እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ፡፡
አሜን፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የሚለውን ቃል፥ አንድ ረዥም ጊዜን (ገላ.4፥4)
፣ የአንድ ወቅት አገዛዝን (ማቴ.2፥1-2 ፤ ሐዋ.12፥1) ፣ አንዳንዴ ሰዓት በሚለው አገላለጥ አምልኮን ወይም የመዳንን ጊዜ
(ማር.1፥15 ፤ 2ቆሮ.6፥2 ፤ኤፌ.2፥6 ፤ 2ጢሞ.1፥9) ፣ ሌላም ተግባር የተከናወነበትን ወይም የሚከናወንበትን ጊዜ (1ጢሞ.4፥1-2
፤ 1ጴጥ.1፥5-6) ፣ ውስን ጊዜንና (መዝ.102፥24) የመሲህ ኢየሱስ በምድር የነበረበትን ጊዜና (1ጢሞ.2፥6 ፤ ዕብ.1፥1)
ሌሎችንም ለማመልከት ቃሉን ይጠቀምበታል፡፡ ስለዚህ ዘመን የሚለውን
ቃል እንደሚገኝበት አውዱ፥ በጥንቃቄ ልናየውና ልንተረጎመው ይገባናል ማለት ነው፡፡
ጊዜያትን የፈጠረ፥ “የዘመኑ ቍጥር የማይመረመር” (ኢዮ.36፥26) ፣
“ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ … አንተ ግን ያው አንተ ነህ፥ ዓመቶችህም
ከቶ አያልቁም።”(መዝ.90፥2 ፤ 102፥27) የተባለለት ቅዱስ እግዚአብሔር
ነው፡፡ (ዘፍጥ.1፥5 ፤ መዝ.102፥24) ስለዚህም ዘመን ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች በስጦታነት ተሰፍሮ ፤ እንኖርበት ዘንድ የተሰጠን
በረከት ነው፡፡ ( ዘፍጥ.6፥3 ፤ ኢዮ.14፥5 ፤ 21፥21 ፤ 31፥15 ፤ 39፥4-5 ፤ 139፥16 ፤ ሐዋ.17፥26) የዘመናችን
መርሑም አንዱ ሲያልፍ ሌላው እንዲተካ “በብዙ ተባዙ” (ዘፍጥ.1፥28 ፤ 9፥1) ፤ በማለፍ ሕግ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ (መዝ.103፥15)