Please read in PDF :- yeEyesus dem 3
ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ሰርቶ በጨረሰ ጊዜ “ሀያ ሁለት ሺህ በሬዎችና መቶ ሐያ ሺህ በጎች ሠዋ” ይለናል ታላቁ መጽሐፍ፡፡ (2ዜና.7÷5)፡፡በአንድ ቀን እንዲህ ያለ መስዋዕት ከቶውንም በብሉይ ኪዳን ውስጥ ቀርቦ አያውቅም፡፡ሀያ ሁለት ሺህ በሬና መቶ ሐያ ሺህ በጎች በአንድ ቀን!!! አስተውሉ! ከአንድ እስከሀያ ሁለት ሺህ ቁጠሩና እንደገና ከአንድ እስከመቶ ሐያ ሺህ ጊዜ ቁጠሩ!!! ቁጥር ብቻ ግን አይደለም የሚፈሰውንም የደም ብዛት እዩ! ከዚያ እናንተ በሰሎሞን ቦታ ቁሙ! ምን ያህል ደም በፊታችሁ እንዳለ አስተውሉ!!! የክርስቶስ ደም እንዲህ ነው ከኃጢአት ሁሉ የጋረደንና ለክብሩ የሰወረን!!!
ሰሎሞንን የመስዋዕቱ ደም ከድኖታል ፤ሰሎሞን የተኛው ሙሉ ለሙሉ በደም እንደተጋረደና በደም እንደተሸፈነ ነው፡፡እንዲህ ሆኖ ተኝቶ ሳለ ጌታ እግዚአብሔር በሌሊት ለሰሎሞን ተገለጠለት፡፡ልዩ ኪዳንም ገባለት፡፡(2ዜና.7÷11-22)፡፡የሚገርመው ግን ይህ ሁሉ መስዋዕት በቀን እየቀረበ እንኳ ፍጽምትና ቅድስት ፣አዲስና ህያው የሆነችውን መንገድ ከኢየሱስ በቀር መርቆ መክፈት የተቻለው አልነበረም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሁሉ መስዋዕቶች ፦
የሰውን ዋጋ ስለማይተካከሉ(ማር.8÷37፤ዕብ.÷10÷1)
ጊዜያዊ መፍትሔ እንጂ ኃጢአትን የማያስወግዱና ፍጹም ድህነትን(ድነትን) የማያሰጡ ስለሆኑ(ዕብ.9÷9፤10÷1)
መስዋዕቶቹ በራሳቸው ፍጹማን ስላልሆኑ
እስከመታደስ ዘመን ብቻ በምሳሌነት አገለገሉ፡፡(ዕብ.9÷9)፡፡ስለዚህም ሰው ልዩና ታላቅ ቤዛ ከኃጢአቱም ነጻ የሚያወጣው ሊቀ ካህን የሆነ ቤዛ አስፈለገው፡፡
ክህነቱ የማይለወጥ ዐቢይ ሊቀ ካህናት(ዕብ.7÷25)
የብሉዩ ሊቀ ካህን ዋና አገልግሎቱ ስለህዝቡ ህዝቡን ተገብቶ ስለኃጢአት ይቅርታ ደምን በእግዚአብሔር ፊት ይዞ መቅረብና መማለድ ነው፡፡ነገር ግን ይህ የሊቀ ካህኑ አገልግሎት ምንም እንኳ ህጉ ንጹህ ቢሆንም (ሮሜ.7÷12) እርሱ ራሱ በኃጢአት የተያዘ (ዕብ.5÷3)፣ሞት የሚከለክለውም ስለሆነ (ዕብ.7÷23) የሚያቀርበው የእንሰሳቱም ደም ፍጹም የሆነ የኃጢአትን ሥርየት ሊያስገኝ አልተቻለውም፡፡ ስለዚህም እርሱ ራሱ በኃጢአት ያልተያዘ ፣ቅዱስና ነቀፋ የሌለበት ንጹህና ከኃጢአተኞች የተለየ (ዕብ.6÷26) ሞት የማይይዘውና ለዘለዓለም በህይወት የሚኖር ዐቢይ ሊቀ ካህናት ይገባናል (ያስፈልገናል)፡፡