የተቀበለ” (ዕብ.2፥15) ነው፡፡ ዲያብሎስ በምሳሌነት ሳይሆን በእውነትም ፈትኖታል፡፡ጌታ ኢየሱስ ከሰማያት ወደእኛ የመጣው በጸጋው ቃል ለድሆች ወንጌልን ሊሰብክ፣የታሰሩትን ሊፈታና በተአምራቱ የተጠቁትን ነጻ በማውጣት የተወደደችውን የጌታ ዓመት ይሰብክ ዘንድ ነው፡፡(ሉቃ.4፥17) ይህ ደግሞ “መለኮታዊ ዝግጅት” ያስፈልገዋል፡፡ የቃል ኪዳኑን ሰነድ ሙሴ ሊቀበል አርባ ቀንና አርባ ሌሊት፣ኤልያስም እስከእግዚአብሔር ተራራ ድረስ ለመጓዝ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጾምን ጾመዋል፡፡ጌታ ኢየሱስም የአባቱን ፈቃድ ሊፈጽም ጾመ፡፡
  ከጾማችን በኋላ ትልቅ ሥራ፤ ትልቅ የመንፈስ ቅዱስ መቀባት ከሌለ ጾሙ ልማድ ወይም ከረሃብ አድማ ያለፈ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ ሙሴም ኤልያስም ከጾማቸው በኋላ ታላላቅ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡(ዘፀ.34፥28፤1ነገ.19፥8) ከእግዚአብሔር ቅዱሳን የምናየው ትልቁ እውነት ከዝግጅት በኋላ ትልቅ ድል በሠራዊት ጌታ ጉልበት እንደሚቀዳጁ ነው፡፡መርዶክዮስ፣ አስቴርና በሱሳ ግንብ ሥር የነበሩት አይሁድ ከጾሙ በኋላ ታሪክ ገለበጡ፡፡(አስ.8፥4) የነነዌ ሰዎች ከጾሙ በኋላ ቁጣ በረደላቸው(ዮና.3፥10) … ብዙ ቅዱሳንና የእግዚአብሔር ህዝቦች ከጾምና በፊቱ ከመማለድ በኋላ የተወደደ መልስን ከጌታ ዘንድ አጊኝተዋል፡፡እኛ በጾም ተርበን ሳንፈተን  በራሳችን እጅ በዶሮና በበሬ ሥጋ፤በዝሙትና በሙዚቃ ኮንሰርት የኃጢአቱን ፈተና በሰይጣናዊ ንስሐ እንመልሳለን፡፡

Friday, 18 April 2014

መካከለኛው መስቀል

ለሁለት ሺህ ዘመናት ግለቱ ያልቀዘቀዘ፣ ኃጥአንን የማረከ፣ መናንያንን ከፍጡር ፍቅር ለይቶ ያመነነ፣ ደናግላንን “የዘመኔ ጌታ አንተ ነህ” እንዲሉ ያስመካ፣ ሊቃውንትና መተርጉማን ቀለምና ብራናቸውን አስቀምጠው እንዲመሠጡና እንዲደመሙ ያደረገ፣ ዘማርያን ክብራቸውን ያስጣለና በደስታ ያዘለለ፣ህጻናት ማር አንደበታቸው እየጣፈጠ የተናገሩለት፣ ሰማዕታት “ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ድል መንሣትህ የት አለ?” እያሉ የፎከሩት፣ ሰማይና ምድር የተራረቁት፣ የመለኮትን ክብር እንዳናይ የጋረደን መጋረጃ ከሁለት የተቀደደው ፣ከበረቱና ከመንጋው የተለዩት አህዛብ ወደአንዱ እረኛና ወደመንጋው የተጨመሩት ፣የሚያስጨንቀን ተጠርቆ በሞቱ ከመንገድ የተወገደው፣ አበው “እንዲህ ያለ ሰውን መውደድ አንዴት ያለ ፍቅር ነው?!” ብለው በመገረም የጠየቁት፣በወንበዴነት የዘላለም ባልንጀሮች የነበሩት በህይወቱ ጌታ ምርጫቸው የተለያየበት፣ከምድር እስከሰማይ የሚያድርሰው መካከለኛው መስቀል ጻድቃን የጸደቁበት፣ሰማዕታት የጨከኑበት ፣እናቶች ያነቡለት፣የሚወዱት ያለቀሱለት ድንቅ ምስጢር ነው፡፡
      የመካከለኛው መስቀል ለሁሉም ፍጥረተ አለም የሚማልድና ለሁሉም አዳማዊ ፍጥረትም እኩል እጁንም የዘረጋ ነው፡፡የመስቀሉ ደም ምርጫቸውን በንስሐ ለሚያስተካክሉ ኃጥአን ህይወትና የዘላለም ገነት ነው፡፡የመስቀሉ ደም ከአቤል ደም ይልቅ ምህረትንና የሚሻለውን የሚናገር “የማስተሥረያ ሥርዓት” ሆኖ በአብ ፊት ለኃጢአን ሁሉ የሚቆምና ስለመዳን፣ስለይቅርታ ሳይታክት የሚጮህ ነው፡፡(ዕብ.12፥23)

