Monday, 31 March 2014

መልካም አገልጋይ ማን ነው ?


    ሳያነቡ የሚመረምሩ ፤ ሳይመረምሩ የሚተቹ ፤ በልማድ እውቀት የሚመላለሱ ፤ በደቦ ለስድብና ለድብደባ የሚጠራሩ ፤ ሳያምኑ የሚመሰክሩ ፤ በክርስቶስ ማዳንና ወንጌል ላይ  እልፍ አማራጭ የሚያኖሩ፤  ከልባቸው ሳይሆኑ አሜን የሚሉ፤ “ስለብልጥግና  ወንጌል” የፀጋውን ወንጌል የሚክዱ፤ እንኳን  ሳያዩ እያዩ እያነበቡ እየሰሙ የማያምኑ፤ በመልካም መሸነፍን  በባርነት  እንደመገት ጠልተው በክፉ  የሚሸንፉ፤ ስለእግዚአብሔር  መሳደብን  እንደፅድቅ  የሚቆጥሩትን ፤  “አንዳንዴ  በዋልድባም ይጨፍራል” በሚል ተረት  በእግዚአብሔር ጉባኤ በሥጋ አምሮት የሰከሩ … በእግዚአብሔር  አምልኮ ላይ እያመነዘሩ በአፋቸው ግን  እኔ ‹‹የጌታ መልካም ባርያ ነኝ›› የሚሉ  አማኞችን አይናችን ማየት ከጀመረ  ሰነባብቷል፡፡ 
    በፀሎት  ሳያጥሩ  የተዝረከረከ መታጠቂያቸውን  ጨብጠው   የሚቸኩሉ ፤  የእዩልኝና  ስሙልኝ  ድምፀትና ፉጨጽ ለማሠማት የሚንቀለቀሉ፤ በንግድ ብልሐት ካሴትና መፃህፍቱን  የሚሽጡ  ‹‹መንፈሳዊያን ነጋዴዎችን››፣ የደመቀ  መድረክና ኪስ የሚያሞቅ በጀትና አበል ያለበት እንጂ ለአንድ ነፍስ የማይገዳቸው ወሮ በል አገልጋዮችን፤ በህዝብ ጫንቃ እየኖሩ በህዝብ ላይ የሚቀማጠሉ፤ ፍትፍት ጎርሰው ምርቅ ስብከታቸውን የሚሰንጉ ፤ ድኃ ሲያዩ ቀሚሳቸውን ሰብሰብ አድርገው ፊታቸውን  አጨልመው  የሚራመዱ ባዕለጠጋ ሲያዩ  ደግሞ ቀሚሳቸውን  አንዘርፈው ጌታዋን እንዳየች ውሻ የሚቅበጠበጡ፤ ባዕለጠጋና  እግዚአብሔር  የተምታታባቸው… ስለገንዘብና  ክብራቸው ወንጌል የሚሸቃቅጡ ……  ከአፋቸው ግን ‹‹እኔ የጌታ አገልጋይ ባርያ ነኝ›› የሚሉ ለቁጥር  የሚታክቱ  አገልጋይ ካህናት ፤ ዲያቆናት፤  ሰባክያን፤ ዘማርያንን … እያየን ያላረርን ያልከሰልን ጥቂት አይደለንም፡፡
      ደቀ መዛሙርት በጻፉት መልዕክታት መግቢያ ላይ ራሳቸውን ‹‹የኢየሱስ ክርስቶስ ባርያ›› ብለው አስቀምጠዋል፡፡(ሮሜ.1÷1፤ፊሊ.1÷1፤ቲቶ1÷1፤2ጴጥ.1÷1፤ያዕ.1÷1፤ይሁ.1÷1)፡፡ባርያ የሚለው ቃል በግሪኩ ሁለት ትርጉሞች ያሉት ነው፡፡

Thursday, 27 March 2014

ጌታ መኖርያህ ነው!



