Friday, 29 November 2013

ሩጫውን ወይስ ሩጫዬን ጨርሻለሁ?

በመጽሐፍ ቅዱስ ካልተጻፉ ነገር ግን እንደተጻፉ ተደርገው በየመድረኩ ከሚጠቀሱልን ጥቅሶች መካከል አንዱና ዋናው ጥቅስ ቅዱስ ጳውሎስ ለቅዱስ ጢሞቴዎስ የጻፈው “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋ ጅቶልኛል፥ …” (2ጢሞ.4÷7) የሚለው ቃል ነው፡፡
      ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በህይወት ዘመናቸው በዙርያቸው ካሉትና ከሩቁ ብዙ ስድብ ፣ነቀፌታንና ትችትን የጠገቡ አባት ናቸው፡፡እንዳለመታደል እነዚያ ይጠሏቸውና በድብቅ በስድብ ይዘምቱባቸው የነበሩት ሰዎች ቅዱስ ፓትርያርኩ በቁም ሳሉ ያልተናገሩትን ሲሞቱ ቁጣቸውን፣ ተግሳጻቸውን፣ ምክራቸውን ወጣ ወጣ ሲያደርጉ አይተናል፡፡ (በእርግጥ እሳቸውም ሰው ናቸውና ይደክማሉ፤ደክመውም ይዝላሉ፡፡ ስህተት አይቶ ከመርገም፦ እንዲመለሱ ፣እንዲታነጹ ያኔውኑ ነበር በግልጥ መግለጡ … ሳይመክሩና መንገድ ሳያሳዩ ቁጣ እንዴት ያለ ስንፍና ነው?) ወደሐሳቤ ልመለስ፡፡
      እሳቸው ባረፉ ሳምንት በ“ታላቁ” የአራት ኪሎው የሥላሴ ካቴድራል ላይ የተለጠፈው “ትልቅ ስቲከር” እንዲህ ይላል፦    
             “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫዬን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን
              ጠብቄአለሁ፤ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥” (2ጢሞ.4÷7)፡፡

ምናልባት እሳቸው ናቸው የጻፉት ወይም የፊደል ግድፈት ነው እንዳንል በየትኛውም ቤተ ክርስቲያን ጀርባ ዘወር ብላችሁ የተጻፉ የመቃብር ላይ የዚህን ክፍል ጽህፈቶች ብትመለከቱ ተመሳሳዩን ለማየት አትቸገሩም፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ “ሃይማኖትን ጠብቄያለሁ” የሚለውን ቃል ጭምር “ሃይማኖቴን ጠብቄያለሁ” ሲሉም ይደመጣሉ፡፡ (የእኔ ብቻ ለማለት ይሆን ክርስትናውን?)
      ይህን ተመልክተን በመጨረሻ የምንደርስበት ድምዳሜ ከታላቁ እስከታናሹ ፣ከሰባኪው እስከተሰባኪው … ቃሉን በህይወት ከመተርጎም ባሻገር በንባቡ እንኳ ያለማስተዋል ከባድ ችግር እንዳለብን ነው፡፡
       ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ልጁ ቅዱስ ጢሞቴዎስን በብዙ ምስክር ፊት የሰማውን ቃል እንዲመሰክርና መከራን በመቀበል ከሙታን የተነሳውን፣ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በማሰብ በትጋት እንዲያገለግል ሊመክረው ከተጠቀመበት ምሳሌዎች አንዱ ሩጫ ነው፡፡(1ጢሞ.2÷2-8)፡፡

