Please read in PDF
የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ዋቢ ያደረገው ዓቢይ ጾም፣ የጾሙ ሳምንታት በየራሳቸው
ስያሜ አላቸው፤ ስያሜዎቹን የሰየመው “የዜማ ደራሲው” ያሬድ ሲኾን፣ የጌታ ኢየሱስን ሕይወቱንና ትምህርቱን ከወንጌላት በመውሰድ
የሰየማቸው ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኢ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የኾኑ ብዙ ትምህርቶች ያሉትን ያህል፣ ከጅማሬአቸው
መልካም የነበሩና አኹንም ድረስ በመልካም ምሳሌነት የተያዙን አንጥሮ፣ በመጽሐፉ ቃል መዝኖ መቀበል ደግሞ ለእኛ ለአማንያን የተተወ
ነው። ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተገኘውን ኹሉ እንድንቀበል ሳይኾን በመጽሐፍ መዝነን እንድንቀበል ቃሉም መንፈሱም ይመክሩናልና።
የዚህኛው ሳምንት ስያሜ ገብር ኄር ይባላል፤ ትርጉሙም መልካም ወይም ትጉህ
ባርያ ማለት ነው፤ ይህ ስያሜ ደግሞ የተወሰደው ከማቴ. 25፥14-30 ወይም ከሉቃ. 19፥12-27 ካለው የወንጌል ክፍል ነው፤
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ክፍል የተናገረው ለሞቱ ወደ ኢየሩሳሌም እየወጣ በነበረበት ወራት ነው፤ በተናቁትና በተገፉት፣ በኢየሩሳሌማውያን
ፈጽመው በማይወደዱት ገሊላውያንና መንደሮቿ መካከል የቆየውና የነበረው ጌታችን ኢየሱስ፣ አሁን ለሞቱ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቷል። በገሊላ
የነበሩት እጅግ የተናቁ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ኃጢአተኞችና በኢኮኖሚም ደረጃ እጅግ ዝቅ ያሉ፣ ከፍተኛ የሥነ ልቡና ጫናም የነበረባቸው
ሰዎች ጭምር፤ ኢየሩሳሌም ደግሞ በሕጉ የሚመኩና የሚመጻደቁ፣ አግላይና ናቂ፣ ትእቢተኞችና ራሳቸው ብቻ የመሲሑ ተቆርቋሪ እንደ ነበሩ
አድርገው የሚያስቡ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውን የበዙባት ከተማ ነበረች።