በእድሜ ስልቻ በዘመን ቀልቀሎ
ማቱሳላ ኖረ ምንም ተሸክሞ?!
የቀደመው ጸጋ ዕድሜ ካስቆጠረ

Monday, 24 March 2014

ጸሎት - አሜን ሆይ በቶሎ ናልን! (ራዕ 22፣ 20)



    በቀደመው ብሉይ ኪዳን  ልጄ ወዳጄን እልክላችኋለሁ፤ መጥቶም ሰዎችን ሁሉ ከኃጢአታቸው ሁሉ በፀጋው ያድናቸዋል ብለህ ኪዳን ሠጥተህ እንደኪዳንህ ቃልህ ያልታበለ አብ አባት ሆይ ስግደት፤ አምልኮ ፤ሽብሸባ፤ ዝማሬ ፤ እልልታና ውዳሴ ከፍጥረት ሁሉ ተጠቅልሎ ለገነነው ድንቅ ስምህ ይሁን፡፡
    አቤቱ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ አንተ የፍጥረት ሁሉ ናፍቆት፤ “ያልተሠራ ልብስ ፤ ያልተፈተለ ቀሚስ ፤ ወደአባቱ ለመድረስ ጎዳና ፤ ወደወለደው ለመግባት የሚሆን በር እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው”  (ቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ) የተባለልህ መድኃኒታችንና ቤዛችን ሆይ እንዳንተ የሆነልን፤ ዋጋ ላልነበረን ዋጋችን ሆነኸን፤በሰማይና በምድር አግነህ ተወዳጆች ላደረገን፤ ወንድምና አባታችን ሆይ አንተን የምናመሰግንበት ብዕርና ቃል ገና አልተፈጠረምና በአርምሞና  በተመስጦ ምስጋናችንን በመንፈስ በበገና ቅኔ እንደረድርልሐለን፡፡
    መዳናችንን ያስታወቅኸን፤ ልጅነታችንን ለመንፈሳችን የመሰከርክልን፤ የክርስቶስን የመስቀል ሥራ በልባችን ፅላት ላይ የቀረፅክልንና እናየውም ዘንድ የረዳኸን፤ በሐዘናችንንና በስብራታችን ሁሉ ያፅናናኸን ወጌሻ ሆነህ የዳስስከን ማህየዊ መንፈስ ቅዱስ ሆይ ለፍጥረት አለቆችና ለምድር መላዕክት የሰጠነውን ስግደትና ምስጋና ውዳሴና ቅዳሴ ክብርና አምልኮ ነጥቀን ጰራቅሊጦስ ለምትሆን ላንተ፤ ለሥላሴ መንግስት ባለመታከት እናቀርባለን፡፡ አሜን፡፡
    አቤቱ ሆይ ! ጎረቤትነት በቂም መርዝ ተመርዟል፤ባልንጀርነት በሐሜትና በክህደት ተፈቷል፤  ወንድማማችነት በዕላቂ ገንዘብና በውርስ እዳሪ ደም ተቃብቷል፤ ቅስናው ልማድ፤ ድቁናው ወግ፤ ጵጵስናው ሹመት (ሺህ-ሞት) እንጂ ለመንጋህ መራራትን አላስተማረንምና፤ ሐሰት እንጂ እውነት ከክብሯ ተራቁታ ዕርቃንዋን ቀርታለችና…….. አቤቱ ጨርሰን ሳንጠፋ ናልን!

Tuesday, 18 March 2014

ግብረ ሰዶማዊነት - የዘመናችን መጻጉዕ (የመጨረሻ ክፍል)


Please read in PDF

    አንድ የምወደው ባልንጀራ ወዳጅ ዳኛ አለኝ፡፡ለብርቱ ጉዳይ እንደሚፈልገኝ በስልክ አቻኩሎ ጠራኝ፡፡አላመነታሁም … ከተሰየመው ችሎት ገብቼ አንድ ጉዳይ እንድሰማ ጋበዘኝ፡፡የአርባ ሁለት አመት ጎልማሳ የስድስት አመት ወንድ ህጻን በፈጸመበት ግብረ ሰዶማዊነት መቀመጥ እንደማይችል ብሎም በፊንጢጣ መቀደድ እንደሚሰቃይ ከውሳኔው ስሰማ ረዥም ዝምታ ከችሎቱ በኋላ ወደ ውስጤ ተሰማኝ፡፡(አቤቱ ይህን ሁሉ ለምን ታሳየኛለህ? ... ጥፋትና ርኩሰት መዋረድስ በመካከላችን ስለምን ሆነ?  … አቤቱ ምድሪቱ ለክፉዎች ተሰጥታለችና ጨርሶ ሳይጨልም ድረስልን!!!...የሚያቃጥል እንባ … መንፈስን የሚለበልብ የቁጣ ነበልባል … )
     መንግስት “ከብዙ ነገር አንጻር” ግብረ ሰዶማዊነትን በግልጥ ባይቃወምም በዝምታ ሊደግፍ እንደሚችል ታዝበናል፡፡ ቢያንስ እንደአሸን እየፈሉ የመጡትን እኒህን የሰዶም ሰዎች ሊያስተምር በሚችል መልኩ እንደወንጀል ህጉ ቀጥቶ አለማሳየትና አቀንቃኞቹን አለመግራት በግልጥ ከመደገፍ አይተናነስም፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ቤተ ክርስቲያን ለዚህ ነገር ትኩረት ሰጥታ አለመስራቷ ይበልጥ እጅግ የሚያደማ ነገር ነው፡፡ በተለይ በገዳም ባሉ ጥቂት በማይባሉ መነኮሳትና መነኮሳይያት ዘንድ ከሚሰሙ ነውሮች መካከል አንዱ ግብረ ሰዶማዊነት ነው፡፡ምናልባት እንዲህ ደፍሬ የምናገረው የቤተ ክርስቲያንን ነውር መግለጥ የሚያስደስት ሆኖ አይደለም፡፡ነገር ግን ማንቀላፋታችን አለልክ ስለበዛ ፣ይህ ነውር ሩቅ እንጂ እዚህ አፍንጫችን ሥር ያለ ስላልመሰለንና ጣታችንን በሌሎች እየቀሰርን የንስሐ ዘመናችንን በክስና በሽንገላ እየጨረስነው እንደሆነ ስለታየኝ ነው፡፡የማንክደው እውነት ግብረ ሰዶማዊነት በመካከላችን አለ፡፡መኖር ብቻ ሳይሆን ቁጥሩ ቢያንስም እንደሐገሪቱ ህግ የተቀጡና በማረሚያ ቤቶች ያሉ ሰዎችም አሉ፡፡