Tuesday, 26 November 2013

ሳይሰሙ መጋል

     ከሸክላ ምጣድ ጠባያት አንዱ ሳይሰማ አለመጋሉ ነው፤ መስማት (መሞቅ) የክርስቲያን ልዩ ጠባዩ ነው፡፡ በክርስትና መቀዝቀዝ አይቻልም፤ ዳግመኛ ወደኃጢአት ቆፈን ወደባርነት እንድንገባ አልተፈቀደልንም፤ (ገላ.5፥1)፡፡ ለማንም የማይመች ለብታም አይሆንልንም፤ ወይ በአግባቡ መስማት (መሞቅ) ወይም ደግሞ ቀዝቅዞ በገዛ እጅ ራስን ከእግዚአብሔር መለየት፡፡ ከብርሐንና ከጨለማ አንዱን መምረጥ እንጂ ሌላ ሦስተኛ ምርጫ አልነበረም፤ አይኖርምም፡፡
      በአንድ ወቅት እንዲህ ሆነ ይባላል፥ ሦስት እንደሰሙ የሚግሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ስለምናኔ ሲነገር መናኝ፣ ስለቅዱስ ጋብቻ ሲነገር ማግባት፣ ስለሰባኪ ሲነገራቸው ሰባኪመሆን የሚያምራቸው በተጣዱበት ሁሉ የሚሰሙ ነበሩ፤ በመጨረሻም መናኝ መሆን አማራቸውና፥ እንደተነገራቸው ሽንብራ ይዘው ወደገዳም ገቡ፡፡ ከብዙ ጾምና ጸሎት ጋር በቀን በሥላሴ ምሳሌነት ሦስት ፍሬ ሽንብራ ሊበሉ ወሰኑ፤ ነገር ግን አልቻሉም፡፡ በሚቀጥለው ቀን በስድስቱ ቃላተ ወንጌል ምሳሌ አሉና፥ ስድስት ስድስት ፍሬ ቢበሉም አልቻሉም፤ በሚቀጥለው ቀን በአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት፣ ቀጥሎም በሐያ አራቱ ካህናተ ሰማይ እንዲህ እያሉ ቢሄዱም ስላልተቻላቸው፥ በመጨረሻ በእልፍ አዕላፋት መላዕክት ብለው የያዙትን ጨርሰው ወደቤታቸው ተመለሱ ይባላል፡፡

Friday, 22 November 2013

የእግዚአብሔር ትራፊ

ከግምት ከበዛው ከማይቆጠረው
ከተትረፈረፈው ጨብጠን ከያዝነው
ከአምስቱ አሳና ከሁለቱ እንጀራ
አለን ከምንለው ከኛ ብዙ ዝና
ይደንቀኛል ይገርመኛል የአምላኬ ሥራ!!

Tuesday, 19 November 2013

ነፍሴ አንተን ብቻ



ወንድሜን አሳዳጅ ቃየላዊ እብደቴ፣
ጥርጥር የሚነዳው ዲዲሞስነቴ፣
ኬፋዊ ግርግር ችኩል የሚያሮጠው
ሄሮድሳዊ መርገም የህፃን ደም 'ሚጥመው፣

Sunday, 17 November 2013

" 'ከወይን እሾህ' ይለቀማልን?"(ማቴ.7÷16)


ከወራት በፊት  አንድ አሁንም በህይወት ያሉ ሊቀ ጳጳስ ኤርትራ ካለው "የተቃዋሚ ጦር ቀጠና" በመገኘት ኢትዮጲያን እንዲወጉ መድፍና ታንኩን መትረየስና ቦንቡን "ባርከው"መመለሳቸውን ሰምተን ነበር፡፡(ይታያችሁ አሁንም ሊቀጳጳስ ሆነው አሉ!? "የሚረግሟችሁን መርቁ" የሚለውን ቃሉን ያስተምሩ ይሆን?!!)፡፡ሰሞኑን ደግሞ ሳውዲ አረቢያ ከዜጎቿ ውጪ ባሉ የውጪ ነዋሪዎቿ ላይ በወሰደችው እርምጃ ከሐገር ቤት ከአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት አንገት የሚያስደፋ ከአንድ ክርስቲያን ማህበረሰብ የማይጠበቅ ጸሎት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ካባ አልብሰው  ሲሉና "ምላሹም እንደተገኘ" ሲናገሩ ሰምቼ ተክኜ በመንፈሴ ተበሳጭቻለሁ፡፡(ይታያችሁ ሶማሊያ፣ሳውዲ አረቢያ፣ፊሊፒንስ፣…. ከሰሞኑ በከባድ የጎርፍ አደጋ ተመተዋል፡፡ሳውዲ አረቢያ በእኛ ጸሎት እንዲህ ከሆነች ሌሎቹን "መአተኛው" እግዚአብሔር በማን ጸሎት ይሆን በጎርፍ የመታው?!)
    በሐገራችን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ "በማዕረጉ ታች ያለ ዲያቆን" የአንዳንድ ቀሳውስትና ጳጳሳትን የጨለማን ሥራ ገልጦ ከወቀሰና ከሥራው ጋር ላለመተባበር ወስኖ አቋሙን በግልጥ ካሳወቀ(የሚበዙ “Business ተኮር" አገልጋዮችን አያካትትም) እስከመወገዝ ያደርሰዋል፡፡ውግዘት ፍራቻም ብዙዎች "ጆሮ ጭው የሚያደርግ ነውርና ኃጢአት" በመካከላችን እየተሰራ እያዩ ገለል ብለው አልፈዋል፡፡እኔም ውግዘትን ሳልፈራ ቀርቼ አይደለም ግና ስለክርስቶስ ኢየሱስ ምናልባት የተናቅሁ ሆኜ ከተገኘሁ "የይበቃናል እንመለስ" ጥሪዬን በደሙና በመንፈስ ቅዱስ ጉልበት ለመጮህና ጥቂቷን መክሊቴን መቅበር ስለሌለብኝ ነው፡፡በተረፈ የማንም ቅጥረኛና ተላላኪም አይደለሁም፡፡ከምንም በላይ ቤተ ክርስቲያን በቅድስና ያለእድፈትና ፊት መጨማደድ ክርስቶስን አጊጣ ማየት የዘወትር ናፍቆቴ ነው፡፡

