ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ዘንድ “አልቃሻው
ነቢይ” ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህንንም ስያሜ ያገኘበት ዋናው ምክንያት፥ ሕዝቡ በኃጢአትና በነውር ምድሪቱን እጅግ በማርከሳቸውና ፊታቸውን
ወደንስሐ ዘወር እንዲያደርጉ፥ ከእነርሱ ጋር እየተራበና እየተጠማ በመካከላቸው ሆኖ አዘውትሮ ቢናገራቸውም፥ እስራኤል ሊሰሙት ካለመውደዳቸው
ባሻገር አጥብቀው ስለተቃወሙትና ሊቀበሉት ፈጽመው ስላልወደዱት ነው፡፡
በዚህም ምክንያት በጥልቅ ሐዘን መዋጡን፥
“አንጀቴ! አንጀቴ! ልቤ በጣም ታምሞአል፥ በውስጤም ልቤ ታውኮብኛል፤ ነፍሴ ሆይ፥ የመለከትን
ድምፅና የሰልፍን ውካታ ሰምተሻልና ዝም እል ዘንድ አልችልም፡፡ … ሕዝቤ ሰንፈዋልና አላወቁኝም ሰነፎች ልጆች ናቸው፥ ማስተዋልም
የላቸውም፤ ክፉ ነገርን ለማድረግ ብልሃተኞች ናቸው፥ በጎ ነገርን ማድረግ ግን አያውቁም፡፡”፤ (ኤር.4፥19-22)፤ “ተወግተው
ስለ ሞቱ ስለ ሕዝቤ ሴት ልጅ ሰዎች ሌሊትና ቀን አለቅስ ዘንድ ራሴ ውኃ፥ ዓይኔም የእንባ ምንጭ በሆነልኝ! ሁሉም አመንዝሮች፥
የአታላዮች ጉባኤ ናቸውና ሕዝቤን እተዋቸው ዘንድ ከእነርሱም እለይ ዘንድ በምድረ በዳ የመንገደኞች ማደሪያን ማን በሰጠኝ? ምላሳቸውን
ስለ ሐሰት እንደ ቀስት ገተሩ፤ በምድር በረቱ ነገር ግን ለእውነት አይደለም፤ ከክፋት ወደ ክፋት ይሄዳሉና እኔንም አላወቁምና፥
ይላል እግዚአብሔር፡፡ ወንድምም ሁሉ ያሰናክላልና፥ ባልንጀራም ሁሉ ያማልና እናንተ ሁሉ ከባልንጀሮቻችሁ ተጠንቀቁ፥ በወንድሞቻችሁም
አትታመኑ፡፡ ሰውም ሁሉ ባልንጀራውን ያታልላል በእውነትም አይናገርም፤ ሐሰትን መናገርንም ምላሳቸው ተምሮአል፥ ክፉንም ለማድረግ
ይደክማሉ፡፡”(9፥1-5)፤ “እረኞች ሰንፈዋልና፥ እግዚአብሔርን አልጠየቁትምና አልተከናወነላቸውም፥ መንጎቻቸውም ሁሉ ተበትነዋል፡፡”(10፥21)፤
“ስለ ነቢያት፤ ልቤ በውስጤ ተሰብሮአል አጥንቶቼም ሁሉ ታውከዋል፤ ከእግዚአብሔር የተነሣ ከቅዱስ ቃሉም የተነሣ የወይን ጠጅ
እንዳሸነፈው እንደ ሰካራም ሰው ሆኛለሁ፡፡ ምድር ከአመንዝሮች ተሞልታለችና፥ ከመርገምም የተነሣ ምድር አልቅሳለች፤ የምድረ በዳ
ማሰማርያ ደርቆአል፤ አካሄዳቸው ክፉ ነው፥ ብርታታቸውም ቅን አይደለም፡፡ ነቢዩና ካህኑም ረክሰዋልና፥ በቤቴም ውስጥ ክፋታቸውን
አግኝቻለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፡፡” (23፥9-11)
|
የሚለው የነቢዩ ንግግር የሚያየው የእስራኤል ክፋት ምን ያህል እንዳቆሰለውና እንዳሳዘነው በትክክል ይገልጠዋል፡፡