Sunday, 16 March 2014

ግብረ ሰዶማዊነት - የዘመናችን መጻጉዕ(ክፍል -1)


Please Read in PDF    
  
አንድ ማታ ስልኬ ምሽት አራት ሰዓት ገደማ ጮኸች፡፡ለማንሳት እያቅማማሁ ስልኬን አነሳሁት፡፡ “Hello” የሚለውን ቃል ከአንደበቴ ከማውጣቴ ተጨንቆ የሚያለቅስ የወንድ ልጅ የሲቃ ድምጽ ወደጆሮዬ አቃጨለ፡፡“ወንድ ልጅ ሳይሸነፍ እንዲህ እንደማይሆን” ውስጤ ሊደመደም አልዘገየም፡፡ከብዙ የማጽናናት ቃል በኋላ “ማታ ማታ ድቁና እናጠና ሳለን አንድ ወንድም በተለያየ ጊዜ ሲነካካኝ በወንድማዊ ፍቅር አስቤ ዝም አልኩት፡፡በሌላ ቀን ግን በጣም አጥንተን ደክሞኝ ስለተኛሁ ፈጸመብኝ፡፡ከዚያ ቀን በኋላ ሲደጋገምብኝ ከእርሱ ጋር ብቻ ሳይሆን እኔም ከሌላ ሰው ጋር ለመፈጸም ተነሳሳሁ፡፡እናም አንድ ቀን ሌላ ወንድሜን እየነካከሁት ሳለ ያልጠበቅሁት ቁጣ አገኘኝ፡፡ “ባልመለስ ለቤተሰቤም እንደሚናገር አስጠነቀቀኝ፡፡እናም ቀኑን ሙሉ ሳለቅስ ነው የዋልኩት፡፡ቢጨንቀኝ አንተ ጋ ደወልኩኝ፡፡እባክህን ምከረኝ፡፡ምን ላድርግ? … ”
      ብዙ የሚያለቅሱ አይኖች ፣መታበስ የሚፈልጉ የእንባ ዘለላዎችን አሰብሁ፡፡እናም ውስጤን አንዳች ነገር ሲንጠኝ ታወቀኝ፡፡ለአፍታ በመካከላችን ዝምታ ሆነ፡፡ይበልጥ እንዳይጨንቀው ፈርቼ “የእግዚአብሔርን ምህረትና ይቅርታ፤የሰውንም ልጅ ኃጢአተኝነት” አወራለት ገባሁ፡፡ዛሬ በእግዚአብሔር ጉልበት ይህ ወንድም ተመልሶ በቤቱ አለ፡፡
     ብዙ ጊዜ በተለያየ መንገድ ከሚደርሱኝ አስተያየቶች ትልቁን ስፍራ የሚይዙት “ጽሑፎችህ በጥናታዊ ይዘት ተደግፈው ስለማይቀርቡ የመረጃ እጥረት ይታይባቸዋል፤ ከወሬም ያላለፉ ናቸው” የሚለው ነው፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ኃጢአትን በተመለከተ ምን አይነት ጥናት ቢካሄድ እንደሚወዱ አልገባኝም፡፡እውነት እንናገር ከተባለ ቅዱስ ጳውሎስ የቆሮንቶስን ቤተ ክርስቲያን “በአጭር ቃል በእናንተ መካከል ዝሙት እንዳለ ይወራል የዚያም ዓይነት ዝሙት በአሕዛብስ እንኳ የማይገኝ ነው፥ የአባቱን ሚስት ያገባ ሰው ይኖራልና።”(1ቆሮ.5÷1) በማለት ሲናገር ከሰማው ነገር ተነስቶ እንጂ ምንም ስለኃጢአት በሰራው ጥናታዊ ጽሁፍ አይደለም፡፡ምነው ጥናታዊ ጽሁፍን ለኃጢአት ከማሰብ ለሌላ ነገር ብናውለውስ?