Thursday, 14 November 2013

በከንፈሩ የሚያከብር ህዝብ(ኢሳ.29÷13)


         ሰሞኑን ከወደምድረ ዓረብ ስለሰማሁትና ስላየሁት ነገር እንዲህ አልኩ…!!!
         በመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ዘንድ "ደረቅ አዲስ ኪዳን" እየተባለ የሚጠራው መጽሐፉ፣ኢሳይያስ የስሙ ትርጓሜ "እግዚአብሔር ያድናል" ማለት ነው፡፡በነቢዩ ዘመን ይሁዳና ህዝቦቿ "የእስራኤልን ቅዱስ" ተወዳጁን ጌታ ንቀውና አቃለው ነበር፡፡ከህዝቡም ኃጢአትና ነውር የተነሳ የእርሻው ቡቃያ ተዘርቶ ሊሰጥ ከሚገባው እጅግ አነስተኛውን የሰጠበት ዘመን ነበር፡፡(ኢሳ.5÷9-10)የእግዚአብሔር ቃል በዘመኑ ለባለራዕዮችና ለነቢያት እንኳ ሳይቀር የተዘጋና የተሰወረ ሆኖም ነበር፡፡(ኢሳ.29÷10)
       መስዋዕቱ፣ቁርባኑ፣የመቅረዙ መብራት፣ዝማሬው ፣ቃሉን መስማት ፣መስገዱ ፣መጾሙ፣መጸለዩ፣…. ያልተጓደለበት ነገር ግን ይህ ሁሉ ሆኖ ህዝብና መሪ በአንድ ያበደበት፣ነቢዩ ከጠንቋይ የተስማማበት፣ አዝማሪ ከዘማሪ የተቋመሩበት፣መሪው በጉቦ አይኑ የታወረበት ፣ሰባኪ ከዘማሪ በዝሙት የረከሰበት፣ህዝቡ "በአስረሽ ምቺው" ኃጢአት የተካነበት፣ካህኑና ዲያቆኑ ተማክረው ሙዳየ ምጽዋት ሰብረው የሚሰርቁበት፣ ህዝቡ ላየው ሁሉ ልቡን የሚከፍትለትን ይህን የእኛን ዘመን ይመስላል የነቢዩ ዘመን፡፡
      ይሁዳ ዕለት ዕለት እግዚአብሔርን የምትፈልግ ፣መንገዱን ለማወቅ የምትጓጓ፣ትዕዛዙን እንዳልተወች፣    እግዚአብሔር ወደእርሷ እንዲቀርብ የምትወድ ፣የምትጾም፣ራስዋን ያዋረደች … ብትመስልም ነገር ግን ሠራተኞችን የምትበዘብዝ፣ጾሟ ከጥልና ከክርክር ያልጸዳ፣ በግፍና በጡጫ የምትደበድብ … ነበረች፡፡(ኢሳ.58÷1-4)፡፡