2. የቂሳርያው የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ(ሐዋ.10፥1-48)
ቆርኔሌዎስ ከቤተ ሰዎቹ ሁሉ ጋር “እግዚአብሔርን የሚያመልክና የሚፈራ
ሰው” ነበር፡፡ እግዚአብሔርን የመፍራቱና የማክበሩ መገለጫ እግዚአብሔርን ያከብራል(ሐዋ.10፥22)፣ ለህዝቡ እርዳታና ቸርነትን
ያደርጋል፤ የጸሎት ህይወትም ነበረው፡፡(ሐዋ.10፥2) ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ የአይሁድን ሥርዐት በመከተል አልተገረዘም፣ ምስክሮች
ባሉበት የውኃ ጥምቀት አልተጠመቀም፤ በመቅደስም መሥዋዕት አላቀረበም፡፡ ይህ ደግሞ አህዛብ ወደይሁዲ እምነት እንዳይመጡ ከልካይ
ከነበሩት ሥርዐት ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች ነበሩ፡፡
ከአህዛብ ወደአይሁድ እምነት ሙሉ ለሙሉ የገባና ሥርዐታቸውን ሳያጓድል
የሚፈጽም ባይሆንም፤ ቆርኔሌዎስ በአንድ አምላክ አምኖ የአይሁድን ሃይማኖትና ምግባር የሚከተል ሰው ነበር፡፡ ለምሳሌ፦ እንደአይሁድ
ሥርዐት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ይጸልይ ነበር፡፡(ሐዋ.3፥1) በዛሬ ዘመን ያሉት አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያሉ አማኞችን ተቀብለው፤
የጸጋውንና የመዳኑን ወንጌል ከመስበክ ይልቅ የራሳቸውን ሥርዓትና መመሪያ በማሸከም አማኞችን ማጉበጣቸው ያሳዝናል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ
እንደመናፍቅና ቀኖና ጣሽ ቆጥረው ማውገዝ እንጂ ማቅረብ አይሆንላቸውም፡፡