Saturday, 29 August 2015

ድንግል ማርያም በድንግል ማርያም አንደበት (ክፍል - 3)

1.    ምስጋና
       ለምስጋና የተሟሸ ቃል የምናወጣው፥ መንፈስ ቅዱስ አንደበታችንን ሲቃኘውና እኛም ቃሉን ከጸሎት ጋር በማጥናት የበሰለ ማንነትን መያዝ ሲቻለን ነው፡፡ እንዳንዶች ተአምራቱን አይተው ድንቅ መዝሙርን (ዘጸ.15፥1-21) ፤ አንዳንዶች በፊቱ ራሳቸውን በማፍሰስ ላደረሱት ጸሎት ምለሹን ከለመኑት ጌታ ባገኙ ጊዜ (1ሳሙ.2፥1-10) ፤ ሌሎች ደግሞ ድልን በፊቱ ባገኙ ጊዜ (መሳ.5፥1-31 ፤ 16፥24) ፤ የበረቱቱ ደግሞ ሙሉ ተስፋቸው እግዚአብሔር መሆኑን በመታመን (ዕን.3፥1-19) በእግዚአብሔር ፊት እንደዘመሩ ድንግል ማርያምም ልዩና ድንቅ ነገር በእርሷ እንደተደረገ ባመነች ጊዜ በቃሉ መሞላት ውስጥ ሆና የዘመረችው መዝሙር እጅጉን ልብ የሚነካ ነው፡፡
      አባቷ ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት (ማቴ.1፥20 ፤ ሉቃ.1፥27 ፤ 32) በገና እየደረደረ መልካም አድርጎ ይዘምር የነበረ መዝሙረኛ (1ሳሙ.16፥18-23 ፤ መዝ.33፥2) ፤ የመዝሙር መጽሐፎቹም በምስጋናና በውዳሴ እጅግ የተመሉ ነበሩ፡፡ (መዝ.111-117) ድንግል ማርያምም ከእርሱም ተምራለችና በምስጋና ተመልታ ስታመሰግን እናያታለን፡፡ ቃሉም ፥ “… በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና።” (1ተሰ.5፥17-18) እንዲል፡፡
       ምስጋና የማጉረምረም ፤ የሽንገላ ፤ የሐሰተኝነት ፤ የስድብና ያለማመስገን ተቃራኒ ነው፡፡ (ዘጸ.16፥2 ፤ ዘኊል.14፥26-30) ዲያብሎስ ዘማሪ ስለነበር ፥ ከዚህ ክብሩ በገዛ ትዕቢቱ ሲዋረድና ሲወርድ ሸንጋይ (ኤፌ.4፥14 ፤ 6፥11) ፣ የእግዚአብሔርን ክብርና ሥራ በመንቀፍ የሚሳደብ (መዝ.74፥10 ፤ ኢሳ.52፥5 ፤ ራዕ.13፥5) ፣ በድምጹ ብቻ እያገሳ የሚያስፈራራ (1ጴጥ.5፥8) ፣ ሐሰተኛ (ዮሐ.8፥44) ሆነ፡፡ ለዚህም ነው እግዚአብሔርን (ዘሌ.24፥16 ፤ 1ነገ.20፥10) ፤ እናትና አባቱን የሚሰድብ (ዘጸ.21፥17 ፤ ምሳ.20፥20) እንዲገደል ፍርዱ እንዲሆን በሕግ የተደነገገው፡፡

Wednesday, 19 August 2015

አርሞንዔም - ጌታ ክብሩን የገለጠበት ተራራ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከስድስት ቀን በፊት በጥንት ስሟ “ፓኒያስ” ፥ በአሁን ስሟ ደግሞ “በናያስ” በምትባለው ከገሊላ ባሕር በስተሰሜን ከሔርሞን ተራራ ተዳፋት ሥር በነበረችው በፊልጶስ ቂሣርያ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ፡፡” (ማቴ.16፥13) ንጹሐ ባሕርይው ጌታ፥ ደካሞችና ገና በእውቀት ያልጎለመሱትን ደቀ መዛሙርት “ሰዎች ማን ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም የሰሙትን ሁሉ ሳያስቀሩ ነገሩት፡፡ “አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው” ብለው ተናገሩ፡፡ ሰዎች ስለጌታ የሰጡት ስያሜ፥ ቀርበውት ያዩት ወይም ከእርሱ የሰሙት አይደለም፡፡ የየራሳቸውንና ከሌሎች ጋር ሲያወሩት የደረሱበት “እምነታቸውን” እንጂ፡፡
      ሰዎች ስለእኛ የሚሉት አንድ ነገር ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገር አላቸው ፤ የሚሉት ነገርም ከእኛ ጋር ምንም ዝምድና ያለውም ፤ የሌለውም ሊሆን ይችላል፡፡ ሰዎች ስለጌታ የተናገሩት ከእርሱ ጋር ምንም ዝምድና የሌለውን ነው፡፡ እኛም በተለይ ከታወቀ ነውርና ከኃጢአት ሕይወት ነጽተን በእውነተኛው በጌታ ወንጌል አገልግሎት ውስጥ ስንመላለስና ቤተ ክርስቲያንን በቅዱስ ቅንአት ስናገለግል ብዙ ጊዜ የምንባለው፥ ከእኛ ጋር ምንም ዝምድና የሌለው ነገር እንደሆነ ከዚሁ ለጌታ ከተነገረውና ከደቀ መዛሙርቱ ሕይወት እንማራለን፡፡ (ማቴ.9፥34 ፤ 12፥24 ፤ ሐዋ.21፥37-38 ፤ 24፥5-6) ስለዚህ ብዙ መባላችን ፤ ተብሎም በድርጊት ቢገለጥ ምንም ሊያስደንቀን ፤ ሊያስበረግገንም አይገባም፡፡ (1ጴጥ.4፥12)
    ጌታችን ሁሉንም ነገር ከደቀ መዛሙርቱ ካደመጠ በኋላ ጥያቄውን፥ “እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ?” በማለት የጥያቄውን አቅጣጫ ወደእነርሱ ቀየረው፡፡ በአገልግሎት አለም ከብዙ አማኞችና አገልጋዮች ሕይወት የራቀው ጥያቄ ቢኖር ይህ ጥያቄ ነው፡፡ በዙርያችንም ያሉ ይሁኑ ከአጠገባችን ያሉ ምን እንደሚሉን በትክክል አለመረዳት ብዙ ጊዜ የንስሐ በራችንን እንኳ ሲዘጋብን ከማስተዋል እንዘነጋለን፡፡ አንድ አገልጋይ ወይም አማኝ የእግዚአብሔር ቤት እውነተኛ አገልጋዮችና አማኞች ለእርሱ ያላቸውን ነገር በሚገባ ማጤን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ይህን ስል አገልግሎቱን ሁሉ በጌታ ከመደገፍ ይልቅ በእነርሱ ቅኝት ሊመራ ይገባዋል እያልኩ አይደለም፡፡

