“እኛ ኢትዮጲያውያን” የሚለው ሃሳብ “ደምና አጥንታችንን ገብረንላታል”
ለሚሉ አርበኞች ልብ የሚመላ ነገር አለው፤ በጥንት በሕገ ልቡና፣ ቀጥሎም በሕገ ኦሪት ከዚያም በክርስትና መኖሯን ለሚያምኑ ደፍረው
የሚሉት ነገር አላቸው ፤ በአክሱምና በዛጉዌ የታነጹትን ሐውልትና ህንጻ አብያተ ክርስቲያናትን ለሚያደንቁ አርክቴክቸሮችና ሌሎች፥
እጃቸውን በአፋቸው ጭነው ብዙ የሚተነትኑት ነገር አላቸው፤ ሁሉም በየሙያውና በያለበት ደረጃ ስለኢትዮጲያችን ቢጠየቅ የሚለው ብዙ
ብዙ አለው፡፡
ሃሳቤ ግን ወዲህ ነው፤ አጼ ቴዎድሮስ በጥር 22 በ1858 ዓ.ም ለእንግሊዛዊቷ
ንግሥት ለቪክቶሪያ በኢትዮጲያ ምድር ከታሠሩት የእንግሊዝ እስረኞች ጋር በተያያዘ፤ እንዲሁም ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ሲያስቀምጡ፦ “የኢትዮጲያን ሰዎች ድንቁርነታችነን ዕውርነታችነን ሣይሰሙት አይቀሩም ያማረ
መስሎኝ ደፍሬ የላክሁብዎን ከፍቶብኝ (አጥፍቼ እንደሆነ) ቢገኝ ይምከሩኝ እንጂ አይክፉብኝ፡፡ እግዚአብሔር የመረጠዎ ንግሥት ዓይንዎ
የበራ ነውና፡፡”(ጳውሎስ ኞኞ ፤ ዐጤ ቴዎድሮስ
፤ ግንቦት 1985 ፤ ቦሌ ማተሚያ ድርጅት ፤ አዲስ አበባ ፤ ገጽ.214)
አሁንም በድጋሚ በሚያዝያ 10 ቀን 1858 ዓ.ም ለዚህችው ንግሥት ድጋሚ
በጻፉት ድብዳቤ እኛን ኢትዮጲያውያንን እንዲህ ገልጠዋል፦ “ የኢትዮጲያ ሰዎች እውር ነንና ዓይናችነን ያብሩልነ፡፡ እግዚአብሔር
በሰማይ ያብራልዎ፡፡” በማለትም በግልጥ አስቀምጠዋል፡፡ (ጳውሎስ ኞኞ ፤ ዐጤ ቴዎድሮስ ፤ ግንቦት 1985 ፤ ቦሌ ማተሚያ ድርጅት ፤ አዲስ አበባ፤ ገጽ 233)