Monday, 10 March 2014

ምኩራብ



ቅዱስ ያሬድ የጌታን ጾም ሳምንታት በሠየመበት ስያሜው ሦስተኛውን ሳምንት ምኩራብ ብሎ ሰይሞታል፡፡ጌታ በምኩራብ ማስተማሩን፤መስበኩንና መፈወሱን ለማስታወስ፡፡ምኩራብ የእስራኤል ልጆች ወደባቢሎን በንጉስ ናቡከደነጾር በተማረኩ ጊዜ ጎበዛዝት ተግዘው፤ኢየሩሳሌም ባድማ ሆና መቅደሷም ፈርሶ ተፈታ በነበረችበት ወቅት በባዕድ ምድር እግዚአብሔርን ለማምለክ የሰሩት የአምልኮ ሥፍራ ነው፡፡የሄዱባት ባቢሎን ጣኦትና ቤተ ጣኦት እንጂ እግዚአብሔርና ቤተ መቅደስ አልነበሩባትምና አይሁድ የእግዚአብሔርን ፊት ለመፈለግ ፣ቃሉን ለማጥናትና ለጸሎት እንዲያመቻቸው በየሥፍራው ምኩራብን መሥራት ጀመሩ፡፡
   የእስራኤል ልጆች ከባቢሎን ምርኮ ተመልሰው ወደደሀገራቸው በተመለሱ ጊዜም ከመቅደሱ ጎን ለጎን ምኩራብን ሠሩ፡፡ምኩራብ በጌታ ዘመን ለአይሁድ ዋነኛ የአምልኮ ሥፍራ በመሆኑ ቅዱሳት መጻህፍትን በውስጡ በማከማቸት ፣ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በማንበብና በመተርጎም እንዲሁም እግዚአብሔርን ማምለክ የሚያዘወትሩበት ሥፍራ ሆነ፡፡
    በአንድ ሥፍራ ላይ ከሰባት እስከአስር ብዛት ያላቸው አባወራዎች ካሉ ምኩራብን እንዲሰሩ ይፈቀድላቸዋል፡፡ዋና አላማው በአንድ ሥፍራ ያሉ ወገኖች በቅርብ በመገናኘት ቅዱሳት መጻህፍትን እንዲያጠኑና እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ማድረግ ነው፡፡ የምኩራቡ አገልጋይም ዋና ሥራው ልጆችን ማስተማር፣ የቅዱሳት መጻህፍትን ጥቅልሎች ማቅረብ ፣ሌሎችንም ሥራዎችን መስራት ነው፡፡(ሉቃ.4÷20)
    አገልግሎቱ ስለማቋረጥና ብዙ ምኩራቦችም ስለነበሩ(ሐዋ.9÷2፤13÷3)በየቀኑና በየሰንበቱ ህዝቡ ሁሉ በአቅራቢያው ወዳሉት ምኩራቦች ይሰበሰብ ነበር፡፡(ሐዋ.13÷14፤17÷17)፡፡ የሚሰበሰቡት ሁልጊዜም ከላይ  ለሠፈረው ዓላማ ብቻ ነው፡፡ ምኩራብ ከመቅደስ ያነሰ መስዋዕት የማይቀርብበት የአምልኮ ሥፍራ ነው፡፡ጥቂት አባወራዎችና መንገደኞችም ጎራ እያሉ ቃሉን በማጥናት እግዚአብሔርን የመፍራት ጥበብ ይማሩበታል፡፡ 

Saturday, 8 March 2014

ምነው እንዲህ ቢቀር?