Saturday, 15 August 2015

እንደብዙ አጋር!


          Please read in PDF


እንደሚራራ እንደሚያሻግር
እንደሚያጽናና እንደሚያፈቅር
ከጐን እንዳለ ቀኝ ደግፎ
በብርታት ቆሞ በድካም ታቅፎ

Tuesday, 11 August 2015

ድንግል ማርያም በድንግል ማርያም አንደበት ስትገለጥ(ክፍል - 2)



         ድንግል ማርያም የክርስቶስ የቃሉ ሙላት እንዳላት በታላቁ መጽሐፍ ከዘመረችው መዝሙር ዋቢ ብንጠቅስ ፥ ለምሳሌ ፦
  
       ነፍሴ ጌታዬን ታከብረዋለች ፤ (መዝ.34፥2 ፤ 44፥8 ፤ 103፥1-4) ድንግል ማርያም የወለደችውን ጌታ “ጌታዬ” ብላ ታከብረዋለች ፤ ታመልከዋለችም፡፡ “ድንግል ፈጣሪዋን ወለደች” እንዲል ፤ እርሷ ፈጣሪዋን ታከብረዋለች ፤ በፍርሃት ታመልከዋለችውም፡፡
       መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች ፤ ( መዝ.18፥46 ፤ 42፥11 ፤ 43፥5 ፤ 69፥32 ፤ 107፥42 ፤ 119፥74 ፤ ኢሳ.45፥15-17 ፤ 45፥21 ፤ 61፥10 ፤ ኤር.9፥24 ፤ ሆሴ.13፥4 ፤ ዕን.3፥18 ፤ 1ጢሞ.2፥3 ፤ 4፥10) የወለደችውን ያንኑ ጌታዋን “መድኃኒቴ” ብላም ትጠራዋለች፡፡ መድኃኒቱ ለእርሷም ፤ ለእኛም ፤ ለአለሙ ሁሉ ነውና፡፡

Friday, 7 August 2015

ድንግል ማርያም ፥ በድንግል ማርያም አንደበት ስትገለጥ (ክፍል - 1)

    
                                          Please read in PDF

  የዘመኑ ፍጻሜ ሲደርስ (ገላ.4፥4) በገሊላ ግዛት ናዝሬት በምትባለው ከተማ፥ የሚያስደንቅ የምሥራች  ዜና ተሰማ፡፡ ምሥራቹም በኃጢአት የተበከለው ዓለም ሊቀደስ ፣ ለዓለሙ ሁሉ የሚሆን ምሥራችና መድኃኒት ሕጻኑ ኢየሱስ ሊወለድ እንዳለ ፣  መልአኩ ገብርኤል ከመለኮት ዙፋን ችሎት የተቆረጠውን ውሳኔ ሊያሰማ ወደምድር መጣ፡፡ (ሉቃ.1፥26) ናዝሬት በሰው ሕሊና “መልካም ሰው አይወጣባትም ወይም አይገኝባትም” (ዮሐ.1፥47) ብትባልም፥ ዛሬ ግን መልካም ሰው ድንግል ማርያም ተገኝቶባታል፡፡

Monday, 3 August 2015

ክርስቶስን በሚያባብል ቃል ለምን? (የመጨረሻ ክፍል)



ኃጢአትን በማለዘብ አንቃወምም!

       እንኪያስ! ኃጢአትንና ኃጢአተኝነትን በማለዘብ ወይም በማድበስበስ አንቃወምም፡፡ መቃወም ያለብን ፊት ለፊትና በድፍረት ነው፡፡ ወንጌልን ለመስበክ የምንደፍርበትን ድፍረት ኃጢአትን ለመቃውም ካልደፈርንበት ምስክርነታችን በጌታ ፊት የተናቀና የተጣለ ነው፡፡   በተለይም ተመክረው ፣ ተዘክረው ፣ ተወቅሰው ፣ ተገስጸው ፣ ተለምነው ፣ በቁጣም ቃል ብዙ ተብለው አልሰማ ፤ አልመለስ ያሉትን ሐሰተኛ የአዞ እንባ አንቢ አባባዮችን እንደአረመኔና እንደቀራጭ ቆጥሮ (ማቴ.18፥17) ያለፍርሃት መቃወም አገባብ ነው፡፡