Wednesday, 16 April 2014

ጌታ ለምን የደቀ መዛሙርቱን እግር አጠበ?

መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገዋል የሚባሉ  ልማዶች በየጊዜው ባለመሰልቸት ሊመረመሩና ሊጤኑ፤ ግድፈት ሲገኝባቸው ሊስተካከሉ፤  መጽሐፍ ቅዱሳዊውን እውነት እንደጨበጡ ያሉ ከሆኑ ደግሞ በፀሎትና በቃሉ ቅጥርነት ሊጠበቁ ይገባቸዋል፡፡ በቤተ-ክርስቲያን ቀኖና  መሠረት ከበዓለ ሥቅለት በፊት ባለው ሐሙስ እግር  የማጠብ ልማድ ስላለ ከታላላቆች ሊቃነ - ጳጳሳት “እንደማዕረጋቸው” እስከታች ያሉቱ የሌሎች “ታናናሾቻቸውን” እግር ያጥባሉ፡፡በዕለቱም ስለትህትና ተገልጦ ይሰበካል፡፡ በእርግጥ እውነተኛ  ትህትና ትልቁ ትንሹን ሲያገለግል እንጂ ትንሹ  ትልቁን ሲያገለግል ብቻ አይደለም፡፡
 በእኛ ማህበረሰብ ውስጥ  “ትልቅ” የተባሉት አካላት ትልቅነታቸውን እንዳስከበሩ መኖር እንጂ ፈፅሞ  ዝቅ ብለው ማገልግል አይሆንላቸውም ቢያደርጉትም በዓመት አንዴ እንደበዓል እንጂ የዕለት ተዕለት በጎ ምግባር ሲሆን አይስተዋልም፡፡ ጌታ ግን ይህ የእግር ማጠብ ሥርዓትም እንደበዓል  በዓመት አንዴ ሳይሆን በየእለቱ እንድናደርገው በፍቅር አዝዞን ነበር፡፡(ዮሐ- 13፥15) ይሁን እንጂ ዘመናችንን ሙሉ ባልጀራችንን እየተጠራጠርን፤ በኑሮዐችን ሁሉ በክፉ ቅንዐት ነቅዘን ያለቅነው፤ ከእኔ ይልቅ የባልንጀራዬ ጥቅም  ይቅደም(ፊሊ.2፥4) ከማለት የተስገበገብነው... የልማድ እግር ማጠብ እንጂ እውነተኛ ትህትና በውስጣችን ስለሌለ ነው፡፡ በተለይ የቤተ-ክርስቲያን መሪዎች፣ የሀገር መሪዎችና  ባዕለሥልጣናት የሾማቸው እግዚአብሔርና አደራ አሳልፎ የሰጣቸውን ህዝብ ሲገዳደሩና ሲዘባነኑበት እንጂ ዝቅ ብለው በትሁት ልብ ሲያገለግሉት ማግኘት እንደ ዔሊ ዘመን የእግዚአብሔር ራዕይና ቃል ብርቅ ነው፡፡ (1ሳሙ.3፥1)