 
                             Please Read in PDF                

    
   አማኝ አለን ብለን እንደምንመካበት ትምክህታችን ሳይሆን ከአፍሪካ ምድር መሪ በመጥላትና ለመሪ ባለመጸለይ እንዲሁም ሰው በቁም የማይከበርባትና ሲሞት የሚገንባት ሀገር ኢትዮጲያ ከግምባር ቀደሞቹ አንዷናት ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ ሁልጊዜ ብዙ ሰው ሀገርን ስለመውደድ ሲጠየቅ ወገንና መሪን መውደድ ትልቁን ሥፍራ እንደሚይዝ ጭራሹን ያስተዋለው አይመስልም፡፡ ከሁሉ ይልቅ ቤተ ክርስቲያን የሞቱ መሪዎችን በክብር ስማቸውን አንስታ እየጠራች ስትጸልይላቸው  በህይወት ያሉትን ግን ከመጥራት ተዘልላ መቀመጧ እጅግ መንፈስን ያውካል፡፡
    ትውልድን የመቅረጽና ለመልካም ነገር የማንቃት ትልቁ ኃላፊነት የወደቀው የእግዚአብሔር መንግስት በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ላይ ነው፡፡ቤተ ክርስቲያን በቅድስና ከቆመች ዓለምን ያለንግግር መውቀስ ትችላለች፤በነውር ግን ከተመላለሰች የተቀደደና የተነወረ ልብሷን አይተው አለማውያንና አህዛብ ይጠቋቆሙባታል፤ይሰድቧታልም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ትልቁ የቅድስና ልብስና ራሷን የምትጠብቅበት የዝናርና የትጥቅ መሳርያዋ ደግሞ ቅዱሱ ወንጌል ነው፡፡
    እጅግ የሚያሳዝነው ነገር ቤተ ክርስቲያን ወንጌል ለመስበክ ያልደከመችበትን መሪና ህዝብን ለመቅበር “ትልቅ ሥነ ሥርዓትን” በማሳየት መድከሟ ነው፡፡ ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ ሲካሄድ የነበረውን የኦሮሚያ ክልል ፕረዘዳንት የቀብር ሥነ ሥርዓት በአይኖቼ ትክ ብዬ አየሁት፡፡ ከዚያም የቀደሙት ጠቅላይ ሚኒስትርን የቀብር ሥነ ሥርዓት በህሊናዬ አሰናሰልኩ፡፡በኋላ ላይ ግን ወደውስጤ የመጣው፦ 

Wednesday, 5 March 2014

በታናሽነትህ



በዕድሜ የተናቀ ሳሙኤላዊ
የነገድ ትንሽ ጌዴዎናዊ
ብላቴናነት ኤርምያሳዊ
ከሰው ያነሰ ትል ዳዊትነት
ጭንጋፍ የመሆን ጳውሎሳዊነት
ገረድ አገልጋይ ማርያማዊነት
ይወደዳሉ ይታሰባሉ
በአዶናይ ፊት ዋጋ ያወጣሉ፡፡

Monday, 3 March 2014

ለሰዎች እንደጦመኛ አትታዩ (ማቴ.6÷16)




       ጾም ለእግዚአብሔር መንፈሳዊ አምልኮአችንን ከምንገልጥባቸው መንገዶች አንዱ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም በዓላማ ከምናደርጋቸው ዝግጅቶችም አንዱ የጾም ዝግጅት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ጾምን በማያሻማ መልኩ መጾም እንደሚገባን አስረግጦ ይነግረናል፡፡ጌታ ይህን ትምህርት በሚያስተምርበት ወራት በአይሁድ ዘንድ ጾም የታወቀና የተረዳ ነገር ነበር፡፡ ምንም እንኳ መንፈሳዊ መልኩና ለዛው ፈጽሞ በግብዝነት የጠወለገ ቢሆንም፡፡
     አይሁድና አህዛብ ራሳቸውን በእግዚአብሔር ፊት ለማዋረድ የቀናውን መንገድ ለመለመን (ዕዝ.8÷21፤መዝ.69÷10)፣ ስለህዝብና ስለዓለም ሁሉ ስለራስም በደልና ኃጢአት በማዘንና በመጸጸት ለመናዘዝ (ነህ.9÷1-2)፣ ንስሐ ለመግባትና እግዚአብሔር ሊያመጣ ያለውን ቁጣ እንዲተወውና በምህረትና በይቅርታ ህዝቡን ይቅር እንዲል (ኢዩ.2÷12፤ዮና.3÷5-10)፣ የእግዚአብሔርን ሃሳብና ፈቃድ ለማወቅ ፣መገለጥንና ጥበብን ለማግኘትም (ዳን.9÷3) … ለተለያዩ ብዙ ምክንያቶች አይሁድ ጾመዋል፡፡