4. የመቶ አለቃው ዩልዮስ (ሐዋ.27፥43)
“የመቶ አለቃው ግን ጳውሎስን ያድነው
ዘንድ አስቦ ምክራቸውን ከለከለ … ”
ቅዱስ ጳውሎስ ለቁጥር በሚታክቱና ምላሳቸው በሳለ ከሳሾች መካከል “እየተብጠለጠለ” ቅንጣት ታህል አለመፍራቱን ሳስብ
የጌታ ኢየሱስ “ … አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ፥ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤
በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፥ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና፡፡” የሚለው የትንቢት ቃል መፈጸሙን ትዝ ይለኝና
ልቤ ይረካል፡፡(ማቴ.10፥19-21) የእስያ አይሁድ፣ የኢየሩሳሌም አይሁድ፣ ጠርጠሉስ፣ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ … ስለእርሱ በጎነት
የላቸውም፡፡ ፊስጦስም እንደቀደሙት ባዕለ ሥልጣናት ክፉ ልማድ አይሁድን ደስ ለማሰኘት ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ተመልሶ እንዲዳኝ ይጐተጉተዋል፡፡(ሐዋ.25፥9፤21)
ቅዱስ ጳውሎስ ነገሩ እንዳላማረ፤ ፊስጦስ ራሱ ወደአይሁድ እንዳደላ ያወቀ ይመስላል፡፡ አሁን በቆመበት የሮማ የፍርድ
ችሎት ፊት መዳኘት እንደሚፈልግ በጽናት ተናገረ፡፡ ምክንያቱም በአይሁድ ሸንጎ ፊት ቢዳኝ የልባቸውን ክፋት ያውቀዋል፡፡ ይገድሉታልና፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ለሌለው ሞት ራሱን አሳልፎ አልሰጠም፡፡(ዮሐ.8፥59) ጳውሎስ “ሰማዕትነት አያምልጠኝ” ብሎ ለስንፍና ሞት
ሳይሸነፍ ወደቄሳር ይግባኝ በማለት በሮማዊ ዜግነቱ የተሰጠው መብቱን ተጠቀመበት፡፡(ሐዋ.25፥11)