Monday, 14 April 2014

ሆሼዕና ኢየሱስ


Please read in PDF ; hoshena Eyesus
ምድር ነዳ ከስላ  - ጠቋቁራ ጠልሽታ፤
ዙርያዋን በኃጢአት - ነበልባል ተከባ፤
ትዳር መቅኖ አ’ቶ፤
ሴሰኝነት ክንፉን አርብቦ ዘርግቶ፤
ትውልድ በአመጻ መንፈስ ነፍሱ ጎብጦ፤
              እያየኸው አይሙት የሞትክለት ትውልድ
              ሆሼዕና ኢየሱስ ልቡን መልስለት፡፡
ቃየላዊ ብልጠት - ባ’ቤል ደም መጨቅየት፤
በለዓማዊ ብልሐት - የመረረ ርኩሰት፤
የከንፈር አምልኮ - የሽንገላ ፍቅር፤
ድኃውን ከፍትህ - በገንዘብ መፈንገል፤

Monday, 7 April 2014

ኒቆዲሞስ - የአይሁድ አለቃ



በቤተክርስቲያን ቀኖና መሰረት ሰባተኛዉ ሳምንት የጌታ ፆም ስያሜ ኒቆዲሞስ ይባላል፡፡የሚነበበም የቅዱሱ ወንጌል ክፍል ደግሞ ዮሐ.3÷1 ጀምሮ ያለዉ ነዉ፡፡የዮሐንስ ወንጌል እንደሌሎቹ ወንጌላውያን የኢየሱስ ታሪክ ላይ አያተኩርም፡፡ የኢየሱስን ክርስቶስ መሆን እያስረገጠ የአዲስ ኪዳንን የአምልኮ መገለጫና መንፈሳዊነትን እያጎላ የተጻፈ ቅዱስ ወንጌል ነው፡፡ገና ወንጌሉን ሲጀምር አከላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስን ጨለማ የማያሸንፈው፣ ሁሉ በእርሱ የሆነ፣ ጸጋንና እውነትን የተመላ፣ የእኛንም ሥጋ የነሳ ህይወትና ጸጋን አስገኚም ቃል እንደሆነ አበክሮ ይመሰክራል፡፡(ዮሐ.1፥1-15) ጌታ መንፈሳዊ የማያረጅ ልጅነትን ለሽማግሌውና ለትልቁ ባለሥልጣን ለኒቆዲሞስ እንዳስተማረውም የዘገበልን የዮሐንስ ወንጌል ብቻ ነው፡፡
    ኒቆዲሞስ የአይሁድ አለቃ የሆነ ፈሪሳዊ ባለሥልጣን ነው፡፡በጌታ ኢየሱስ ዘመን ብዙ አይሁድና ፈሪሳውያን ጌታን ያሳድዱት ፤ሊገድሉትም ይፈልጉት ነበር፡፡(ዮሐ.5፥16፤7፥19) የህጉን ምንጭ ክርስቶስን እየተቃወሙ ስለህጉ እንቀናለን ብለው ኢየሱስን ፈጽመው ጠሉት፡፡እነርሱ ከማይወዱትና የገዛ ወገናቸው ሆኖ ካልተቀበሉት (ዮሐ.1፥11) ከዚህ ሰው ጋር ኒቆዲሞስ ብርቱ ወዳጅነትን መሰረተ፡፡ትንሹ ባለሥልጣን ትልቁ ባለሥልጣን ዘንድ ቀርቦ ያወራው የሥልጣኑን ዘለቄታነትና የማርዘሚያውን መንገድ ሳይሆን መንፈሳዊውን እውነት ነው፡፡

Thursday, 3 April 2014

ሁለተኛው መስቀል

Please read in PDF ;- huletegnaw Meskel

ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ የቱ ወንበዴ በግራ እንደተሰቀለ ሳይነግረን፤ ጌታ ግን በሁለቱ ወንበዴዎች መካከል መሰቀሉን ይነግረናል፡፡እንዳለመታደል ግራና በግራ መሆንን ፈጽሞ እንጠላለን፡፡ጸሎታችንም በቀኝ አውለኝ እንጂ በግራ አውለኝን አያካትትም፡፡መቼም ጌታ ፍየሎች(ኃጥአን) በግራ ይቆማሉ ሲል በሰማያዊ ዓለም ግራና ቀኝ አለ ሊለን አይደለም፡፡
     ግራና ጨለማ ቅዱስ የእግዚአብሔር ፍጥረቶች ናቸው፡፡እኛ ግን ለጠላት “ግዛትህ ነው” ብለን ስለለቀቅንለት ቅዱሱ ፍጥረት የጠላት መገለጫ ሆኖ ተገኘ፡፡ጌታ እግዚአብሔር ጨለማ በፊቱ የተገለጠ ብርሃን ነው፡፡ጨለማን ለሰይጣን ሰጥተን ጠልተነው በሰባኪዎቻችንና በመነኮሳቱ ቀሚስ መውደዳችን ግን እጅግ የሚገርም ነው፡፡
      ሰው በቦታ አይከብርም ወይም አያርፍም፡፡እግዚአብሔር ካልቆመበት ቀኝ እግዚአብሔር የቆመበት ግራ ይሻላል፡፡አዳም በውቧ ኤደን ገነት ቢቀመጥም ከእግዚአብሔር ስለተለየ በገነት መካከል ተቀምጦ ስደተኛ ፣ያላረፈ፣ ተቅበዝባዥ … ነበር፡፡ እግዚአብሔር ከሌለባት ገነት እንኳ የስደተኞች ቅዱሳን ማረፊያ አትሆንም፡፡እግዚአብሔር እንጂ ቦታ አያሳርፍም፡፡ዛሬ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በአለም ካለው ኃጢአትና ነውር የማይተናነስ ክፋት ይሰራባቸዋል፡፡ለ“ቅድስና ተለይተው” ከአለሙ ያልተሻሉ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ቦታ ቢያሳርፍ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት ለብዙ ኃጢአተኞች ማረፊያ ሆነው በተገኙ ነበር፡፡በአንድ ወቅት በአንድ ቤተ ክርስቲያን ለህንጻ ማሰርያ ገቢ ማሰባሰቢያ ተብሎ በቢራና በሥጋ “የምግብ ባዛር” ተዘጋጅቶ ሳለ ፕሮግራሙን የሚመራው የመድረክ ሰው እንዲህ አለ፦ “ቅዱስ ጊዮርጊስን እየጠጣችሁ በእርሱ ትባረካላችሁ”፡፡(ጠጪዎችና ሰካራሞችን “የሚያጽናና ስብከት”)
     ጥቂት ያይደሉ ገዳማት፣አድባራትና አብያተ ክርስቲያናት በምንም መልኩ ከአለሙ ሥፍራ የማይሻሉ ናቸው፡፡የአምልኮ መልክ ይዘው የዕረፍት ቃልና መዝሙር የማያሰሙ አውደ ምህረቶችና አደባባዮችም ብዙ ናቸው፡፡ለዚህ ይመስላል በቀኝ ቆመናል እያልን በግራ ከምናስባቸው በሚበልጥ ክፋትና ነውር የተያዝነው፡፡ቦታ ቢያጸድቅ አዳም ከገነት የተሻለ የትም ሥፍራ አያገኝም፡፡